የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ወስኖ የነበረው ፍርድ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መሻሩን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው የሦስተኛ ዓመት የአንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በወሰነው መሠረት፣ ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉትን ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ቤቶች እንዲሰጡ የሚለው ውሳኔ የተወሰኑ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችን የሚጥሱና ተቀባይነት የላቸውም በማለት በሙሉ ድምፅ ሽሮታል።

በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተፈርሞ ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ፣ በ2005 ዓ.ም ወጥቶ የነበረውን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዕጣ ድልድል ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ የሚሰጠው መመርያ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው በምክር ቤቱ ታምኖ እንዲታይ ይገልጻል፡፡

" ሕገ መንግሥታዊ የአካታችነትና የፍትሐዊነት መርህን የጣሰ " ሲል የመመርያውን አንድ አንቀጽ የገለጸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ፣ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቁጠባ ቤቶች ዋነኛ ዓላማ 40 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ከባንክ በተመቻቸ 60 በመቶ ክፍያ በመደገፍ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ነው የሚያስረዳው፡፡

ሆኖም አንደኛው የመመርያ አንቀጽ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ድንጋጌ መግባቱ ‹
" የመመርያውን ግልጽ ዓላማና መንፈስ ያልተከተለ " ሲል ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

" ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ መስጠት በመርሐ ግብሩ ለተመዝጋቢዎች እኩል ዕድል ለማሰጠት የታለመውን መሠረታዊ ዓላማ የጣሰ ነው፤ " ሲል ደብዳቤው ያብራራል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብርን የሚያስፈጽመው መመርያ በሰጣቸው መብት መሠረት ሙሉ ለሙሉ የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ ከቆጠቡ በኋላ፣ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የጠበቁ 761 ቆጣቢዎች በዕጣ ማውጣት መርሐ ግብሩ ላይ ቅድሚያ ሳይሰጣቸው 40 በመቶ ከቆጠቡት ጋር እኩል ነበር የተሳተፉት፡፡

ለዚህም ነበር 761 ተመዝጋቢዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝን በመክሰስና እስከ ሰበር ድረስ በመድረስ ሊፈረድላቸው የቻለው፡፡

በፍርድ ቤቶች ተወስኖ የነበረው እየተገነቡ ያሉና ዕጣ ያልወጣላቸውን ቤቶች፣ ከዚህ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች እንዲተላለፉ ነበር፡፡

በውሳኔው ቅር ተሰኝቶ የነበረው የከተማ አስተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከአንድ ዓመት በፊት ለሕገ መንግሥታዊው ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ አቅርቦ፣ ጉባዔው ጉዳዩን በመመርመር በዚህ ዓመት መስከረም ወር ምክር ቤቱ ሲከፈት ውሳውን አሳልፏል፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መርሐ ግብር ለማስፈጸም ወጥቶ በነበረው መመርያ ሙሉ ለሙሉ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ የሚያሰጠውን አንቀጽ፣ ከመስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ " ኢሕገ መንግሥታዊ " በመባሉ እንደማይሠራ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም አውጥቶት የነበረው የዚህ መመርያ ድንጋጌ፣ ደብዳቤው ከደረሰው ከኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ እንዲያሻሽልና ውጤቱን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ ያሳስባል፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤውን በግልባጭ ለሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደሮች አሳውቋል።

#ሪፖርተር_ጋዜጣ

@tikvahethiopia