TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የተማሪና የወላጆች ስጋት-የተቋማት መልስ⬇️

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣት ብቻ ሳይሆን የት ዩኒቨርሲቲ ይደርሰኝ ይሆን? የት ይመደቡ ይሆን? የሚለው የተማሪዎችም የወላጆችም ስጋት ከሆነ ቆይቷል።

በአዲስ አበባ የሚኖረው በቃሉ ሰንዳፋ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥቶ፤ ምደባ እየተጠባበቀ ይገኛል።

እንደ አዲስ ተማሪነቱ ቀደም ብለው ሲማሩ ከነበሩ ጓደኞቹ ጋር ስለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ ሃሳብ ተለዋውጧል።

ከእነርሱ የሰማውና ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ያሉ አጋጣሚዎች እርሱን ብቻ ሳይሆን ወላጆቹንም በተለይ እናቱን #ስጋት ውስጥ እንደጨመረ ይናገራል።

"ብጥብጥ ነበረባቸው የሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ብመደብ የምፈራ ይመስለኛል" ይላል።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ልጅ ያለቸው አባት በበኩላቸው "ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን አይተናል፤ ብዙዎች ለመማር ሄደው ሞተዋል። ይህ ችግር አሁንም እየቀጠለ ነው። በዚህ ሁኔታ ልጆቻችን የኛን ተስፋ እንዲሞሉ ብለን ሬሳቸውን መቀበል አንፈልግም፤ ለመላክም ፍቃደኛ አይደለሁም" ሲሉ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደተገደዱ ይናገራሉ።

ያነጋገርናቸው ተማሪዎችና ወላጆች ከተናገሩት በተጨማሪ በቅርቡ በመቀሌ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በአገሪቱ በሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሄዶ ለመማር ደህንነት አይሰማንም ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቃቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።

ይህ ስሜት በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የሚገኙ ተማሪዎችና ወላጆችም ይጋሩታል።

#ብሔርን መሰረት ያደረጉ ናቸው የተባሉ ጥቃቶች በተለያዩ አካባቢዎች መሰማታቸውም #ጭንቀታቸው እንዲባባስ አድርጎታል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ የሚያስተምሩት አቶ ሰለሞን ዮሐንስ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው አጋጥመው የነበሩ ብሔርን መሰረት ያደረጉ እንግልቶችን ጠቅሰው "የአሁኑ ደግሞ የባሰ ነው፤ እንኳን ብዙ ርቀት ለመላክ ይቅርና እዚህም ሆነን እየሰጋን ነው፤ እርሷ መመረቅ ብትፈልግም እኔ ግን ጨክኜ ለመላክ አልወሰንኩም" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አብዱልዋሴ ሁሴን በየዓመቱ ሁሉንም በሚፈለገውና በተሳካ ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስችል አደረጃጀት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ዘንድሮም በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ በመግለፅ "ወደዚህ የሚመጣ ተማሪ የኛም ልጅ ነው፤ ከምንም በላይ ደግሞ የሰላሙ ዘብ ተማሪው ራሱ ስለሆነ ምንም ዓይነት ስጋት ሊገባቸው አይገባም" ብለዋል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪም "ደህና ናቸው የሚባሉ አካባቢዎችም ወደ ረብሻና ግርግር እየገቡ ነው፤ ባለፉት ዓመታት የነበረው አገራዊ ሁኔታ ሊቀየር ስላልቻለ፤ ወደ ሌላ ክልል መሄድ ያሰጋኛል" ሲል ይናገራል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ይዳኝ ማንደፍሮ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመቀበል በተለያየ ዘርፍ በቂ ዝግጅት አድርጓል ይላሉ።

"ተማሪዎቹ ገና ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ ጀምሮ ህግና ደንቡ ስለሚነገራቸውና ትምህርት ስለሚሰጣቸው ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ችግር ገጥሞን አያውቅም። ዩኒቨርሲቲው አምስት ግቢ ሲኖረው በቂና አስተማማኝ ፀጥታ አላቸው፤ ምንም ስጋት ሊገባቸው አይገባም" ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚህ ቀደም ከሌላ ቦታ ወደ ዩኒቨርሲቲው መጥተው የሚማሩ ተማሪዎች የሚያሰጋቸው የደህንነት ጉዳይ አልነበረም የሚሉት በዲላ
ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሔኖክ ንጉሴ ናቸው።

አሁንም ከየትኛውም አካባቢ የሚመጣ ተማሪ ደህንነት እንዲሰማው የተማሪዎች አደረጃጀቶችና የዩኒቨርሲቲው አካላት የቅርብ ክትትል እንዲቀጥል ተማሪዎች ከመግባታቸው አስቀድሞ እየሰሩ እንደሚገኙ ዳሬክተሩ ገልፀዋል።

"ክልሉ የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚኖርበት ነው፤ ድሮም ከሁሉም አካባቢ መጥተው ይማራሉ፤ አሁንም ለየት ያለ ዝግጅት የሚያስፈልገው አይደለም" የሚሉት ደግሞ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ዱንኳና ንጉሴ ናቸው።
"የፀጥታ ስጋት የለም፤ በግቢው ውስጥም በቂ የሆነ ክትትልና ጥበቃ ይደረግላቸዋል" ብለዋል።

የተማሪዎችንና ወላጆችን ስጋት አንስተን ያነጋገርናቸው በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሳሙዔል ክፍሌ ያለፉት ዓመታት ተመሪዎችን ብቻ ሳይሆን ወላጆችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሰጋ እንደነበር ያወሳሉ። ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውን አልካዱም።

"በዚህ ዓመት የተሻለ ሁኔታ እየተፈጠረ ስለሆነ ስጋት ላይ የሚጥል ነገር የለም። መንግሥትና የፀጥታ ኃይሉ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ጥሩ አቅም ላይ ይገኛል" ይላሉ ዶክተር ሳሙዔል።

አንድ አገር እስካለን ድረስ በተወለድንበት ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ካልሆነ መማር አንችልም የሚለው ጥያቄ ግን ተቀባይነት እንደሌለው አስረግጠው ተናግረዋል።

ማንኛውም ዜጋ በአገሪቱ ባሉ አካባቢዎች የመማር ብቻ ሳይሆን የመኖርና የመስራት ህገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው የገለፁት ኃላፊው "እንደ አገር ሰላም ከሌለ፤ በክልላችን ብቻ ስለተመደብን ሰላም እንሆናለን ብሎ ማሰብ ስህተት ነው" በማለት ሃሳቡን ተቃውመውታል።

በመሆኑም ተማሪዎቹ በተመደቡበት ቦታና እጣ መሰረት መሄድ አለባቸው፤ ለደህንነት በሚል ሰበብ በክልላቸው የሚመደቡበት ሥርዓትም አይኖርም፤ መፍትሔም አይሆንም ብለዋል።

በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ሌሎች ነዋሪዎችም በመሆናቸው የሚበጀው የሁሉንም ሰላም ማረጋገጥ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲ መምህራንና አመራሮች በፍኖተ ካርታው ላይ የሚያደርጉት ውይይት እንደተጠናቀቀ እንደ የራሳቸው ዝግጁነት ተማሪዎችን ለመቀበል ከመስከረም 28 በኋላ ጥሪ ማድረግ እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

ዶክተር ሳሙዔል ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩት ችግሮች በትምህርት ዘርፉ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በዲፕሎማሲው፣ በልማቱ ዘርፍ፣ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በአገር ገፅታ ላይ ኪሳራ ማሳደራቸውን አስታውሰዋል።

©BBC
@tsegabwolde @tikvahethiopia