#UNESCO #WHO

" ... ድርጅቶቹ ያለአድሎ ኃላፊነታቸውን ሊወጡና የህወሃት ቡድን የፈጸመውን ውድመት በይፋ ማውገዝ ይጠበቅባቸው ነበር " - አቶ ዮሴፍ ካሳዬ

ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ካሳዬ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተጠሪ ከሆኑት ዶ/ር ዮሚኮ ዮኮዝኪ እና የዓለም ጤና ድርጅት ተጠሪ ዶ/ር በርማ ኤች. ሳምቦ ጋር ተወያይተዋል።

በወቅቱም አቶ ዮሴፍ ፥ የህወሓት የሽብር ቡድን የትግራይ ክልልን ጨምሮ በአፋር እና አማራ ክልሎች የባህላዊ ቅርሶች እና የጤና መሰረተ ልማቶች ላይ የፈጸመውን ውድመት ለማውገዝ ድርጅቶቹ ቸልተኝነት ማሳየታቸው ገልጸውላቸዋል።

አቶ ዮሴፍ ፥ " ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ንብረቶች ላይ የደረሰው ውድመት እና የንብረት ዘረፋ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው " ያሉ ሲሆን " የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በቸልታ ማለፉ ህወሃት በተግባሩ እንዲገፋበት አበረታቶታል " ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ተመድ መስራች አባልነቷ ከሁሉም የተመድ ድርጅቶች ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላት አንስተው፣ ድርጅቶቹም ያለአድሎ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና የህወሃት ቡድን የፈጸመውን ውድመት በይፋ ማውገዝ ይጠበቅባቸው እንደነበረ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ በበኩላቸው ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት ምስጋናቸውን ገልፀው፣ ያላቸውን ኃላፊነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የኢትዮጵያን ጉዳይ በአንክሮ ለመመልከት ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

@tikvahethiopia