TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ስምምነት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠመውን ፈተና ለመፍታት የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ፦

1. በኦሮሚያ ክልል በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት፤ ቅዳሴ እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ እንዲጠናከር። ለዚህም ከዚህ በፊት ከተደረገው በተጨማሪ አስፈላጊው በጀትና የሰው ኃይል እንዲመደብ።

2. በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች የተዳከሙ አብያተ ክርስቲያናት ቋንቋውን በሚያውቁ አገልጋዮችና በአገልግሎት እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ዕቅድ ተዘጋጅቶ ከበፊቱ በበለጠ ተገቢው በጀትና የሰው ኃይል እንዲመደብ።

3. በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚያገለግሉ ቋንቋውን የሚያውቁ አገልጋዮችን የሚያሠለጥኑ ተጨማሪ ኮሌጆች እና ማሠልጠኛዎች እንዲከፈቱ፣ የተከፈቱትም እንዲጠናከሩ እንዲደረግ።

4. ለኦሮሚያ አህጉረ ስብከት በቂ የሆነ የኦሮምኛ ቋንቋን የሚያውቁና በቋንቋው የሚያገለግሉ ኤጲስቆጶሳት በቀጣይ የግንቦት ርክበ ካህናት ተወስኖ እንዲሾሙ፡፡

5. ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ቀደመ ሀገረ ስብክታቸውና የክነት ማዕረጋቸው እንዲመለሱ።

6. በሦስቱ አባቶች የተሾሙት አባቶች ቀድሞ ወደነበሩበት የክነት ማዕረግ ይመለሳሉ፡፡ ከእነርሱ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ተመዝነው የሚያሟሉት እንደገና በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሾሙ ይደረጋል።

7. በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፋይናንስ ፣ በምደባ፣ በቅጥር የሚታዩ ክፍተቶችን በጥናት የወንጌል አገልግሎትን በሚያጠናክር መልኩ እናሻሽላለን።

8. የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከርና ለትውልድ አርአያ የሚሆን ቤተ ክህነት እንዲኖረን ለማድረግ አሠራራችንን በጥናት አሻሽለን ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ እናሻግራለን፡፡

9. ጥላቻን የሚያባብሱ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይገባል። ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መምህራን እና አባቶች ፍቅርን ከሚያጠፋ፣ ጥላቻን ከሚያበዛና መለያየትን ከሚያሰፋ ነገር ሁሉ እንዲቆጠቡ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን። ይሄንን ተግባር ሆን ብለው የሚያደርጉትንም እናወግዛለን።

10. የገጠመን ፈተና ይበልጥ ውስጣችንን ለመፈተሽ፤ አንድነታችንን ለማጠናከር፤ ወንጌልን የበለጠ ለመስበክና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስፋፋት ለበጎ እንጠቀምበታለን።

በመጨረሻም #ፍቅር#ይቅርታ እና #አንድነት እንዲመጣ የደከማችሁትን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ስም እናመስግናለን። ዋጋችሁንም እግዚአብሔር እንዲከፍላችሁ እንጸልያለን።

@tikvahethiopia