TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

• " ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን መልሶ ያጢን " - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

• " ታስቦበት ኪሳራና ትርፍን ተመዝኖ የተሻለውን ማድረግ እንደሚሻል ታምኖበት የተወሰነ ውሳኔ ነው " - ትምህርት ሚኒስቴር

የትምህርት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም የክረምት ትምህርት መርሐግብር እንዳይሰጥ ያስተላለፈውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጠየቀ፡፡

ባለፉት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ጦርነት በክረምት ሥልጠና መርሐግብር ሥልጠና ላይ ያሳደረው ጫና ሳይካካስ፣ በ2015 የመምህራንና የትምህርት አመራሮች የክረምት ሥልጠና እንደማይሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር ማሳወቁ ማኅበሩን እንዳሳሰበው ለትምህርት ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ አስገንዝቧል፡፡

የሚኒስቴሩ ክልከላ በቀጣይም ችግር የሚፈጥርና የመልካም አስተዳደር ግድፈት ምንጭ እንደሚሆን ማኅበሩ አሳስቧል፡፡

የአሠራር ሥርዓት ሳይዘረጋለት ሥልጠናውን ማቋረጡ ተገቢ ስለማይሆን፣ ሐምሌ 2015 ዓ.ም ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተላለፈው ሰርኩላር እንደገና እንዲታይ ጠይቋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት ዓመታት የተዛነፈውን የትምህርት ካላንደር ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን ለተቋማቱ በላከው ሰርኩላር ጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ ደብዳቤውን ከመጻፉ በፊት ምንም ዓይነት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለማኅበሩም ሆነ ለመምህራኑ አለመስጠቱን የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ድንቃለም ቶሎሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

ትምህርታቸው ከተስተጓጎለባቸው መምህራን መካከል በዚህ ዓመት መጨረስ የነበረባቸው ፣ የመመረቂያ ጽሑፍ ብቻ የቀራቸው እንዲሁም በሚሠሩባቸው ተቋማት ትምህርቱን ጨርሰው የደረጃ ዕድገት ሊያገኙ የሚገባቸው የነበሩ ቢሆንም በሚኒስቴሩ ደብዳቤ ምክንያት ይህን ማግኘት አልቻሉም ተብሏል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) " በአንድ ወር ትምህርት ተሰጥቶ መምህር መፍጠር አይቻልም፣ በዚህ በኩል ትምህርት ጥራት እየተባለ በሌላ በኩል በአንድ ወር ዲግሪ እንደተማረ ተደርጎ ይነገራል፣ ይህ አብሮ አይሄድም ስለዚህ መታረም አለበት " ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል ፤ የትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ዕቅድ የሚሄድ በመሆኑ ታስቦበት ኪሳራና ትርፍን መዝኖ የተሻለውን ማድረግ እንደሚሻል ታምኖበት የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

#ሪፖርተር

More : @tikvahuniversity
#AddisAbaba

" የእንጀራ ዋጋ በመጨመሩ በልተን ለማደር ተቸግረናል " - ነዋሪዎች

በአዲስ አበባ ከተማ ከጤፍ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የእንጀራ ዋጋ በመጨመሩ በልተው ለማደር መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ለሪፖርተር ጋዜጣ ቃላቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ፤ ሰሞኑን የአንድ እንጀራ ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረበት 17 ብር ወደ 22 እና 24 ብር ከፍ በማለቱ፣ ገዝተው ለመጠቀም ተቸግረዋል፡፡

እንጀራን ጋግረው ለመጠቀም ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን የተናገሩት እንዲት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እናት፣ የሚከፈላቸው የ3,000 ብር ደመወዝ ከወር ስለማያደርሳቸው በብድር እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

እንጀራን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪም እንዳማረራቸውም እኚሁ እናት አክለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የእንጀራ ዋጋ በአንድ ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባት ብር መጨመሩን የተናገረው ወጣት ሻምበል ቢሆነኝ፣ ወጣቱ እንዳለው ከሆነ እንጀራን በቤት እንኳን ለማስጋገር አከራዮች " መብራት ይቆጥርብናል " በማለት ፈቃደኛ ስለማይሆኑ እየገዛ ለመብላት መገደዱን ተናግሯል፡፡

በዚህም ሰሞኑን በእንጀራ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ከሚከፈለው የወር ደመወዝ ጋር ፈፅሞ የማይመጣጠን ነው ሲል አብራርቷል።

እንጀራ ሻጮችን ዋጋ ለምን እንደጨመሩ ሲጠይቃቸው፣ " ጤፍ ጨምሯል ስለተባልን ነው "  እንደሚሉት ገልጿል።

ጋዜጣው በአንዳንድ የእንጀራ መሸጫ ሱቆች  ተዘዋውሬ ተመልክቻለው ባለው የእንጀራ ዋጋ ከ14 ብር ጀምሮ 17፣ 22 እና 24 ብር እየተሸጠ ነው።

የእንጀራ መሸጫ ዋጋ በዚህን ያህል የዋጋ ልዩነት ለምን እንዳሳየ ነጋዴዎች ሲጠየቁ የእንጀራው መወፈርና መሳሳት፣ እንዲሁም በጤፉ ላይ የሚቀላቀለው እህል መብዛት እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ስለዋጋው ጭማሪ ደግሞ የጤፍ ዋጋ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ እንደሆነም ጠቁመዋል። ተደረገ የተባለው የዋጋ ጭማሪ በመርካቶ እህል በረንዳ ባሉ መጋዘኖችም እንደታየ ተመላክቷል።

ብዙ የጤፍ አቅርቦት እንደሌለና የሚመጣው ጤፍ ደግሞ ዋጋው እየጨመረ መሆኑን አንዳንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነጋዴዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ፤ በተለይ በቢሾፍቱና በዱከም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ የሚገባውን ጤፍ፣ በአካባቢው ያሉ ሆቴሎች አርሶ አደሮችም ሆኑ ነጋዴዎች አዲስ አበባ አምጥተው ከሚሸጡበት ዋጋ በላይ ስለሚገዟቸው በአቅርቦቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ ግጭት ከጎጃምና አካባቢው ወደ መዲናዋ የሚገባው ጤፍ መቅረቱ ደግሞ አሁን ለታየው የዋጋ ጭማሪ ሌላው መንስዔ መሆኑን ነጋዴዎቹ አብራርተዋል።

ሰኞ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በእህል በረንዳ በነበረው ወቅታዊ ግብይት ፦
- ማኛ ነጭ ጤፍ 13,500 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣
- ሠርገኛ ጤፍ ከ10,000 ብር እስከ 10,700 ብር፣
- ቀይ ጤፍ ከ9,500 ብር እስከ 10,000 ሺሕ ብር ሲሸጥ መቆየቱን ለመመልከት ተችሏል።

ሌሎች ነጋዴዎች እንዳሉት ከሆነ ደግሞ በጎጃም በኩል የሚገባው ጤፍ መቅረቱ የተወሰነ እጥረትን ቢያስከትልም፣ ከአርባ ምንጭና ከባሌ፣ እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች የሚገባው ጤፍ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ አከፋፋዮችም የቻሉትን ያህል እየጫኑና እየወዱ ነው። በዚህም የምርት እጥረት አለ የሚባለውን እንደማያምኑበት ነው የተናገሩት።

ያንብቡ - https://telegra.ph/Reporter-08-23-3

#ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#የዋጋ_ንረት📈

መስከረም 2015 መጀመርያ ላይ ከ6 ሺሕ ብር በታች ይሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ለመጀመርያ ጊዜ ከ10 ሺሕ ብር በላይ ዋጋ ያወጣው ሊጠናቀቅ ሰዓታት በቀሩትና አሮጌ ብለን ልንሸኘው በተዘጋጀው 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ የጤፍ ዋጋ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ እስከ 15 ሺሕ ብር ሲደርስ ይኸው የዋጋ ጭማሪ 1 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዕጥፍ በላይ እንደደረሰ ያመለክታል።

#የስንዴ_ገበያም በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ የተመዘገበበት ዓመት ይኼው 2015 ዓ.ም. ነው፡፡

በአጠቃላይ ከጤፍና ስንዴ በተጨማሪ በሌሊችም ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ባለሆኑ ሸቀጦች ላይ በዚህ ልንሸኘው ጥቂት ሰዓታት በቀረን 2015 ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ተመዝግቧል።

የኢኮኖሚው ባለሙያ አቶ አወት ተክኤ ምን ይላሉ ?

" በሀገሪቱ ከፀጥታና አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የዋጋ ንረትን በማባባስ ዓይነተኛ ሚና ነበራቸው። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዳይስፋፉ ጭምር አድርገዋል።

በ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት ለዋጋ ንረቱ መባባስ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ባሻገር፣ መንግሥት የወሰዳቸው የፖሊሲ ዕርምጃዎች ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

ለአብነት የኢኮኖሚ የነዳጅ ጭማሪ እና ሌሎች የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔዎች ለዋጋ ንረቱ የራሳቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ይህ የዋጋ ንረት በቀጣይ ዓመትም እንዳይተላለፍ ለችግሩ መንስዔ የነበሩት፣ ለምሳሌ የፀጥታና ያለ መረጋጋቶች መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎችን በአግባቡ መተግበር ለዋጋ ንረት መርገብ መፍትሔ ሊሆኑ ይገባል፡፡ "

ያንብቡ👇
https://telegra.ph/Ethiopianreporter-09-11

#ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
ለግብፅ መግለጫ ምን ምላሽ ተሰጠ ?

" ግብፆቹ ስለ4ኛው ሙሌት በደንብ ያውቃሉ ፤ ምንም የተጣሰ መርህ የለም " - ኢ/ር ጌዲዮን አስፋው

ከሰሞኑን ኢትዮጵያ 4ኛውን ዙር የአባይ ግድብ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በይፋ ካሳወቀች በኃላ ግብፅ ሙሌቱ ህገወጥ እንደሆነና እ.ኤ.አ. በ2015 በሱዳን፣ በግብፅና በኢትዮጵያ የተፈረመውን የመርህ ስምምነት  የጣሰ ነው በሚል ቁጣ አዘል መግለጫ አውጥታ ነበር።

ለዚህ ግብፅ መግለጫ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችና ባለስልጣናት " ምንም የተጣሰ ነገር የለም ፤  መግለጫዋ ለሀገር ውስጥ የሚዲያ ፍጆታ የሚውል ነው " ብለውታል።

የኢትዮጵያ የግድቡ ተደራዳሪ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ምን አሉ ?

" ምንም የተጣሰ ነገር የለም፡፡ ግብፆች ያወጡት ነገር ትክክል አይደለም፡፡ የመርህ ስምምነቱ አልተጣሰም፡፡

በመርህ ስምምነቱ መሠረት የወጣ የሙሌት ሠንጠረዥ አለ፣ በእሱ መሠረት ነው አሁን የሞላነው፡፡

አሁን በቅርቡ የተጀመረው ድርድር የአገሮቹ መሪዎች በሰጡት መመርያ መሠረት የተጀመረና የተካሄደ ነው።

የሦስትዮሽ ድርድር ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረው ከቆመበት መቀጠል እንጂ፣ አዲስ ድርድር አይደለም።

አራተኛው ሙሌት በቅርቡ ከተጀመረው ድርድር ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡

ግብፆቹ ስለአራተኛው ሙሌት በደንብ ያውቃሉ፡፡ በተስማማነው መሠረት ነው የተሞላው። "

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ምን አሉ ?

" ሙሌቱ በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የለውም።

የእነሱ የሚዲያ እንካ ሰላንቲያ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የቀጠለ ነው፡፡

አሁን ያወጡት መግለጫም የተለመደ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ፍጆታ ነው፣ ለውስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙበት ነው፡፡

እኛ የእነሱ የሚዲያ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡

ይኼ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያከብረው ፕሮጀክት ነው፡፡ ግድቡ የትብብር እንጂ የፉክክር ምንጭ መሆን የለበትም። "

Credit - #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች አስጠልላቸው የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች የዕርዳታ እህል በመቋረጡ፣ ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑንና ለአገርም የደኅንነት ሥጋት መደቀኑ ተነገረ፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኢትዮጵያ ተፈጸመ ባሉት የዕርዳታ እህል ዝርፊያ ምክንያት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ዕርዳታ ማቆማቸው ይታወሳል፡፡

የምግብ አቅርቦቱ እንደገና እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥት እየተነጋገርኩበት ነው ቢልም፣ ዕርዳታው እየቀረበ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ የተጠለሉ የውጭ አገሮች ስደተኞች በምግብ ዕጦት እየሞቱና ሕመም ላይ መውደቃቸውን፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምን አለ ?

- ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ስታስተናግድ የዓለም አቀፉን ሕግ መሠረት በማድረግ ከለላና ጥበቃ የምታደርግ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስደተኞች የሚቀርበው ዕርዳታ በመቆሙ ቀውስ ተፈጥሯል።

- በምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱትና የሚታመሙት ወይም የሚቸገሩት ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ችግር ሲፈጠር በመሠረታዊነት የመጀመርያ ተጎጂ ሕፃናትና ሴቶች ናቸው።

- በመጠለያ ካምፕ የሚገኝን ሀብት አፈላልጎ ለመመገብ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት፣ ስደተኞቹ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ ይገቡና ሰላማዊ የኑሮ ሁኔታን የሚያናጋ ነገር እየተፈጠረ ነው።

- በአሁኑ ወቅት ምግብ ነክ ድጋፎች እየቀረቡ ባለመሆናቸእ በቀጣይ አፋጣኝ ዕርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ የከፋ ሊሆን ይቻላል። በሁሉም የአገሪቱ መጠለያ ካምፖች ችግሩ ተከቷል።

- በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን ለመታደግ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ፤ በአጭር ጊዜ ዕርዳታው እንደገና ይጀመራል የሚል እምነት አለ።

በስደተኛ ቁጥር ፦
👉 በጋምቤላ ወደ 400,000
👉 በቦሎ መልካዲዳ በሶማሌ ክልል 200,000፣
👉 በቤኒሻንጉል አሶሳ ወደ 90,000፣
👉 በአፋር 68,000፣
👉 በሶማሌ ጅግጅጋ ወደ 50,000፣
👉 አማራ ክልል ባባት 25,000፣ መተማ ወደ 40,000፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ወደ 80,000 ስደኞች ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ከ900,000 በላይ የሚሆኑት በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለተረጂዎች እየቀረበ ባለመሆኑ ወደ 400,000 የሚጠጉ በጋምቤላ ክልል ውስጥ በካምፕ የሚገኙ ስደተኞች ሕይወት አደጋ ውስጥ መውደቁን ገልጾ አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ወር ጀምሮ ዕርዳታ ያላገኙ ስደተኞች (አብዛኞቹ ከደ/ሱዳን የተሰደዱ) በምግብ እጥረት የተነሳ በሚመጣ ረሃብ ለሞትና ለከፋ ሕመም እየተጋለጡ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ኮሚሽኑ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም አገኘሁት ባለው መረጃ በምግብ እጥረት ምክንያት በጋምቤላ ብቻ 30 ሰዎች መሞታቸውን፣ 5 ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት ለከፋ ሕመም መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡

በተከሰተው የምግብ እጥረት የተነሳ ከስደተኞች መጠለያ ካምፕ ወጥተው ወደ ማኅበረሰቡ በሚገቡበት ወቅት ለሰላም ችግር መንስዔ መሆናቸው በኮሚሽኑ ሪፖርት የተገለጸ ሲሆን፣ ከመጠለያ ወጥተው በምግብ ስርቆት በመሰማራታቸውና ከቆሻሻ ላይ ምግብ ለማንሳት ሲጥሩ ሕይወታቸው ያለፉ መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡

አሁን ላይ በርካታ ስደተኞች አደጋ ላይ በመሆናቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ ኢሰመኮ አሳስቧል።

#ሪፖርተር

@tikvahethiopia
" ኢትዮጵያ ውሉ በጠፋና ተለዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥ ናት " - ጥናት

አገር በቀሉ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ውሉ በጠፋና ተለዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንደምትገኝ ገለጸ፡፡ 

ይፋ ባደረገው ጥናቱ የኢትዮጵያን ወቅታዊና የወደፊት መፃዒ ሁኔታ ዳሷል፡፡

"ኢትዮጵያ ወዴት? ቢሆንታዎች" በሚል ርዕስ የቀረበው ይኼው ጥናት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መንገራገጭ፣ የሐምሌ ጨለማና ፀደይ በማለት በሦስት ቢሆንታዎች (Scenarios) ለማስቀመጥ የሞከረ ነበር፡፡

የቢሆንታዎችን ምንነትን ወደኋላ በመመለስ ከታሪካዊ ዳራ ተነስቶ ብይን ለመስጠት የሚሞክረው ጥናቱ፣ የወቅቱን የአገሪቱን ሁኔታም ፍቺ ለመስጠት ሞክሯል፡፡

" በአንድ ማኅበረሰብ የመንግሥት ተዓማኒነት እየተሽከረከረ ሲሄድ፣ ማኅበረሰባዊ ትስስር ሲመነምንና በሕዝብ ዘንድ የፍትሕ መጓደል/ ተበዳይነት ስሜቶች ሲያንዣብቡ #ጽንፈኝነት ይነግሣል " በማለት ነው ይኸው ጥናት የኢትዮጵያን ገጽታ በማስቀመጥ ወደ ሐተታው የሚንደረደረው።

ጥናቱ በአሁኗ ኢትዮጵያ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች እንደሚታዩ ገልጾ ፖለቲካዊ መግባባት በአገሪቱ መፍጠር ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡

ያም ቢሆን ግን ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ችግሮችን ተወያይቶ የመፍታት ባህል አለመዳበሩ ትልቁ ራስ ምታት እንደሆነ ያወሳል፡፡

በዘውዳዊው ሥርዓት መውደቅ ማግሥት አምባገነናዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ በማቆጥቆጡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተስፋው መምከኑን ያስረዳል፡፡

ደርግ ወድቆ በ1983 ዓ/ም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ " የሕዝቦች እኩልነት ይፈጠራል " የሚል ተስፋ መፈጠሩን ይሁን እንጂ ይህንን ለውጥ ተከትሎ የተቀረፀው ሕገ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ይፈጥራል ቢባልም ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የጭቅጭቅ ምዕራፍ መክፈቱን ያትታል፡፡

በየታሪክ ምዕራፉ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሽግግር ተስፋ የፈነጠቁ አጋጣሚዎችን አለፍ ገደም እያለ የሚዘረዝረው ጥናቱ፣ በ2010 ዓ.ም. የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ እንደ አንዱ አጋጣሚ ያነሳዋል፡፡ 

" ለውጡ ከፈጠረው ከፍተኛ የሕዝብ ፈንጠዚያ ጀርባ ግን በለውጥ አቀንቃኞችና በቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች መካከል ውስጥ ውስጡን ውጥረት ሰፈነ " ይላል፡፡

የአዲስ ተስፋው ፍንጣቂ በለውጡ  ማግሥት ብዙም ሳይዘገይ በመጣው " የነውጥ ጊዜ " እንደተተካም ነው ጥናት ያመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ታሪክ በብዙ ፈታኝ ውጣ ውረዶች ውስጥ የማለፍ አስገራሚ ፅናት የተላበሰ መሆኑን ጥናቱ ያብራራል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ግን ፈላጭ ቆራጭነት የሰፈነበት ሆኖ መቆየቱን ይገልጻል። በኢኮኖሚውም መስክ በአስከፊ ድህነት ውስጥ አገሪቱ ተዘፍቃ መኖሯን ያትታል፡፡

ከዚህ ሁሉ ተነስቶ አገሪቱ የሐምሌ ጨለማ፣ መንገጫገጭና ፀደይ የሚል ስም የተሰጣቸው ቢሆንታዎችን ልታስተናግድ እንደምትችል ሰፊ ትንተና ያቀርባል፡፡

በሌላ በኩል የመበታተን አደጋን እንደ አንድ ቢሆንታ ያነሳዋል። " አስደንጋጭ ቢሆንም የአገሪቱ የመበታተን አደጋ የማይታሰብ ነው ለማለት አይቻልም " ሲል ነው ጥናቱ ያብራራው።

ጥናቱ ከአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ እስከ አየር ንብረት ለውጥ #ከሃይማኖት እና #ፖለቲካ ፅንፈኝነት እስከ የብሔርና ያልተማከለ አስተዳደር ውጥረት አገሪቱን ሊፈትኑ የሚችሉ ነጥቦችን ይፈትሻል፡፡

ከኢኮኖሚ አለመረጋጋት እስከ የዋጋ ንረት ውጣ ውረዶንችም ያነሳል፡፡

በሌላ በኩል፤ የአማራ ክልልና አገሪቱን ወጥረው የያዙ በየአቅጣጫው ያሉ የግጭት ሁኔታዎችን ተፅዕኖም የፈተሸ ነው። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#ኮንትሮባንድ

የመንግሥት ሆኑ ሌሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተቋማት ለኮንትሮባንድ ንግድ መቆም መፍትሔ ከመሆን ይልቅ፣ ሕገወጥ ንግድን የሚያባብሱ ሆነው አግኝተናቸዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

በየአካባቢው ያሉ ተቋማት በኮንትሮባንድ ዙሪያ የሚያከናውኑትን በሚመለከት ሲያስረዱ፣ ድርጊቱን በመቃወም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የመንግሥትና ሌሎች አካላት እንዳሉ ሁሉ፣ " ከችግሩ ጋር አብረው የሚኖሩና የሚተገብሩም " እንዳሉ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ተናግረዋል፡፡

የተቋማቱን ስምና አድራሻ ሳይገልጹ እነዚህ ተቋማት ምንም እንኳን ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ቢሆንም፣ የኮንትሮባንዲስቶቹ አካልና ተባባሪ ሆነው እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

" ሁኔታ የሚያመቻቹ፣ የሚያሳልፉ፣ መረጃ የሚሰጡ፣ ሕገወጦችን የሚከላከሉላቸው፣ የሚደብቁ፣ እንዳይያዙና እንዳይመረመሩ የሚያደርጉ፣ ዕቃዎቻቸውን በሽፋን የሚያሳልፉ፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመሥራት የሚተባበሩ… " ሲሉ አቶ ደበሌ በሕገወጥ ንግድ ላይ " ቀላል ቁጥር የሌላቸው " ተቋማት እንዴት እንደሚሳተፉ አብራርተዋል፡፡

ስለኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ሲነገር እነዚህ ችግሮች በበርካታ ተቋማት እንደሚፈጸሙ፣ ወደታችኛው የአስተዳደር አካል ሲወረድ ደግሞ ችግሮቹ " በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየሰፉ ነው " ሲሉ ኮሚሽነሩ ይገልጻሉ፡፡

ችግሩን በመቃወም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ካሉ ተቋማት መካከል፣ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከገቢዎች ሚኒስቴር በተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ የክልል የፀጥታ አካላትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡

ኮንትሮባንዲስቶች ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ሁሉ፣ ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመውን ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍል እስከ ኬንያ ድንበር ድረስ ያለውን ሥፍራም ለዝውውር እንደሚጠቀሙበት ተገልጿል፡፡

በችግሮቹ ግዝፈትና አስከፊነት ልክ አቅም ያላቸው ተቋማትን መገንባት አንደኛው ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ፣ እንደ ሕግ አስከባሪ ዓይነት ተቋማትንም በሚገባ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነሩ አውስተዋል፡፡

አቅምን ከመገንባት ባለፈም የሚወሰደው ዕርምጃ ትልቅ ሊሆን እንደሚገባና ከዚህ በፊት የተወዱት ዕርምጃዎችም ጥሩ እንደሆኑ ሲገልጹ፣ በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ እስከ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡

" ይህ ቁጥር የሕገወጥነትን ጉልበት በልኩ የሚናገር፣ የተወሰደውን ዕርምጃ በልኩ የሚናገር፣ ቀጣይ ምን መሥራት እንደሚገባንም የሚናገር ነው " ሲሉ አቶ ደበሌ ቃበታ ከሰሞኑን መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#የብድር_ገደብ

ብሔራዊ ባንክ የጣለው የብድር ገደብ በባንኮች እና ተበዳሪዎች ላይ ተግዳሮት መፍጠሩ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ / #NBE ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ዋነኛ ዓላማ ያደረገው ይህ ፖሊሲ ፣ የባንኮች የብድር ምጣኔ ካለፈው ዓመት ከ14 በመቶ በላይ እንዳይበልጥ ገደብ የጣለ ነው፡፡

በተለይ ባንኮች የሚሰጡት ብድር በገንዘብ ፖሊሲው ከተጣለባቸው ገደብ ጋር ለማጣጣም በማሰብ ቀደም ብለው የፈቀዷቸውን ብድሮች ጭምር ከመልቀቅ እንዲቆጠቡ ወይም መሰል አሠራርን እንዲከተሉ እያደረጋቸው ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ከመመርያው መውጣት ቀደም ብለው የተፈቀዱ ብድሮች ሊለቀቅላቸው እንዳልቻለ የተለያዩ ባለሀብቶችና የንግድ አንቀሳቃሾች ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ገልጸዋል።

በዚህም የተፈቀደላቸውን ብድር ታሳቢ በማድረግ የገቧቸው የቢዝነስ ስምምነቶች እየተፋረሱባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቤትና ተሽከርካሪ ግዥ ውሎች ሳይቀሩ በእንጥልጥል እንዲቆዩ ማድረጉንም ከተበዳሪዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ብድር እንዲለቀቅላቸው #ማረጋገጫ አግኝተው የነበሩት ተበዳሪዎች አሁን ላይ ብድሩን ማግኘት ለምን እንዳልቻሉ ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚያገኙት ምላሽ " አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ የጣለው የብድር ዕቀባ " መሆኑን ያስረዳሉ።

አንዳንዶቹም የተፈቀደላቸውን ብድር በትዕግሥት እንዲጠብቁ እንደተነገራቸው ያመለክታሉ፡፡

ቤት ለመግዛት ተዋውለው ከሚገለገሉበት ባንክ የፈቀደላቸውን ብድር እየተጠባበቁ የነበሩ አንድ ተበዳሪ ብድሩ እንደሚያገኙት በተገለጸላቸው ወቅት ሊለቀቅላቸው ባለመቻሉ የቤት ሽያጭ ውላቸው ሊፈርስባቸው እንደሆነ ገልጸዋል። እንዲህ ያለው ችግር በአብዛኛው በግል ባንኮች አካባቢ የሚስተዋል ነው፡፡

ያንብቡ 👇
https://telegra.ph/Reporter-Newspaper-10-17

#ሪፖርተር

@tikvahethiopia
አቶ ታምሩ ገምበታን ጨምሮ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መታሰራቸው ተሰምቷል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ታምሩ ገምበታን ጨምሮ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰሞኑን መሆኑንና አቶ ታምሩ ገምበታ ግን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ተገልጿል።

የምክትል ዳይሬክተሩ ቤት በፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መበርበሩንና ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ እንዳሉም ተመላክቷል።

አገልግሎቱን በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፣ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ፍራኦል ጣፋና አቶ ታምሩ ገምበታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከ3 ወራት በፊት ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

ተቋሙ ከፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።

በተጨማሪ ከዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በሕወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር ሲልኩ ነበር የተባሉ 16 የተቋሙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም 5 በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎችም ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በተያዘው ሳምንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተሰማው ምክትል ዳይሬክተሩን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም ከሙስና ጋር በተያያዘ መጠርጠራቸው ተገልጿል፡፡

ምንጭ፦ #ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia
የሀገር_ውስጥ_ተፈናቃዮች_የሰብአዊ_መብቶች_ሁኔታ_ዓመታዊ_ሪፖርት.pdf
3.8 MB
#ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) 2ኛውን በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ የሚያተኩር ዓመታዊ ሪፖርት በቀናት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡

በሪፖርቱ ምን አለ ?

- ዜጎችን ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው ያፈናቀሉ፣ የሰው ሕይወት ያጠፉ፣ ሀብት ያወደሙ፣ አካላዊ ጉዳት ያደረሱ ቡድኖችና ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በቂ ዕርምጃዎች ባለመወሰዳቸው የሕግ በላይነት፣ ተጠያቂነትንና የተፈናቃዮችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚነፍግ ነው።

- በዘፈቀደ ለሚደረጉ የማፈናቀል ድርጊቶች አስተማሪ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ አይደሉም።

- ዘላቂ የመፍትሔ አማራጮች አተገባበርም የመፈናቀል ምክንያት የሆኑትን የደኅንነት ሥጋቶች ባስወገደ፣ ተፈናቃዮችንና ተቀባይ ማኅበረሰብን ባሳተፈ፣ የተፈናቃዮችን ፍላጎት ባገናዘበ፣ እንዲሁም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በሚያቋቁም ሁኔታ ባለመሆኑ፣ ለዳግም መፈናቀል የሚያጋልጥ ነው።

- አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኙ በመጠለያ ጣቢያዎችና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው መኖር ከጀመሩ በትንሹ ሦስት ዓመታት አልፏቸዋል።

- ተገቢው ጥበቃ የማይደረግላቸው፣ እንዲሁም የሲቪልነት ባህሪን ያልጠበቁ በወታደራዊ ካምፖች አካባቢ የሚኖሩ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች መኖራቸው፣ የተፈናቃዮች የደኅነነት ሁኔታ አደጋ ላይ መሆኑን እንደሚያሳይ፣ በተጨማሪም መንግሥት በካምፓላ ስምምነት መሠረት የተጣለበትን ግዴታ በአግባቡ አለመወጣቱን የሚጠቁም ነው።

- መንግሥት ፈርሞ የተቀበለውን የካምፓላ ስምምነትን ለማስፈጸም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ሥራ ላይ አለመዋሉና የተፈናቃዮችን ጉዳይ በባለቤትነት የሚያስተዳድር ተቋማዊ አደረጃጀት የለም።

- መፈናቀልን ለመከላከል ለተፈናቃዮች የሚደረጉ የጥበቃና ድጋፍ ሥራዎች፣ እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ሒደቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሁንም አሳሳቢነታቸው ቀጥሏል።

- የተፈናቃዮች ምዝገባና ሰነድ የማግኘት ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዳይከናወን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በተጨማሪ ተፈናቃዮች ሌሎች የመንቀሳቀስና የማኅበራዊ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸውን ለመጠቀም እንዳይችሉ አድርጓል።

- በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው መፈናቀል ኃይል በተቀላቀለባቸው ግጭቶች ምክንያት የሚከሰት በመሆኑ መፈናቀልን ለመከላከልና በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት፣ በዋናነት ግጭቶችን ወቅታዊ በሆነ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ #ሪፖርተር

(ከኢሰመኮ የተላከ ሙሉ ሪፖርት ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ወስኖ የነበረው ፍርድ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መሻሩን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው የሦስተኛ ዓመት የአንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በወሰነው መሠረት፣ ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉትን ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ቤቶች እንዲሰጡ የሚለው ውሳኔ የተወሰኑ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችን የሚጥሱና ተቀባይነት የላቸውም በማለት በሙሉ ድምፅ ሽሮታል።

በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተፈርሞ ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ፣ በ2005 ዓ.ም ወጥቶ የነበረውን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዕጣ ድልድል ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ የሚሰጠው መመርያ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው በምክር ቤቱ ታምኖ እንዲታይ ይገልጻል፡፡

" ሕገ መንግሥታዊ የአካታችነትና የፍትሐዊነት መርህን የጣሰ " ሲል የመመርያውን አንድ አንቀጽ የገለጸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ፣ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቁጠባ ቤቶች ዋነኛ ዓላማ 40 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ከባንክ በተመቻቸ 60 በመቶ ክፍያ በመደገፍ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ነው የሚያስረዳው፡፡

ሆኖም አንደኛው የመመርያ አንቀጽ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ድንጋጌ መግባቱ ‹
" የመመርያውን ግልጽ ዓላማና መንፈስ ያልተከተለ " ሲል ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

" ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ መስጠት በመርሐ ግብሩ ለተመዝጋቢዎች እኩል ዕድል ለማሰጠት የታለመውን መሠረታዊ ዓላማ የጣሰ ነው፤ " ሲል ደብዳቤው ያብራራል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብርን የሚያስፈጽመው መመርያ በሰጣቸው መብት መሠረት ሙሉ ለሙሉ የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ ከቆጠቡ በኋላ፣ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የጠበቁ 761 ቆጣቢዎች በዕጣ ማውጣት መርሐ ግብሩ ላይ ቅድሚያ ሳይሰጣቸው 40 በመቶ ከቆጠቡት ጋር እኩል ነበር የተሳተፉት፡፡

ለዚህም ነበር 761 ተመዝጋቢዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝን በመክሰስና እስከ ሰበር ድረስ በመድረስ ሊፈረድላቸው የቻለው፡፡

በፍርድ ቤቶች ተወስኖ የነበረው እየተገነቡ ያሉና ዕጣ ያልወጣላቸውን ቤቶች፣ ከዚህ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች እንዲተላለፉ ነበር፡፡

በውሳኔው ቅር ተሰኝቶ የነበረው የከተማ አስተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከአንድ ዓመት በፊት ለሕገ መንግሥታዊው ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ አቅርቦ፣ ጉባዔው ጉዳዩን በመመርመር በዚህ ዓመት መስከረም ወር ምክር ቤቱ ሲከፈት ውሳውን አሳልፏል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መርሐ ግብር ለማስፈጸም ወጥቶ በነበረው መመርያ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ የሚያሰጠውን አንቀጽ፣ ከመስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ " ኢሕገ መንግሥታዊ " በመባሉ እንደማይሠራ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም አውጥቶት የነበረው የዚህ መመርያ ድንጋጌ፣ ደብዳቤው ከደረሰው ከኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ እንዲያሻሽልና ውጤቱን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ ያሳስባል፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤውን በግልባጭ ለሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደሮች አሳውቋል።

#ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia
" የተሸለምኩትን 100 ሺህ ብር በትግራይ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ሠጥቻለሁ " - ዕበ ለገሠ

የግሉን አውሮፕላን ሠርቶ በሰማይ ላይ መንሳፈፍ የልጅነት ምኞቱ ነበር ፣ በሽረ እንደሥላሴ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዕበ ለገሠ።

ሐሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ እልህ አስጨራሽ ጉዞ ማድረጉን ይናገራል። ከበርካታ ጥረቶች በኋላ ለሦስት ደቂቃ ያህል መብረር የምትችል ሔሊኮፕተር መስራቱን እንደቻለ ገልጿል።

በስምንት ወራት ውስጥ ተሠርታ የተጠናቀቀችው ሔሊኮፕተሯ፣ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባት ዕበ ተናግሯል።

ለአብራሪው ብቻ የሚሆን ቦታ ቢኖራትም፣ እስከ አራት ሰው ወይም አራት ኩንታል ጭነትን ተሸክማ መብረር እንደምትችል ተናግሯል፡፡

ሔሊኮፕተሯ ተጠናቃ ወደ ሥራ ስትገባ፦
- ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎዎችን ለማጥፋት፣
- የአንበጣ መንጋን ለመከላከልና ቅኝት ለማድረግ ታገለግላለች፡፡ ሰዎች ለትራንስፖርት ሊጠቀሙበትም ይችላሉ ብሏል።

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ውድድር፣ ሔሊኮፕተር ሠርቶ በማቅረብ አንደኛ በመውጣት 100 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።

የሽልማቱን ገንዘብ በትግራይ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንደሰጠ ዕበ ጠቁሟል፡፡

ሔሊኮፕተሯ ተሻሽላ ገበያ ላይ መዋል የምትችልና የተሠራችበት ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ በአካባቢ የሚገኙ መሆናቸው ዕበን ለአሸናፊነት አብቅቶታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጠራውን ለማገዝ ቃል እንደገባለት የገለጸው ዕበ፣ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ነገር ይዞ ለመቅረብ እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡ #ሪፖርተር

Via @tikvahuniversity
#ጥናት

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ጥራታቸው ተጠብቆ ባለመገንባታቸው፣ በዕጣ የቤት ባለቤት የሆኑ ዕድለኞች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት (ACRC) እና ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) በጋራ ባደረጉት ጥናት ማረጋገጥ መቻላቸውን አስታውቀዋል።

ሁለቱ ተቋማት ጥናቱን ለአንድ ዓመት ያህል ነው ያደረጉት።

በጥናቱ ከ6 በላይ ከፍተኛ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊ ሽግግርና በወጣቶች አቅም ግንባታና በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተደረገ ነው።

ጥናቱ ምን ይላል ?

- በአዲስ አበባ ከተማ ከመነሻውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፡፡

- መንግሥት 40/60 ወይም የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በዕጣ ለደረሳቸው ሲያቀርብ ጥራታቸውን በጠበቀ መንገድ ስለማይገነቡ፣ ዕድለኞች መልሰው አፍርሶ ለመሥራት ይገደዳሉ ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ።

- የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ዕድለኞች ፦
* ለኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ፣
* የሲራሚክ ንጣፍ፣
* ለመፀዳጃ ቤት መስመር፣
* ግድግዳ እንደገና ለመሥራትና ሌሎች የጎደሉ ነገሮች ለማሟላት ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ።

- እነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ መንግሥት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከግብዓት ጀምሮ እስከ ባለሙያ ድረስ ጥራታቸውን በመጠበቅ ማቅረብ ይኖርበታል።

በተጨማሪ ...

በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ተስማሚ የሆኑ ነገሮች እንደሌላቸው ታይቷል። ወጣቶች በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ፣ በኢመደበኛ ዘርፍና በጤና ላይ ያላቸውን በጎ ተግባራትና ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው በጥናቱ ተካተዋል።

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አብዛኛውን የቤት አቅርቦት ተፈጻሚ የሚሆነው በመንግሥት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ቤት አልሚ ድርጅቶች ተቋቁመው የማኅበረሰቡን የቤት ጥያቄ እየመለሱ መሆናቸው የሚበረታታ ነው።

በቤት አቅርቦት ላይ ለውጦች እየመጡ ቢሆንም አሁንም የመሬት አቅርቦት፣ እንዲሁም በዝቅተኛና በመካከለኛ ገቢ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቤት ለመሥራት ቢፈልጉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው ነው።

👉 በአጠቃላይ ጥናት የተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትና በጥናቱ የቀረቡ ግኝቶች መሬት ወርደው ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች የሚቀርቡ ይቀርባሉ ተብሏል።

#ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia
#AddisAbaba

ለነዳጅ ማደያዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በሙሉ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

ቢሮው በተለያዩ ባለሙያዎች እያደረገ ባለው የመስክ ሥራ አማካይነት በከተማዋ ሕገወጥ የነዳጅ ንግድ በመስፋፋቱ ምክንያት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቢሮው ባልደረባ ተናግረዋል።

እኚሁ ባልደረባ ምን አሉ ?

- ቢሮው ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም የነዳጅ ማደያ መመርያው በሚያዘው መሠረት ታሽጎ ክስ ይመሠረትበታል።

- በተለያዩ ሱቆች፣ በመኖሪያ ቤት፣ በመንገድ ላይና ሕጋዊ የነዳጅ ማደያ ቦታ ባልሆኑ አካባቢዎች ነዳጅ በዕቃ በመቅዳት ሽያጭ እየተከናወነ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

- በቢሮው መመርያ መሠረት ሕጋዊ ደብዳቤ ከተጻፈላቸው ድርጅቶች ውጪ፣ በቀንም ሆነ በሌሊት ምንም ዓይነት የበርሜል ሽያጭ ማካሄድ አይቻልም።

- መመርያውን መሠረት በማድረግ ለነዳጅ አዳዮች በተደጋጋሚ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ እንዲሁም ደብዳቤ እንዲደርሳቸው በማድረግ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ጥረት እየተደረገ ነው።

- በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሕጋዊ ደብዳቤ ከሚጻፍላቸው የንግድ ድርጅቶችና ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በስተቀር፣ በዕቃና በበርሜል የነዳጅ ሽያጭ የተከለከለ ነው፡፡

- የነዳጅ ማደያዎቹ በዕቃ እንዲሸጡ የሚፈቅደውን በየስድስት ወራት የሚታደሰውን ደብዳቤ መያዝ ግዴታ ነው።

- ያለ ደብዳቤ ነዳጅ በመግዛት ሕገወጥ ሽያጭ የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ማደያ መግባት ለማይችሉ አነስተኛ ባጃጆች፣ እንዲሁም የነዳጅ እጥረት በሚኖርበት ወቅት በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ ነው።

- በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የቤንዚን ዋጋ 77.65 ብር ሲሆን፣ በዕቃ በመቅዳት ውጪ የሚሸጠው እስከ 80 ብር ድረስ ነው።

- በዕቃ ተቀድቶ የሚሸጠው የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከመንግሥት ታሪፍ ውጪ ከመሸጥም በላይ፣ እንደ ቤንዚን ያሉ ምርቶች ደግሞ ወዲያውኑ አገልግሎት ላይ ማዋል እንጂ ማስቀመጥ ለደኅንነት አሥጊ ናቸው።

- ይህ እየታወቀ የነዳጅ ማደያ ድርጅቶች ስህተት እንዳይፈጽሙ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ፣ እንዲሁም ቢሮው ባደረገው የመስክ ምልከታ በየመንገዱ ሲሸጥ የተገኘውን በመመልከት ሽያጭ እንዳያካሂዱ ክልከላ ብቻ ያደረገ በመሆኑና እስካሁን የቅጣት ዕርምጃ ባለመወሰዱ፣ ሕገወጥ ድርጊቱ ሳይስፋፋ ዕርምጃ ለመውሰድ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው።

የንግድ ቢሮው ዕርምጃ መውሰድ የሚችለው በንግድ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ላይ ብቻ በመሆኑ፣ ሕገወጥ ድርጊት የሚከናወነው በመኖሪያ ቤት ከሆነ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ፣ ከሕገወጥና ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን ምርቱ እንዲወረስና ክስ እንዲመሠረት ይደረጋል ተብሏል። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#ድርቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቅን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ " አሁን የተከሰተው ከ77ም ያልተናነሰ ነው " በሚል ከዚህ ቀደም የተሰጡ አስተያየቶችን ኮነኑ። " የሚታረስ መሬት እያለን የሰው ጉልበት እያለን ድህነንት እና ልመናን ጌጥ አናድርገው " ያሉት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ " ተቸግረዋል ሊያልቁ ነው ሲሉን እንደ ሽልማት አንውሰደው ኮሮና መጣ ሊረግፉ ነው አሉ ረገፍን እንዴ ? አልረገፍንም ሟርት ነው።…
#OxfamInternational

ኦክስፋም ኢንተርናሽናል በትግራይ ክልል ጦርነትና የዝናብ እጥረት ያስከተለውን የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ጠቅሶ፣ " ሰው ሲራብ ቆሞ መመልከት የሞራልና የፖለቲካ ኪሳራ ነው " ሲል አስታወቀ፡፡

ኦክስፋም ፤ በረሃብ የተጠቁ ቤተሰቦች ችግሩን ለማምለጥና በሕይወት ለመትረፍ ሲሉ የመጨረሻ ተስፋ አስቆራጭ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

ኦክስፋን አነጋገርኳቸው ያላቸው በአንድ ትምህርት ቤት ከተጠለሉ ቤተሰቦች መካከል  ፦
- እናቶች፣ ልጆቻቸው ተርበው ቀኑን በሙሉ የሚያበሏቸው ነገር ማጣታቸውን፣
- እናቶች ልጆቻቸው ረሃቡን ሊቋቋሙ ባለመቻላቸው የረሃብ ሕመምን ለማስታገስ ለረጅም ሰዓታት እንዲተኙ እንደሚያስገድዷቸው
- ሰዎች ለእንስሳት የሚሆኑ ሥራ ሥሮችን ለመመገብ መገደዳቸውን መናገራቸውን ገልጿል፡፡

ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውንም አክሏል፡፡

የኦክስፋም የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ፤ " አሁን የሚታየው የችግሩ ጫፍ  ነው " ብለዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አስከፊ የሆነ ረሃብ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉና ዜጎች ቀጣዩን ምግባቸውን ማግኘት ከባድ የሆኑ መንገዶችን እያለፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አስከፊ ከሆኑ የሰብዓዊ ቀውስ ክስተቶች አንዱ ለሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ የዕርዳታ አቅርቦት፣ ይጠበቅ ከነበረው 4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት የተቻለው 34 በመቶ ብቻ መሆኑን ኦክስፋም ጠቁሟል፡፡

አፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ካልተደረገ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ኮንሰርን ወርልድ ዋይድ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ተከስቷል ያለው ረሃብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡

በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ከተሰጣቸው መሰል ክስተቶች እጅግ የላቀ መሆኑን ድርጅቱ በሪፖርቱ አመላክቷል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በትግራይ እና በአማራ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት 372 ሰዎች መሞታቸውን ፤ 23 ህፃናት በአልሚ ምግብ እጥረት ምክንያት ተገቢዉን ዕድገት ባለማግኘታቸዉ ሞተው መወለዳቸውን ማረጋገጡ ማሳወቁ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ " ድርቅ ለኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ባህላችንና እንደ ዓድዋ ድል ለ100 ዓመታት ሲጎበኘን የቆየ ጉዳይ በመሆኑ፣ እንደ አዲስ ሊወራ የሚችል ነገር አይደለም " ብለው ነበር።

" ድርቁን መንግሥት አላመጣውም " ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ " ድርቅን እንደ ፖለቲካ ማየት የለብንም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር አለ፣ ችግኝ እንትከል ሲባል ችግኝ ምን ያደርጋል ? ድርቅና ረሃብ አለ ስንዴ እናምርት ሲባል ስንዴ ምን ያደርጋል? ካልን በኋላ ድርቅ መጣ ብለን ብንጮኸ ትርጉም የለውም " ሲሉ አስረድተዋል፡፡

" ድርቁን ለፖለቲካ መጠቀም ጥፋት ነው " ብለው፤ ባለፉት 4 ወራት 500 ሺሕ ኩንታል እህል በመንግሥትና በተራድኦ ድርጅቶች ትብብር ለተረጂዎች መላኩን ተናግረዋል፡፡

" ይህ ሀብት በቂ ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅም እያለው በረሃብ የሚሞት ሰው ዓይተን ዝም አንልም " ብለዋል፡፡

" እስካሁን ባለኝ መረጃ በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም " ያሉት ዶ/ር ዐቢይ  " መንግሥት ትናንት እንዳደረገው ዛሬም የሚራብ ሰው ካለ ፕሮጀክት ሁሉ አጥፎ በረሃብ እንዳይሞት ከሕዝቡ፣ ከባለሀብቶችና ከክልል መንግሥት ጋር በመሆን የሚችለውን ሁሉ ይሰራል " ብለዋል።

#ሪፖርተር

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
በአዲስ አበባ የመሬት አገልግሎቶች ታገዱ። በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት ተከናውኖ በአዳስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ የተወሰነውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ የሠራተኞች የባህሪ እና የቴክኒክ ፈተና ተሰጥቶ ውጤቱ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። በዚህም አዲስ በተጠናው መዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት መሰረት የሰራተኞች ድልድል ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከዛሬ…
" ዓርብ መጋቢት 6 ምሽት ወደ ትግበራ እንዲገባ ይታወጃል " - ዶ/ር ጣሰው ገብሬ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው የወደቁ ከ7,500 በላይ ሠራተኞች ከደረጃ ዝቅ ተደርገው የተመደቡበት የሥራ ዕርከን ድልድል መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ፤  " ፈተና ያላለፉት ከደረጃ ዝቅ ብለው ነው የሚሠሩት። ድልድሉ ስለተጠናቀቀ ደብዳቤው በየተቋሙ ይሰጣል " ብለዋል።

" ከሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለ5 ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠናቸው ነው " ያሉት ኃላፊው " 2ኛው ዙር ሥልጠና ከመጪው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 2 እስከ ዓርብ መጋቢት 6/ 2016 ዓ.ም. ይሰጣል። ዓርብ መጋቢት 6/ 2016 ዓ.ም. ምሽት ወደ ትግበራ እንዲገባ ይታወጃል፣ ሥልጠናው እንዳለቀ ወደ ትግበራ ነው የሚገባው " ብለዋል።

በሌላ በኩል ፤ የሠራተኞች ድልድል እንደ አዲስ ተካሂዶ እስኪጠናቀቅ ድረስ በከተማው ሁሉም ክ/ከተሞች " ማናቸውም የመሬት አገልግሎቶች " ለአጭር ጊዜያት መታገዳቸው ይታወሳል።

ታዲያ በመጪው ሳምንት ድልድሉ ይፋ ሲሆን የመሬት አገልግሎቶች መሰጠት ይቀጥላሉ ወይ ? ተብለው ከጋዜጣው የተጠየቁት ዶ/ር ጣሰው ፤ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

ጋዜጣው ግን ከመጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ የሥራ ዕርከን ድልድል በኋላ የመሬት ሥራ አገልግሎት በቅርብ እንደሚጀመር በዘርፉ ከተሰማሩ ምንጮች መስማቱን አመላክቷል። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#AU #Fraud #CBE

ቀሲስ በላይ መኮንን ከአፍሪካ ኅብረት ኦፊሳላዊ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ የተለያዩ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ #ከ6_ሚሊዮን_ዶላር_በላይ (367 ሚሊዮን ብር) ለማዘዋወር ሲሞክሩ ነው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ፍድር ቤት ቀርበውም ለፖሊስ ተጨማሪ ቀን ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዜዳንት አቶ አቤ ሳኖ ምን አሉ ?

" በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለው የአፍሪካ ህብረት ሒሳብ የወጣ ገንዘብ የለም።

አንድ ሰው ሀሰተኛ ሰነዶችን ተጠቅሞ ለማውጣት ቢሞክርም እዛው በቦታው ላይ ተይዟል።

የማጭበርበር ሃሳብና ገንዘብ ለመውሰድ ጥረት ቢደረግም ማክሸፍ ችለናል። ይህንን የሞከሩት ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ናቸው። እኔ የማውቀው ይህን ብቻ ነው።

በመሰረቱ ጥሬ ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ሊሰጥ አይችልም። አጭበርባሪው መጥቶ  ሲጠይቅ ይህን እንኳን አያውቅም ነበር።

ሰውዬው እዚህ ሀገር የዶላር አካውንት ከሌለው ገንዘቡ ቢተላለፍም የትም ውስጥ ሊገባ አይችልም።

አጭበርባሪዎች በየቀኑ ነው ወደ ባንካችን የሚመጡት ፤ ባንክ ስለምንሰራ ይህ የተለመደ ነው። ነገር ን ሁሌም የማጭበርበር ድርጊቶቹ ከመሳካታቸው በፊት እንደርስባቸዋለን። ለፍርድም እናቀርባቸዋለን።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፥ የደንበኞቹን ሒሳቦች የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ያንን እያደረግን ነው። የአፍሪካ ህብረት እስካሁን ድረስ በይፋ ቅሬታ አላቀረበብንም። "

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአፍሪካ ኅብረት ምንጭ ምን አሉ ?

"የእኛ ሒሳብ ላይ መሰል ማጭበርበር ሲያጋጥም ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

አሁን ላይ ማጭበርበሩ #በተከበሩ_ሰዎች አማካኝነት እየተሞከረ ነው። ይህ ደግሞ በጣም አስጨንቆናል። አንድ ቀን ባለስልጣናት ተመሳሳይ ነገር ላለማድረጋቸው ምንም አይነት ዋስትና የለንም።

እምነት እያጣን ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለደሞዝ አነስተኛ መጠን ያለው ፎሬክስ (የውጭ ምንዛሬ) ለመያዝ ወስነናል።

ይህን መሰሉ ሁኔታ የድርጅቱን ገንዘብ በውጭ ማቆየት እንድናስብ እያስገደደን ነው። "

https://telegra.ph/The-Reporter-04-21 #ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Ethiopia

ትላንትና ማክሰኞ #ከሀዋሳ ወደ #አዲስ_አበባ በመብረር ላይ እያለ የደኅንነት ችግር ሊያስከትል የሚችል ክስተት በገጠመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ቁጥር #ET154 ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጥልቅ የሆነ የደኅንነት ምርመራ ሊያደርግ እንደሆነ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

ትላንት ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ከፍተኛ ጭስ መከሰቱን፣ ነገር ግን በመንገደኞች ላይም ሆነ በአውሮፕላኑ ላይ ምን ዓይነት እክል ሳይፈጠር ቦሌ ኤርፖርት በሰላም ማረፉ መገለጹ ይታወሳል።

አውሮፕላኑ ውስጥ ለጊዜው በምን ምክንያት እንደተነሳ ያልታወቀው ጭስ መንገደኞችን ከፍተኛ ድንጋጤና ፍርኃት ውስጥ አስገብቷቸው ነበር።

የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ባስተላለፉት የደኅንነት ጥንቃቄ ዕርምጃ መሠረት ሁሉም ተሳፋሪዎች በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመውን የአየር መሳቢያ የፊት ጭምብል (oxygen mask) እስከማድረግ ደርሰው ነበር።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የበረራ ደኅንነት ክፍል እክል የገጠመው አውሮፕላን ቀጣይ በረራ እንዳያደርግ በማገድ በበረራ ወቅት ያጋጠመውን የደኅንነት ክስተት እንደሚያጣራ ሪፖርተር ጋዜጣ ስማቸው ያልተገለጹ የተቋሙን ምንጮች ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።

እኚሁ ምንጮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየር መንገዱ በሚሰጠው የአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት ላይ የደኅንነት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ደጋግመው መከሰታቸውን አስታውሰው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አጠቃላይ የደኅንነት ፍተሻ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ባለፈው ጥር ወር 2016 ዓ/ም ላይ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ ሲበር የነበረ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን በመቐለ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ በሚሞክርበት ወቅት ከማረፊያው አስፋልት ውጪ የመውጣት እክል ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።

ሌላው የመንገደኞች አውሮፕላን በተመሳሳይ በአርባ ምንጭ አውሮፓላን ማረፊያ ከማረፊያ መስመሩ (ራንዌይ) የመውጣት እክል ገጥሞት እንደነበር ተስምቷል።

በአጠቃላይ በአንድ ዓመት 4 የደኅንነት እክሎች የተመዘገቡ መሆኑን ጋዜጣው ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ጠቁሟል።

ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲበር የነበረውን ጨምሮ እክል ያጋጠማቸው አውሮፕላኖች ' #Q400 ' በመባል የሚታወቁት አየር መንገዱ በአገር ውስጥ እና ወደ ጎረቤት አገሮች ለሚደረጉ በረራዎች የሚገለገልባቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 178 አውሮፕላኖች መካከል 33 የሚሆኑት Q400 በመባል የሚታወቁት ለመካከለኛ ርቀት የሚጠቀምባቸው አውሮፕላኖች ናቸው። #ሪፖርተር

@tikvahethiopia
#AddisAbaba⛽️

በአዲስ አበባ የሚታየው የነዳጅ እጥረት በቀጣይ ቀናት እንደሚፈታ የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት አሳውቋል።

የነዳጅ እጥረት በከተማዋ መከሰቱን የገለጸው ድርጅቱ " እጥረቱ ያጋጠመው በዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል ምክንያት እሑድ ሰኔ 9 በማግሥቱ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ/ም ነዳጅ ከጂቡቲ ባለመጫኑ ነው " ብሏል።

የነዳጅ ማጓጓዝ ሒደቱ አምስት እና ስድስት ቀናትን የሚወስድ መሆኑንና አሁን የሚስተዋለው እጥረት በመጪዎቹ ቀናት እንደሚፈታ አሳውቋል።

ከሱሉልታ መጠባበቂያ ቤንዚን ከአዋሽ መጠባበቂያ ደግሞ ናፍጣ እየተጓጓዘ መሆኑንም በማመልከት የነዳጅ ችግሩ በእርጠኝነት በ2 ቀናት እንደሚፈታ ተናግሯል።

በየተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ከሚታየው የነዳጅ እጥረት ባለፈ ማደያዎች ነዳጅን ከተጠቃሚዎች እንደሚደብቁ አሽከርካሪዎች ለሪፖርተር በሰጡት ቃል ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ በሆነ መንገድ በውኃ ፕላስቲኮች ጭምር የሚሸጡ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ባለፉት ሳምንታት በመዲናዋ ነዳጅ ለመቅዳት የሚጠብቁ ረዣዥም የተሽከርካሪ ሠልፎች መታየታቸውንና አሁንም እጥረቱ እንዳለ አክለዋል፡፡ #ሪፖርተር

@tikvahethiopia