#Ethiopia #US

አሜሪካ ከ #አማራ_ፋኖ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግር እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደጠየቀች አሳውቃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ እንዲሁም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሃመር በኦንላይን መግለጫ ሰጥተው ነበር።

መግለጫቸው ባለፉት ቀናት በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ቆይታ የተመለከተ ነበር። 

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠ/ ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ጨምሮ ከተለያዩ ባለስልጣናትና የተቋማት መሪዎች ጋር በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች #በውይይት እንዲፈቱ መነጋገራቸውን አሳውቀዋል።

አሜሪካ በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው ግጭት እልባት እንዲያገኝ የበኩሏን ሚና እየተጫወተች መሆኑን ገልጸው በአማራ ክልልም ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ ከፋኖ ጋር ንግግር እንዲጀመር ጥሪ መቅርቡን ተናግረዋል።

አምባሳደር ማይክ ሃመር ምን አሉ ?

" ባለፈው ሕዳር ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በዳሬሰላም በተደረገው ውይይት ላይ በቀጥታ ተሳትፈናል። አሁን ይህን ለመቀጠል ዝግጁ ነን። ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ እንዴት መመቻቸት እንደሚቻል ለሁለቱም አካላት ሃሳብ አቅርበናል።

ከፋኖ ጋር ንግግር እንዲደረግ አምባሳደር ማሲንጋ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን እናውቃለን።

ሰላምን ለማረጋገጥ ያሉትን እድሎች በመጠቀም ጥረታችንን ለመቀጠል ዝግጁ ነን። በተደጋጋሚ እንዳልነው ለነዚህ ግጭቶች ወታደራዊ መፍትሄ አማራጭ አይሆንም አሁንም ትኩረት መደረግ ያለበት ውይይት ላይ ነው። " ብለዋል።

ሞሊ ፊ ምን አሉ ?

" ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያጋጠሟትን ፈተናዎች በሰላም ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ቁርጠንኝነታቸው እንዲቀጥሉ እናበረታታለን።

በታጣቂዎች ለሚፈፀሙት ጥቃቶች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ስለሚወስዱት እርምጃ አሳሳቢነት ገልጸናል። የጸጥታው ሁኔታን አሳሳቢነት ብንረዳም የሲቪሎችን መብት ለመጠበቅ ተጨማሪ ጥሪ ያስፈልጋል " ብለዋል።

አምባሳደር ማይክ ሃመር ፤ " ከተለያዩ ባለስልጣናት ጋር በተደረገው ስብሰባ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ውይይት ለማመቻቸት እንዲሁም የቀጠሉትን ግጭቶች በሰላም ለመፍታት ከአማራ ፋኖ ጋር ሊደረግ የሚችል ንግግር ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለን ገልጸናል " ብለዋል።

ሃመር በኢትዮጵያ ላለው ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለ ገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥትም ለሰላማዊ መፍትሄ ዝግጁነት እንዳለው መግለፁን እናደንቃለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ፅኑ አቋም እንዳለው መግለፁ ይታወቃል። ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋርም በይፋ ሁለት ጊዜ ድርድር ቢቀመጥም መጨረሻ ላይ መሳካት አልቻለም። በአማራ በኩል ከፋኖ ጋር ለድርድር ስለመቀመጥ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

አሜሪካውያኑ ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ሳይሳካ ቀርቶ የተቋረጠው ድርድር መቼ እንደሚቀጥል እንዲሁም መንግሥት ከፋኖ ጋር ለድርድር ይቀመጥ እንደሆነ በግልፅ ባይናገሩም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሄ ዝግጁ እንደሆነ እንዳሳወቃቸው ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃው የቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ / ጋዜጠና ኬኔዲ አባተ መሆኑን ያሳውቃል።

@tikvahethiopia