TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#Afar

በከባድ መሣሪያ ጥቃት 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን ተሰማ።

ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት የአፋር ክልል ነዋሪ የሆኑት አቶ ሁሞ ኢብራሂም ከቀናት በፊት በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሚስታቸውንና 5 ልጆቻቸውን አጥተው እጅግ ከባድ ሐዘን ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል።

ቢቢሲ በጎ ፈቃደኞችንና ከአካባቢው የወጡ ሰዎችን በማነጋገር በሰራው ዘገባ ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 8 ምሽት በተፈፀመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል።

በጥቃቱ 10 የቤተሰብ አባሎቻቸው የተገደሉባቸው አቶ ሁሞ እና ቤተሰባቸው ይኖሩ የነበረው 'አዳ' የምትባል ትንሽ ከተማ ነበር።

ከተማዋ ከበርሃሌ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ እንደሆነች በሰመራ ነዋሪ የሆኑት የአቶ ሁሞ የቅርብ ዘመድ አቶ ያሲን ከድር ገልፀው አጠቃላይ ዘመድ በከባድ ሐዘን ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቃቱ ልጆቻቸውን ይዘው በመሸሽ ላይ ከነበሩት የቤተሰብ አባላት መካከል 5 ህጻናት፣ እናት፣ የእናት እናት [አያት]፣ የእናት ወንድምና የአባት እህት 2 ልጆች መሆናቸው ተገልጿል።

አባወራው አቶ ሁሞ ቀድመው ከአካባቢው ተፈናቅለው ወጥተው ስለነበር በቤተሰባቸው ላይ ከደረሰው አደጋ ሊተርፉ ችለዋል። ሙሉ ቤተሰባቸውን ያጡት አባት ሐዘኑን ሊቋቋሙ በማይችሉት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

"ምግብ አይበሉም። እንደ ድንገት የወረደባቸውን መዓት መቋቋም አልቻሉም። የሃይማኖት አባቶች እያጽናኑዋቸው ነው" ሲሉም ከባድ የሃዘን ስሜት ላይ መሆናቸውን አቶ ያሲን ተናግረዋል።

ቢቢሲ አቶ ሁሞን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም በደረሰባቸው መሪን ሐዘን ምክንያት ከማንም ጋር እንደማይነጋገሩ ዘመዶቻቸው መግለፃቸውን በዘገባው ጠቅሷል።

ከሟቾች በተጨማሪ 13 ሰዎች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸው ዱብቲ ሆስፒታል ይገኛሉ። #BBC

@tikvahethiopia
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
#Afar

የዓለም ምግብ ፕሮግራም [ WFP ] በአፋር ክልል በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል።

ድርጅቱ በአፍዴራ፣ ያሎ፣ሲልሳ ለሚገኙ የውስጥ ተፈናቃዮች እና በሰመራ ከተማ ላሉ ስደተኞች እህል እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጿል።

ባለፉት ቅርብ ሳምንታት በመላው WFP በአፋር ፦

➡️ በ14 ወረዳዎች ላሉ 520,000 ሰዎች የነፍስ አድን ምግብ አቅርቧል።

➡️ ለ80,000 እናቶች እና ህፃናት የወሳኝ ምግብ ድጋፍ አድርጓል።

በሌላ ከአፋር ጋር በተያያዘ መረጃ የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፥ በአፋር የተለያዩ ቦታዎች በዋነኝነት በበርሃሌ ፣ ኤሬብቲ፣ ኮነባ፣ አብዓላ ወረዳዎች እና በከልበቲ ዞኑ ሙሉ አሁንም ግጭቶች ስለመኖራቸው የከባድ መሳሪያ እና የአየር ጥቃቶች ፣ ስለመኖራቸው አመልክቷል።

በክልሉ ባለው ጦርነት እስካሁን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን አሁንም ተፈናቃዮች እየተመዘገቡ መሆኑና በዚህም ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቱ በእጅጉ መጨመሩን ገልጿል።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Situation_Report_Northern_Ethiopia_Humanitarian_Update_3_Mar_2022.pdf
#SituationReport

#Tigray #Amhara #Afar📍

የሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የተመድ ሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ የዚህን ሳምንት ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

ዋና ዋና ነጥቦች ፦

#Afar📍

- በአፋር ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል። በተለይም በራህሌ፣ ኢሬብቲ፣ ኬልቤቲ ዞን (ዞን 2) ውስጥ የትጥቅ ግጭቶች መኖራቸው ሪፖርት ተደርጓል።

- በአፋር እየተካሄደ ያለው ግጭት የሰብአዊ ድጋፍ መርሃ ግብሮችን እያደናቀፈ ፤ የሲቪሎችን ህይወት፣ ደህንነታቸውን አደጋ ላይ እየጣለ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም የሰብአዊ ፍላጎቶችን እየጨመረው ይገኛል።

- በአፋር ክልል ዞን 4 መረጋጋት በመፈጠሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመው ቀያቸው ተመልሰዋል።

- በዞን 2 በቀጠለው ግጭት ምክንያት ተጨማሪ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ ባለስልጣናት አሳውቀዋል። ተፈናቃዮቹ በተለይም ከአባላ፣ ኢረብቲ፣ በረሃሌ፣ መጋሌ እና ዳሎል ወረዳዎች መሆናቸው ተገልጿል። አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት በዳሎል፣ አፍዴራ፣ ሲልሳ/ጉያህ እና ሰመራ እየተጠለሉ ሲሆን አንዳንድ ተፈናቃዮች ደግሞ ራቅ ባሉ እና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ነው ያሉት።

- የተመድ አጋሮች በተደራሽነት ውስንነት ምክንያት በዞን 2 የሚገኙትን የተፈናቃዮች ቁጥር ማረጋገጥ አልቻሉም።

- ቁጥራቸው ያልተረጋገጠ ከአፋር የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች በትግራይ ክልል በሚገኙ ጥቂት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

#Tigray 📍

- አሁን ላይ የ ሰመራ - አብአላ - መቐለ መስመር መዘጋት ወደ ትግራይ የሚደርሰውን የሰብአዊ አቅርቦት የበለጠ አባብሶታል። ሰብዓዊ አቅርቦቱ ከታህሳስ አጋማሽ በፊት ከተፈቀደው ውስን አቅርቦት ጋር ተዳምሮ በዋነኛነት ቀደም ባሉት አስተዳደራዊ ርምጃዎች ምክንያት ሰብዓዊ አቅርቦቱ ከሚያስፈልገው በታች ነበር።

- እኤአ ከሃምሌ 12 ጀምሮ አስፈላጊውን የሰብአዊ አቅርቦት ከያዙ 16,500 የጭነት መኪናዎች ውስጥ 8 በመቶው ብቻ ትግራይ ገብተዋል። በዚህም የተመድ ሰብአዊ አጋሮች ተግባራቸውን መቀነሳቸውን ቀጥለዋል።

- ይህ ሪፖርት በተዘጋጀበት በዚህ ሳምንት የሰብአዊ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች 47 ሜትሪክ ቶን የህክምናና የስነ ምግብ አቅርቦቶችን ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቐለ በበረራ አድርሰዋል። ይህ እኤአ ከጥር 24 አንስቶ በበረራ ወደ ትግራይ የገባውን አጠቃላይ አቅርቦት 144 ሜትሪክ ቶን አድርሶታል።

- በዚህ ሳምንት ወደ ትግራይ ከቀረበው አቅርቦት መካከል 10 ሜትሪክ ቶን የተመጣጠነ ምግብ (Ready to Use Therapeutic Food - RUTF) ይገኝበታል። ይህም ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባ ሲሆን በመቐለ፣ በምስራቅ እና ደቡብ-ምስራቃዊ ዞን ይከፋፈላል። ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ለመንከባከብ ይውላል።

- ባለፉት ሳምንታት ወደ መቐለ የደረሱ የህክምና ቁሳቁሶች ይህ ሪፖርት በተዘጋጀበት ሳምንት ወደ ምስራቅ ዞን ውቅሮ እና ዓዲግራት አጠቃላይ ሆስፒታሎች፣ ወደ ማዕከላይ ዞን ዓድዋ፣ አክሱም፣ አቢአዲ ጠቅላላ ሆስፒታሎች እና አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ በሰሜን ምዕራብ ዞን ወደ ስሁል ሽሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ተከፋፍለዋል።

- አሁንም የነዳጅ እጥረት ቀሪዎቹን ቁሳቁሶች ለማከፋፈል እንቅፋት እንደሆነ ነው።

- በትግራይ አሁንም የህክምና ቁሳቁሶች ችግርና የተወሰኑ አይነት መድሃኒት እጥረቶች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል HIV ላለባቸው ሰዎች ሚሰጥ መድሃኒት ይጠቀሳል፣ የHIV መመርመሪያ ኪት፣ የፀረ ራቢስ መድሃኒት፣ የኮሌራ ክትባት እጥረትም አለ።

#Amhara 📍

- በአማራ ክልል አንዳንድ ' ከትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ' አሁንም ተደራሽ አይደሉም። በተለይም በሰሜን ጎንደር ፣ ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ያሉ አካባቢዎች እጅግ አሳሳቢ ሲሆኑ አልፎ አልፎ በሚከሰቱት ግጭቶች ምክንያት ሰዎች ወደ ዝቋላ ፣ ሰቆጣ ፣ ቆቦ እና ዛሪማ መፈናቀላቸውን የሚገልፁ ሪፖርቶች አሉ።

- በሰቆጣ እና ዝቋላ ከ40 ሺ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ይገመታል።

- በአማራ ክልል በዘጠኝ ዞኖች እኤአ ከታህሳስ እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ በ " Find -and - Treat " ዘመቻ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ህጻናትን የመለየት ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 21,804 ህጻናት ወይም 1.1 በመቶው ህጻናት በከፋ የምግብ እጥረት (SAM) ተጠቅተዋል።

- በምስራቅ አማራ እ.ኤ.አ. ከየካቲት 14 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው 'find and treat' ዘመቻ እስካሁን ምርመራ ከተደረገላቸው 293,208 ከ5 አመት በታች ህጻናት 8,160 SAM ኬዝ ወይም 2.7 በመቶና 48,118 GAM ኬዞች ወይም 16.4 በመቶ ተገኝቷል። ምርመራ ከተደረገላቸው 52,828 ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ውስጥ 21,687 ሴቶች ወይም 41 በመቶው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው ተብሏል።

#UNOCHA

@tikvahethiopia
#Tigray #Amhara #Afar #Oromia

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በትግራይ ፣ በአማራ ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች በጸጥታ ችግር እና በጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚቀርብ ሰብአዊ ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም የሚውል 134,884,285 ብር መርሃግብር አስጀምራለች።

ይኸው መርሃግብር ለ227,255 ዜጎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን በአፋጣኝ ለማድረስ የሚውል ሲሆን ከእነዚህም መካከል 9,690 ህፃናት 36,199 ተፈናቃዮች እና ተቀባይ ማህበረሰብ ይገኙበታል።

ፕሮጀክቱ የሚከናወነው በቤተክርስቲያኗ የልማት ኮሚሽን 4 ሀገረስብከቶች አማካኝነት በተጠቀሱት 4 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 7 ዞኖች እና 11 ወረዳዎች ነው።

ገንዘቡን ለማሰባሰብ ድጋፍ ያደረጉት የካሪታስ ዓለም አቀፍ አባል ድርጅቶች እና ሌሎች የቤተክርስቲያን አጋር ድርጅቶች መሆናቸው ተገልፆልናል።

@tikvahethiopia
#Afar

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመሆን ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ላይ ለተጠለሉ 9,000 ሰዎች የምግብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉ የስንዴ ዱቄት ፣ አተር ክክ ፣ የማዕድ ጨው እና የምግብ ዘይትን ያካተተ ነው፡፡

በሌላ በኩል ፤ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በአፋር ክልል ከ500,000 በላይ እንስሳትን ከአደገኛ በሽታዎች ለመከላከል የሚረዳ የክትባት ዘመቻ እያከናወነ ይገኛል፡፡

ይህም በግጭት የተጎዱ በክልሉ የሚገኙ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች መተዳደሪያ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ይረዳል ተብሏል።

#ICRC

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update 21 የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል " አብኣላ " መንገድ ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ዛሬ ከሰዓት አስታውቋል። ተሽከርካሪዎቹ የእህል እርዳታ የጫኑ ሲሆን በዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) አማካኝነት ነው በአፋር አብዓላ በኩል በየብስ ወደ ትግራይ እየሄዱ የሚገኙት። መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ ቁርጠኛ…
#Tigray #Afar #WFP

ወደ ትግራይ ጉዞ እንደጀመሩ የተገለፀላቸው የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባት መጀመራቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) አስታውቋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ኢሬብቲ ደርሰው ወደ ትግራይ ማቋረጥ መጀመራቸውን የገለጸው ድርጅቱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መቐለ ይገባሉ ብሏል፡፡

ከ500 ሜትሪክ ቶን በላይ የተመጣጠነ ምግብ በርሃብ አፋፍ ላይ ለሚገኙ የእርዳታው ፈላጊዎች ይከፋፈላል ተብሏል።

በተጨማሪ ፤ ከ1000 ሜትሪክ ቶን በላይ የተመጣጠነ ምግብ የጫኑ ሌሎች የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ዛሬ ከሰዓት ሰሜናዊ አፋር መድረሳቸውንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

የሰብዓዊ እርዳታው ፦
👉 ዳሎል፣
👉 በራህሌ
👉 ኮነባ አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚደርስ ገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲያልፉ የአፋር ክልላዊ መንግስት እና ህዝብ ትልቅ ድጋፍ እንዳደረገ ገልጿል።

መረጃው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የትዊተር ገፅ ነው።

ፎቶ ፦ ወደ ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው እየተጓዙ የነበሩት ተሽከርካሪዎች (ከአፋር ክልል ቲክቫህ አባላት)

@tikvahethiopia
#Afar

" በእሳት አደጋው 160 የሚጠጉ ሱቆች እና የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል። በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም " - ሰሙሮቢ ገልዐሊ ወረዳ

በአፋር ክልል ሰሙሮቢ ገልዐሊ ወረዳ በድንገት በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ በግምት ከ160 በላይ የሚጠጉ ሱቆች እና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን የወረዳው አስተዳድር አሳውቋል።

የሰሙሮቢ ገልዐሊ ወረዳ አስተዳድር አቶ ሀሰን ሀንዲ ለአፋር ብዙሀን መገናኛ በሰጡት ቃል ፤ " የእሳት ቃጠሎ አደጋው የደረሰው ወደ 10 : 00 ሰዓት አካባቢ በድንገት ከቢንዝል መሸጫ ቤት በተነሳ እሳት ነው " ብለዋል።

በድንገተኛው የእሳት አደጋ ምክንያት የደረሰው ውድመት ወደፊት የሚጣራ ሁኖ በግምት ግን ከ80 በላይ መኖሪያ ቤቶች እንደዚሁም ወደ 80 ሊጠጋ የሚችል የተለያዩ የንግድ ሱቆች ወድመዋል።

በእሳት አደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አሳውቀዋል።

በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ንፋስ መኖሩ እና የውሀ እጥረት በመኖሩ ቃጦሎው በፍጥነት በመባባሱ ምክንያትም እሳቱን ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ከፍተኛ ውድመት መከሰቱን አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

ለተጎጂዎቹ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

በብዛት የቢንዚል ሽያጭ ከሚከናወንበት ቦታም በቀላሉ የእሳት አደጋ እየተፈጠረ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቂ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

መረጃው የአፋር ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ነው።

@tikvahethiopia
#Afar

ህወሓት ኃይሎቹን ከአፋር ክልል፤ " ኤሬብቲ " ማስወጣቱን በመግለፅ መግለጫ አውጥቷል።

ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ኃይሎቹን ከአፋር ክልል ኤሬብቲ ያስወጣው ሰብዓዊ እርዳታ የማድረስ ስራን ለማገዝን ነው ብሏል።

የሰብዓዊ እርዳታ ወደክልሉ እንዲገባና ችግር ላይ ላሉ ዜጎች እንዲደረስ ከዚህ ቀደም ለሰብዓዊነት ተብሎ የተደረሰው ስምምነት ለማክበር ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል።

ኃይሎቹን ከኤሬብቲ ማስወጣቱን የገለፀው ህወሓት በሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ አፋጣኝ ለውጥ እንደሚጠብቅ ገልጿል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስና ሁሉም አስፈላጊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በህወሓት በኩል የወጣውን መግለጫ "የተሳሳተ" ብሎታል።

ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ለዶቼ ቨለ በሰጡት ቃል፤ አሁንም አፋር ውስጥ ወረዳዎችን እንደያዙ ነው ብለዋል።

አቶ ከበደ፥ "እንደዚህ አይነት ነገር ሰማን (ወጡ የሚል) ትርጉም ያለው መልቀቅ አይደለም፤ የተያዙ ቦታዎች አሉ ለቀቁ የሚል እምነት የለንም በኛ በኩል። ሰብዓዊ እርዳታው በአግባቡ እንዲደርስ በሚል ነው መንግስት ያለ ቅድመ ሁኔታ ስለፈቀደ ነው እንጂ አልተለቀቁም" ብለዋል።

ከዚህ ቀደ። የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታው እንዲሳለጥ የህወሓት ኃይል ከአፋር ክልል ለቆ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን 2 በኃይል ይዘዋቸዋል ካላቸው ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲና በራህሌ ይገኙባቸዋል።

ለሰብዓዊት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ከታወጀ በኃላ እስካሁን በአፋር በኩል ወደትግራይ የገባው 26 ተሽከርካሪ ነው።

@tikvahethiopia
#ICRC #Oromia #Afar

ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን፣ ኩምቢ ለሚገኙ 5000 አባወራዎች የእንስሳት መኖ እያከፋፈለ ይገኛል።

ስርጭቱ በአካባቢው ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ሲሆን በዚህ ኦፕሬሽን እስከ 150,000 እንስሳት ይመገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ድርጅቱ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ ፤ ባሳለፍነው ሳምንት በአፋር ክልል ሲልሳ ለሚገኙ 9,000 የተፈናቀሉ ሰዎች መሰረታዊ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ማለትም ሶላር የእጅ ባትሪዎችን፣ ጀሪካኖችን፣ የማዕድ ቤት እቃዎችን፣ ምንጣፍ እና መጠለያ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

@tikvahethiopia
#Somali #Afar

በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል 2ቱ ክልሎች ከስምምነት መድረሳቸውን አስታወቁ።

ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል የተባለው መሠረታዊ ስምምነት የታጠቁ ኃይሎች ከግጭት አካባቢዎች እንዲወጡ እና የፌደራል ፀጥታ ኃይሎች ወደነዚህ ቦታዎች እንዲገቡ የሚፈቅድ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን መናገራቸውን የጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ ዘግቧል።

በአዋሳኝ ቀበሌዎች በየቦታው ተኩስ ፣ ስርቆት እና መፈናቀል ይከሰቱ እንደነበር የተናገሩት አቶ ኢብራሂም ዘላቂ ሰላም ለማምጣትም የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀያቸው መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኢብራሂም « ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ችግር እንዳይከሰት፣… ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲመጣ እና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሚና መሆን እንዳለበትም ነው ትናንት ከስምምነት ላይ የደረስነው።» ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን ማሣረጊያ እንዲሆን የሁለቱ ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንፈረንስ እንደሚያካሂዱም ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ በተካሄደው ውይይት የሰላም ሚንስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ጨምሮ የአፋር እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተው እንደነበር ሬድዮ ጣቢያው ዘግቧል።

@tikvahethiopia