#ችሎት

6 ሺህ 1 መቶ ብር የወራዊ ደሞዝ ተከፋይ ለነበረ የመንግስት ሠራተኛ በተጭበረበረ መንገድ 69 ሺህ 1መቶ ብር እንዲከፈለው ያደረጉ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ።

የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቃቤ ህግ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም የቀረበለት ክስ መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል።

የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ የሙስና ወንጀል ህጎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 አንድ ሐ ላይ የተመለከተውን ተላልፈው በተገኙ 3 ግለሰቦች ላይ ነው።

• 1ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ሻሜቦ በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት የሂሳብ ባለሙያ ፤

• 2ኛ ማርቆስ ሄራሞ ተከሳሽ በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት የክፍያ ክፍልና የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ቡድን መሪ፤

• 3ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ታዬ አለሙ በምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት መምህር፤

ለ3ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ታዬ ሊከፈል የሚገባው እና ያልተጣራ ወራዊ ደምወዝ ጣሪያ 6 ሺህ 1መቶ 46 ብር ሆኖ በዚህ ደምወዝ የተጣራ በእጁ ላይ መድረስ የነበረበት 4 ሺህ 7መቶ 12 ብር ከ32 ሳንቲም መሆን ነበረበት።

1ኛ ተከሳሽ ለወረዳው ፋይናንስ ከተሰጠው የክፍያ ትዕዛዝ ውጭ ያለ አግባብ ያልተጣራ የወር ደምወዝ ጣሪያ 69 ሺህ 1መቶ 46 ብር በእጁ የሚደርስ የተጣራ ገንዘብ ደምወዝ መጠን 41ሺህ 6መቶ አራት ብር ከ68 ሳንቲም የሚያገኝ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ የደምወዝ ፔሮል አዘጋጅቷል።

2ኛ ተከሳሽ በበኩሉ የተዘጋጀውን የደምወዝ ፔሮል አጽድቆ ወጪ እንዲሆን አዟል።

3ኛ ተከሳሽ ሊከፈለው የማይገባውን ገንዘብ በልዩነት 36 ሺህ 8 መቶ 92 ብር ከ36 ሳንቲ ለ1 ወር ከምዕራብ ባደዋቾ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ሂሳብ ቁጥር ተቀናሽ ተደርጎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግለሰቡ የሂሳብ ቁጥር ገቢ ተደርጓል።

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት በማድረስ ለራሳቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በፈጸሙት የመንግሥት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።

የክሱን ሂደት ሲመረምር የቆየው የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 12/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች በምክንያትነት ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ እና ገንዘቡ ለመንግሥት ተመላሽ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ውሳኔ ሰጥቷል።

በዚህ መሠረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው 2 ዓመት እና የ3 ሺህ ብር መቀጮ እንዲሁም 3ኛው ተከሳሽ 1 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

ምንጭ፦ የሃዲያ ዞን ኮሚኒኬሽን

@tikvahethiopia