" ሱተን ዙሪያ ቀበሌ ድረስ ተከታትለው በመምጣት ነው የገደሉት ፤ ... ይሄን ለማን አቤት ልበል ? " - ወላጅ አባት

በኦሮሚያ ክልል፤ ደ/ምዕራብ ሸዋ ዞን  የትራፊክ ፖሊስ አባላት የጠየቁትን ያህል ጉቦ አልሰጥም ያለን አንድ አሽከርካሪ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን የሟች ቤተሰቦችና የሥራ ባልደረቦች መግለፃቸውን ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዘግቧል።

ድርጊቱ የተፈፀመው ባለፈው ዓርብ ዕለት ሲሆን በትራፊክ ፖሊስ አባላቱ በጥይት የተገደለው እና ትላንት ስርዓተ ቀብሩ ተፈፀመ የተባለው የ33 ዓመት እድሜ ያለው ሳሙኤል መረተ ነው።

ሳሙኤል መረት ነዋሪነቱ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡

ጓደኞቹ እንዳሉት ሳሙኤል ከረጅም ጊዜ አንስተቶ የአሽከርካሪነት ሥራውን ሲያከናውን የቆየው ከአዲስ አበባ ቡታጅራ በተዘረጋው መስመር ላይ ነበር።

በመስመሩ በሰበብ አስባቡ ካልቀጣንህ የሚሉትን የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለማባበል ዝርዝር የ " ሃምሳ ብር " ኖቶችን በእጃቸው እያስጨበጠ ማለፍ የሁልጊዜ ተግባሩ እንደነበር  ጓደኞቹ ይናገራሉ።

ይህ የሃምሳ ብር ጣጣ ታዲያ  " አንሷል ጨምር አልጨምርም " በሚል ከትራፊክ ፖሊስ አባላት ጋር የገባበት እሰጥ አገባ ለህይወቱ መጥፋት ምክንያት መሆኑን ነው በሥፍራው ነበርን ያሉ ገልጸዋል።

የሳሙኤል ረዳት ምን አለ ?

የሳሙኤል መረተ ረዳት ሆኜ ሥሠራ ነበር የሚለው አንዱዓለም ሁሴን ፦

" መንገደኞችን አሳፍረን ከአዲስ አበባ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ እያለን በኦሮሚያ ክልል ፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ስንደርስ ሦስት ትራፊኮች ያስቆሙናል።

ሳሙኤል የመውጫ ወረቀት እና ሃምሳ ብር ሲሰጥ ከትራፊኮቹ አንዱ ሀምሳውን ቀይረህ መቶ አድርግ ሲለው ሰምቻለሁ።

ሳሙኤል አሁን የለኝም አልተዘጋጀሁም ሲለው ትራፊኩ አለበለዚያ የተሸከርካሪውን ሠሌዳ እፈታለሁ በማለት በቦክስ መታው፡፡

ይሄኔ በንዴት ተሽከርካሪውን አስነስተን ወደፊት መሄድ ስንጀምር ተከትለው መተኮስ ጀመሩ፡፡

ጥቂት እንደተጓዝን ተሸከርካሪውን በማቆም እኔም ሆንኩ ሌሎች መንገደኞች ደንግጠን ወረደን መሮጥ ጀመርን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እሱን በጥይት መትተው ጣሉት " ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

የሟች ሳሙኤል አባት አቶ መረተ ለማ በበኩላቸው ፤ ከትራፊክ ፖሊስ አባላቱ ጋር አለመግባባቱ የተነሳው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ቢሆንም ግድያው የተፈጸመው ግን በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ሱተን ዙሪያ ቀበሌ ድረስ ተከታትለው በመምጣት  አንደሆነ ገልጸዋል።

" ይህን ለማን አቤት ልበል ? " ሲሉም ጠይቀዋል ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደ/ምዕራብ ሸዋ ዞን የተሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ፈይሳ ደበላን ጉዳዩን በተመለከተ ከሬድዮ ጣቢያው ተጠይቀው ፤ ወንጀሉ የተፈጸመው እሳቸው ከሚመሩበት የተሬ ወረዳ አልፎ ጉራጌ ዞን ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ " በዚህ ላይ እኔ የምለው ነገር የለም ፤ ባይሆን የደቡብ ክልል ፖሊስን ጠይቁ " ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ ፤ የወንጀሉ አድራሾች በኦሮሚያ ክልል ፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ ድርጊቱን በመፈጸም የተጠረጠሩ ሦስት የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

" የተከሰተው ነገር አሳዛኝ ነው " ያሉት ኮማንደር ጠጄ " የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ወዲያው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ አሁን ምርመራውን ከኦሮሚያ ክልል የሥራ ሃላፊዎች ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን ፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በጉራጌ ዞን ውስጥ በመሆኑ ምርመራውን ወደ ዞኑ ለማዛወር በሂደት ላይ ነው ያለነው " ብለዋል፡፡

#ዶቼቨለ

@tikvahethiopia