TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት ደራርቱ ቱሉ ፤ አትሌት ጥላሁን ኃይሌን ይቅርታ ጠየቀች።

ደራርቱ ፤ " ጥላሁን ስላዘንክ ፤ ስለተበሳጨህ በጣም ይቅርታ " ያለች ሲሆን " ይቅርታ የምለው በጣም ስላለቀሰ ስላዘነ ነው ፤ ነገር ግን መብቱን አልነካንም ፤ እሱን አስወጥተን ማንንም አላስገባብም። ሁሉም ባላቸው ሰዓት እና በብቃታቸው ነው የገቡት " ብላለች።

ደራርቱ እንደ አመራር እና እንደ እናት በተፈጠረው ነገር አዝኛለሁ ፤ ይቅርታም እላለሁ ስትል ተናግራለች።

" የአትሌቱን መብት ነክተን አላስቀረነውም 4ኛ በመሆኑ ብቻ ነው ያስቀረነው " ስትልም አክላለች።

ውሳኔዎች ሲተላለፉ በኮሚቴ ተነጋግረን ለሀገር የሚበጀውን ነው ያለችው ደራርቱ እኔ ብቻዬን ማንም የማስገባትም ሆነ የማስወጣት መብት የለኝም ብላለች።

አትሌት ጥላሁን ኃይሌ በ5000 ሜትር ውድድር ተመርጦ ወደ ሀንጋሪ ከተጓዘ በኃላ ፤ ትላንት በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ እና በሱ ምትክ በሪሁ አረጋዊ መካተቱን ሊያውቅ ችሏል።

በዚህም እጅግ ሀዘን ውስጥ የገባ ሲሆን " የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት ደራርቱ የሰራችብኝን ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ " ብሏል።

" የሀገሬን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረድ ስለፋ ስደክም ቆይቼ የተሻለ ብቃት ኖሮኝ ፌዴሬሽኑ በሰራብኝ ግፍ ተቀንሻለሁ " ያለ ሲሆን " አሰልጣኝ ሁሴን ሽቦ ነው ፌዴሬሽኑን እየመራ ያለው ማለት ይቻላል ልጄ ይሮጥልኛል ብሎ በሪሁ አራተኛ ወጥቶ ገብቶ እንዲወዳደር ተደርጓል " ሲል ቅሬታው አቅርቧል።

" ቀን እና ማታ በአጥንት እስክቀር ድረስ የለፋሁበት እንጀራዬን እንዲህ መደረጉን ህዝቡ ይወቅልኝ ፤ ፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚሰራውን ግፍ ህዝብ ይወቅልኝ " ብሏል።

" ፌዴሬሽኑን የሚመሩት አትሌት የነበሩ ናቸው እነሱ ሲመጡት ውስጥ ያለው አሰራር ይሻሻላል ቢባልም ጭራሽ በነሱ ባሰ፤ ስም አለም ሚዲያውን እንቆጣጠራለን ታዋቂ ነን ፤ ህዝቡን ማሳመን እንችላለን ብለው ይሄን ሁሉ ግፍ የሚያደርጉት እነሱ ናቸው " ሲል አክሏል።

ይህን የአትሌቱን ቅሬታ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የፌዴሬሽን አመራሮች ምርጫው ብቃትን መሰረት ያደረገ ሀገርንም ይጠቅማል በሚል እንጂ ማንንም አስወጥቶ የማስገባት ጉዳይ አይደለም፤ በሪሁ የተሻለ ሰዓት ስላለው ብቃቱም ጥሩ ስለሆነ ነው የገባው ብለዋል።

አትሌት ጥላሁን ኃይሌ የማይወዳደር ከሆነ ለምን እንዲሄድ እንደተደረገ ሲገልፁም ፤ ምናልባት በሪሁ የሆነ ነገር ቢሆን የሱ መኖር አስፈላጊ ነው ፤ ተጠባባቂ አትሌት ሁኔም ይኖራል ይህ ድሮም የነበረ አሰራር ነው ሲሉ አስረድተዋል።

@tikvahethiopia