#Afar

ህወሓት ኃይሎቹን ከአፋር ክልል፤ " ኤሬብቲ " ማስወጣቱን በመግለፅ መግለጫ አውጥቷል።

ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ኃይሎቹን ከአፋር ክልል ኤሬብቲ ያስወጣው ሰብዓዊ እርዳታ የማድረስ ስራን ለማገዝን ነው ብሏል።

የሰብዓዊ እርዳታ ወደክልሉ እንዲገባና ችግር ላይ ላሉ ዜጎች እንዲደረስ ከዚህ ቀደም ለሰብዓዊነት ተብሎ የተደረሰው ስምምነት ለማክበር ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል።

ኃይሎቹን ከኤሬብቲ ማስወጣቱን የገለፀው ህወሓት በሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ላይ አፋጣኝ ለውጥ እንደሚጠብቅ ገልጿል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስና ሁሉም አስፈላጊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በህወሓት በኩል የወጣውን መግለጫ "የተሳሳተ" ብሎታል።

ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ለዶቼ ቨለ በሰጡት ቃል፤ አሁንም አፋር ውስጥ ወረዳዎችን እንደያዙ ነው ብለዋል።

አቶ ከበደ፥ "እንደዚህ አይነት ነገር ሰማን (ወጡ የሚል) ትርጉም ያለው መልቀቅ አይደለም፤ የተያዙ ቦታዎች አሉ ለቀቁ የሚል እምነት የለንም በኛ በኩል። ሰብዓዊ እርዳታው በአግባቡ እንዲደርስ በሚል ነው መንግስት ያለ ቅድመ ሁኔታ ስለፈቀደ ነው እንጂ አልተለቀቁም" ብለዋል።

ከዚህ ቀደ። የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታው እንዲሳለጥ የህወሓት ኃይል ከአፋር ክልል ለቆ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን 2 በኃይል ይዘዋቸዋል ካላቸው ወረዳዎች መካከል አብአላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲና በራህሌ ይገኙባቸዋል።

ለሰብዓዊት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ከታወጀ በኃላ እስካሁን በአፋር በኩል ወደትግራይ የገባው 26 ተሽከርካሪ ነው።

@tikvahethiopia