TIKVAH-ETHIOPIA
" ... ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስገልገዋል " - የአማራ ክልል መንግስት የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስታና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ፥ በክልሉ ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው ዞኖች ማለትም ፦ - ሰሜን ወሎ - ደቡብ ወሎ - ከፊል ደቡብ ጎንደር - ዋግኽምራ ውስጥ የሚኖሩ እና ተፈናቅለው ያሉትን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል…
"... እስከ ትናንት ድረስ በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን 218 ሺህ 955 ዜጎች መጥተዋል " - አቶ አበባው መሰለ

ከ1 ሳምንት በፊት ከዋግህምራ እና ሰሜን ወሎ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደሴ እና አካባቢዋ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ጦርነቱን ሸሽተው በድጋሚ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን መፈናቀላቸው ተሰምቷል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኀላፊ አቶ አበባው መሰለ ለአል ዐይን የዜና ማሰራጫ በሰጡት ቃል ፤ እስከ ትናንት ድረስ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው 218 ሺህ 955 ዜጎች ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ወደ ዞኑ የገቡ ተፈናቃዮችን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አበባው ፤ 12 ጊዜያዊ መጠለያዎችን በማዘጋጀት ለተፈናቃዮች ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን አሳውቀዋል።

በተፈናቃዮች ስምም ሌሎች አካላት ሰርገው እንዳይገቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አቶ አበባው ተናግረዋል።

በጦርነቱ የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የተናገሩት ኃላፊው የክልሉ መንግስትና የፌደራል መንግስት ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸውን አል ዓይን ዘግቧል።

ህወሓት አማራ ክልል ላይ በከፈተው ጦርነት ከ991 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ደግሞ ከ5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው እነዚህ ነዋሪዎች ለምግብ እጦት ፣ የመጠጥ ውሃ እና የመድሃኒት እጦት ችግር መጋለጣቸው ከቀናት በፊት የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስታና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ማሳወቁ አይዘነጋም።

@tikvahethiopia