TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Amhara

ኢሰመኮ፦

- ከየካቲት 15 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ/ም በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ (ዝቋላ ወገም፣ ፈረስ ቤት01፣ ገሳግስና ጉድባ ሰቀላ ቀበሌዎች) እና ሰከላ (አጉት፣ ጉንድልና አምቢሲ ቀበሌዎች እና ግሼ ዓባይ ከተማ) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ አካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል።

- የካቲት 20/2016 በሰሜን ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ቀበሌ በሚገኘው የጋፊት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የአብነት ተማሪዎች የዕለቱን ትምህርትና ጉባኤ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ አጠናቀው ወደ ማደሪያ ጎጇቸው ከገቡ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አባላት ከሌሊቱ 6፡30 ሰዓት ገደማ ላይ ወደ ቦታው ደርሰው ተማሪዎችን “ #ውጡ ” እያሉ ተኩስ በመክፈት ቀድመው በወጡ #በ11_ተማሪዎች ላይ ግድያ እንደፈጸሙ፤ ሌሎች 8 ተማሪዎችንም ደግሞ በቁጥጥር ሥር አውለው ካሳደሩ በኋላ በማግስቱ ምንም ጥፋት የለባችሁም ብለው እንደለቀቋቸው ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። በወቅቱ በአቅራቢያው የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል እንዳልነበር ምስክሮች አስረድተዋል።

- መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ/ም በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የተነሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር #በኤፍራታና_ግድም እና #ቀወት ወረዳዎች በሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ንብረት መውደሙን፣ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እና የቀንድ ከብቶችና ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።

- መጋቢት 6 ቀን 2016 በአማራ ክልል፣ በባሕር ዳር ከተማ ዘንዘልማ አካባቢ አቶ ብርሃኑ ሽባባው አካል ፣ አቶ በላይ አካል እና አቶ ተሾመ ይበልጣል የተባሉ ነዋሪዎች አንዱ በሚሠራበት ሱቅ እና ሁለቱ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ " ኑ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ " በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መጋቢት 7 ቀን 2016 በባሕር ዳር ቀበሌ 14 በተለምዶ ጉዶ ባሕር አካባቢ #የፊጥኝ_እንደታሰሩ በጥይት ተገድለው ተገኝተዋል።

- በባሕር ዳር ዳግማዊ ምኒልክ ክ/ከተማ ጋጃ መስክ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በተፈጸመ ጥቃት ሶላት ስግደት አከናውነው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ የነበሩ የእስልምና ተከታይ 5 ሰዎች (4ቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ) ተገድለዋል።

- ሚያዝያ 7/2016 ከጧቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና ቀበሌ ላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከእስቴ ወረዳ ወደ ላይ ጋይንት ወረዳ በመጓዝ ላይ እያሉ በአካባቢው ላይ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች (#ፋኖ ) ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ጥለው እንደሸሹ #የመንግሥት_የጸጥታ_ኃይሎች ወደ ቦታው በመግባት 7 (1 ሴትና 6 ወንዶች) ሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ ፈጽመዋል። ከ15 በላይ የሚሆኑ የቆርቆሮ ክዳን ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እና 3 የገለባ ቤቶችና ንብረት መቃጠላቸውን እንዲሁም ከ100 በላይ የሚሆኑ የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ የተፈናቀሉ መሆኑን የቀበሌው ነዋሪዎች እና ተጎጂዎች ገልጸዋል።

- ግንቦት 4/2016 ዓ/ም ከቀኑ ከ7፡00 ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በጉሎ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ 2 ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሴት መምህርትን ጨምሮ ሌሎች 9 ሲቪል ሰዎች የቆሰሉ መሆኑን ኢሰመኮ ተረድቷል።

#Amhara #EHRC

@tikvahethiopia
#Amhara

የኤፍራታ ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ ተገደሉ።

በወረዳው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ አልብስ አደፍራሽን ትለንትና በምሽት በመግባት እንደገደሏቸው ተሰምቷል።

ወረዳው ባወጣው የሀዘን መግለጫው ፥ " አቶ አልብስ ለዓመታት በቀውስ ነጋዴዎች ለችግር ተጋልጦ የሴራ ፖለቲካ መሸቀጫ የተደረገውን የጀውሃና አካባቢው ማህበረሰብ ቀርቦ በማወያየት መተማመን ፈጥሮና አደራጅቶ ወደ ቀደመ አካባቢውና ኑሮው እንዲመለስ በማድረግ ላይ ነበሩ " ሲል ገልጿል።

አክሎ " የወደሙትን የጤናና ሌሎች ተቋማትንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስራት መልሶ እያቋቋመ የነበረ ደከመኝን የማያውቅ፣ ለእውነት የቆመ ንፁህ የሕዝብ ልጅና አገልጋይ፤ እውነተኛ የአማራ ጀግና ነበር " ብሏል።

አቶ አልብስ አደፍራሽ ትላንትና ምሽት ቤታቸው በገቡ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

@tikvahethiopia
#Amhara

በአማራ ክልል ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን በአድርቃይ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት 15 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳደር አሳውቀዋል።

ይህ አካባቢ የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ነው።

ነዋሪዎች ምን አሉ ?

- ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 27 ከንጋቱ በ11፡00 ሰዓት አሊጣራ ቀበሌ አንካቶ በተባለ ጎጥ የቡድን መሳሪያ #ከትግራይ_በኩል በመጡ የታጠቁ ኃይሎች ከባድ ጥቃት ተከፍቶ ነበር።

- ጥቃቱ ከንጋቱ 11፡00 ጀምሮ እስከ ጠዋት 2፡30 ገደማ ነበር የዘለቀው።

- አንድ የአካባቢው ነዋሪ ፥ " #በአንድ_ቤት 5 ነበርን፣ ከአምስታችን እኔ ነኝ በአጋጣሚ የተረፍኩት፤ ሌሎቹ ሞቱ። አሰልፈው ነው የተኮሱብን።...እኔንም ሞቷል ብለው ነው ትተውኝ የሄዱት። በፈጣሪ ፈቃድ ነው የተረፍኩት ፤ ጀርባዬን በጥይት ተመትቼ ሆስፒታል ነው ያለሁት " ብለዋል።

- ሌላ ነዋሪ ፤ " በጥቃቱ 15 ሠዎች መገደላቸውን በዐይኔ ተመልክቻለሁ። ሁለት የ16 እና የ19 ዓመት የእህት ልጆቼም ተገድለዋል። " ሲሉ ተናግረዋል።

- ሌላኛው ነዋሪ ፥ " በእሳት እና በጥይት 3 ታዳጊዎችን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል። ህጻናትን ጨምሮ 15 ሠዎች መገደላቸውን አይቻለሁ " ብለዋል።

- የአካባቢው #የሚሊሻ አባል ፤ " ከጥቃት ፈጻሚዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ነበር። አብሮኝ የነበረው ታናሽ ወንድሜ በጥቃቱ ተገድሏል። ቦምብ ጉዳት አድርሷል፤ ጥይቱ፤ መሳሪያውም ብዙ ስለሆነ፤ ድሽቃ፣ ስናይፐር፣ ብሬን አላቸው። በእርቀት እየተኮሱ ነው ጉዳት ያደረሱት " ብለዋል።

-  ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቀው ሲወጡ 3 ሰዎችን ወስደዋል። 500 ከብቶችን ዘርፈወል። ቤቶችም ተቃጥለዋል።

ወረዳው ምን አለ ?

ዋና አስታዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ታደሰ ጥቃቱን የፈጸሙት በዋልድባ ገዳም በኩል አድርገው የገቡ የትግራይ ኃይሎች ናቸው ብለዋል።

ቀብራቸው መፈጸሙን #ማረጋገጥ የቻሉት የስምንት ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከ8ቱ ሟቾች መካከል 6ቱ #ንጹሃን_ነዋሪዎች እንደሆኑ 2ቱ የአካባቢው ሚሊሻ አባላት እንደነበሩ ገልጸዋል።

ጥቃተ የፈጸሙት የትግራይ ኃይሎች ስለመሆናቸው በምን እንዳወቁ ተጠይቀው ፥ ነዋሪዎች በሚናገሩት ቋንቋ እንደለይዋቸውና በተለያዩ ጊዜያትም ትንኮሳዎችን ይፈጽሙ እንደነበር ገልጸዋል።

" የትግራይ ታጣቂዎች ናቸው። ከእነሱ ውጪ የሚመጣብን ሌላ እንደሌለ ነው የተረዳነው " ብለዋል።

" ቡድኑን የሚመራውን ግለሰብ ጭምር እናውቃለን ፤ የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው " ሲሉ ተናግረዋል።

ቦታው ይገባኛል የሚነሳባቸውን አካባቢዎችን ለመያዝ " ስልታዊ " መሆኑን ተንተርሶ ጥቃቱ ሳይፈጸም አልቀረም ብለዋል።

" የማንነት ጉዳይ ሚነሳባቸውን አካባቢዎች በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የግድ የእኛን አካባቢ ማጥቃት አለባቸው። በ2013ም የተመለከትነው ይህን ነው። ስለዚህ ይህን አካባቢ የመቁረጥ፤ ቆርጦ መሀል ላይ ያለን የመንግሥትን መዋቅር የማጥቃት ፍላጎት አለ " ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምን ምላሽ ሰጠ ?

የትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባልደረባ አቶ አማረ ኃይሌ ፤ የትግራይ ኃይሎች ጥቃት አልፈጸሙም ብለዋል።

" እስካሁን ድረስ ወደዚያ አካባቢ ያደረግነው ምንም እንቅስቃሴ የለም " ብለዋል።

" እኛ ያለንበት ቦታና አሁን እየተባለ ባለው ቦታ በጣም ሰፊ ርቀት ነው ያለው። በቀጥታ የሚዋሰን ቦታም አይደለም " በማለት ጥቃቱን እንዳላደረሱ ገልጸዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር " ያሉ ችግሮችን ግጭት አልባ በሆነ መንገድ ለመፍታት ነው የሚያስበው ወደ ግጭት የመግባት ሁኔታ የለንም " ብለዋል።

Credit - BBC AMHARIC

@tikvahethiopia
#Amhara

በአማራ ክልል ዓመቱን ሙሉ ጭራሽ ምንም ያልተማሩ ተማሪዎች እንዳሉ ተሰምቷል።

በዚህም ምክንያት ምንም አይነት የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12 ክፍል ፈተና የማያስትፈትኑ ዞኖች እንዳሉ ታውቋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በሰጠው መግለጫ ፥ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ምንም መቆራረጥ ሳይኖር እየተማሩ አሁን ላይ ትምህርታቸውን እየጨረሱ ያሉ ተማሪዎች አሉ ብሏል።

መሃል ላይ እንዲጀምሩ የተደረጉና የይዘት ክለሳ ተደርጎ እክሰ ነሃሴ ወር ተምረው እንዲያጠናቅቁ የሚደረጉም አሉ ፤ እነሱ አሁን ትምህርት ላይ ናቸው ሲል ገልጿል።

ዓመቱን ሙሉ በሙሉ ደግሞ ጭራሽ ምንም ያልተማሩ ተማሪዎች እንዳሉ ቢሮው አሳውቋል።

ይህ በአብዛኛው በጎጃም ቀጠና እንደሆነ ተጠቁሟል።

ሰሜን ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ምንም አይነት ተማሪ / አንድም እንኳን ተማሪ የ6ኛ ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና #እንደማያስፈትኑ ገልጿል።

ምስራቅ ጎጃም ግን ትንሽ ተማሪ አለው ተብሏል።

የትምህርት ቢሮው አሁን ላይ እየተማሩ ያሉ ግን ፈተና የማይፈተኑትን በቀጣይ በሁለተኛው ዙር እንዲፈተኑ ለማድረግ መታቀዱን አመልክቷል።

ምንም ያልተማሩ ተማሪዎችን በሚመለከት ያለ አንዳች ጥፋታቸው ከእድሜያቸው ላይ አንድ አመት መቀነሱ አገባብነት ስለሌለው የተጎዳ ስነልቦናቸውን ለመጠገን ሚያግዝ ስልጠና ይዘጋጃል ብሏል።

የይዘት ክለሳ ተደርጎም ቢሆን ሲማሩ ከነበሩ ተማሪዎች ወደኃላ እንዳይቀሩ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ሲል ገልጿል።

በአማራ ክልል የ8ኛና 6ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 4/2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን ፦

184,393 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሰኔ 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም

170,470 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ሰኔ 13 እና 14 ቀን 2016 ዓ.ም ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሏል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ (በሁሉም የትምህርት ደረጃ) በዚህ ዓመት መመዝገብ የነበረባቸው 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ የተመዘገቡት 4 ሚሊዮን ናቸው።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
#Amhara

" እስኪበቃን ተገዳድለናል ፤ እስኪበቃን ተዋጋን አሁን ይብቃን !! መፍትሔው ንግግር ነው፣ መነጋገር ነው፣ መከባበር ነው " - አቶ አገኘሁ ተሻገር

በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት በውይይት እና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ አቀረበ።

ጥሪውን ያቀረበው በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ነው።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ምን አሉ ?

" ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መሄድ ቅንጦት ሆኗል፣ ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር መምጣት ቅንጦት ሆኗል ያላቸው በአውሮፕላን ነው የሚሄዱ፣ የእኔና የእናንተ ቤተሰቦች በአውሮፕላን መሄድ አይችሉም።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን መማር አልቻሉም ፣ በርካታ ተማሪዎች ለክልላዊ እና ለአገራዊ ፈተናዎች መቀመጥ አልቻሉም ፣ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች ተገቢ የሆነ ውጤት ለማምጣት እየተቸገሩ ነው፣ በርካታ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እያቋረጡ ነው።

መንግስት የልማት ስራዎችን መስራት አልቻልም።

በኢኮኖሚውም ዘርፍ የአማራ ክልል 35 ከመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን የሰብል ምርት የሚሸፍን ሆኖ ሳለ ፣ ዛሬ ማምረት እንኳ አልቻለም ፣ ማዳበሪያ ማሰራጨት አልቻለም ፣ ምርጥ ዘር ማሰራጨት አልቻልም ፣ የአበዳሪ ተቋማት ብድር መሰብሰብ አልቻሉም ፣ ባንኮች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ፣ ነጋዴው ሰርቶ ፣ ነግዶ ራሱን ማሻሻል አልቻለም፡፡

ህዝባችን የከፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው አይናገርም ቢናገር ችግር ይደርስበታል።

መገዳደሉና ፣ በጠላትነት መፈላለጉ ከበቂ በላይ ነው። ይሄን መገዳደል ካላስቆምን በስተቀር ክልላችን ወደፊት መራመድ / ፈቀቅ እንኳን ማለት አይችልም።

በቃ !! እስኪበቃን ተገዳድለናል፣ እስኪበቃን ተዋጋን ስለዚህ አሁን ይብቃን፣ መፍትሔው ንግግር ነው፣ መነጋገር ነው፣ መከባበር ነው።

ሌለው አካል ብቻ  ችግር ያለበት አድርጌ እኔ እራሴን ከችግር እያወጣው አይደለም፣ እኔ ችግር የለብኝም እያልሁም አይደለም፣ እኔም ሁላችንም የችግሩ አካል ነን፣ ስለዚህ ይብቃን፣ ህዝባችን ከችግር እናውጣው።

አሁንም መንግስታችን እና ፓርቲያችን የሰላም ጥሪ ያቀርባል፣ ለመነጋገር ፣ ለመወያየት ለመደራደር ፣ ለመመካከር የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ዝግጁ ነው። "

#Ethiopia
#AmharaRegion

@tikvahethiopia
#Amhara

ከሰሞኑን በአማራ ክልል፣ በባህርዳር ከተማ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ከተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ በኃሏ ተቋቁሟል የተባለው ' አመቻች የሰላም ምክር ቤት ' በአማራ ክልል እየተደረገ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው ብሏል።

ምክር ቤቱ በዚህ ጦርነት ፥ " ወንድም ከወንድሙ፣ ልጅም ከአባቱ ጋር ነው እየተገዳደለ ያለው " ሲል ገልጿል።

ለፌዴራል መንግሥት / ለአማራ ክልላዊ መንግሥት እና ለፋኖ ኃይሎች ሲል በስም ጠርቶ ባቀረበው የሰላም ጥሪ " የወገናችሁን ስቃይ ተረድታችሁ ምንም መሸናነፍ በማትችሉት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደምትችሉት ንግግር እና ድርድር እንድትመጡ እንጠይቃለን " ብሏል።

ም/ ቤቱ መንግሥት እና የፋኖ ኃይሎች ወደ ሰላም መድረክ እንዲመጡ ለማመቻቸት እንደሚሰራ አመልክቷል።

" በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ንጹሃን ይገደላሉ፣ በጠራራ ጸሃይ ያለ ከልካይ ይዘረፋሉ  " ያለው ምክር ቤቱ ከ12 እስከ 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን አመልክቷል።

መንግሥት ጦርነቱን በድርድር ለመቋጨት ፍቃደኛ እንደሆነ ገልጾ " ብዙ መሪ እና አደረጃጀት ያላቸው የፋኖ ታጣቂዎች ለመደራደር ወደ አንድ መምጣት አለባቸው በማለቱ ይህ የሰላምና ድርድር አመቻች ምክር ቤት መቋቋሙ ተነግሯል።

ምክር ቤቱ 15 አባላት ያሉት ነው።

በሌላ በኩል ፥ ከሰሞኑን በርካታ ሰዎች በክልሉ መገደላቸው ተሰምቷል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ፤ በዳባት ወረዳ፣ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና ፋኖ ኃይሎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የፓሊስ አባላት መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ሁነቱን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ ነዋሪ ፤ " ከተማው ውስጥ አሁንም ሀዘን/ልቅሶ አለ " ሲሉ ተናግረዋል።

" ሀዘኑ የተፈጠረው በአካባቢው ላይ ከ ‘ ፋኖ ’ ጋር በነበረ ውጊያ በርካታ የአካባቢው የጸጥታ አባላት ስለተገደሉ መሆኑን አረጋግጫለሁ " ብለዋል።

የሟቾች ቁጥር ምን ያህል ነው ? ተብሎ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ " የሟቾች ቁጥር ከ115 በላይ ነው " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሟቾቹን በተመለከተም አድማ ብተና ሚሊሻና ፖሊስ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ቃላቸውን የሰጡ ሌሎች ነዋሪዎች የሟቾች ቁጥር እስከ 130 እንደሚደርስ ንጹሐን እንደቆሰሉ ገልጸው ሰሞኑን ከተማዋ ከባድ ሀዘን እንዳስተናገደች ተናግረዋል።

ስለግድያው ምላሽ የጠየቅነው የዳባት ወረዳ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ጉዳዩን በጽሞና ከሰማ በኋላ ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንትም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን ባአዊ ዞን የቲሊሊ ወረዳ ነዋሪዎች ደግሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች 3 ሰዎችን ከቲሊሊ ሆቴል አውጥተው ገድለዋል ሲሉ ከሰዋል።

ሌሎች 2 ሰዎችም ተገድለዋል። በድምሩ 5 ንጹሐን በቲሊሊ ወረዳ መገደላቸውን ተናግተዋል።

በቦታው የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ነበር እንዴ ? በሚል ለነዋሪዎቹ ለቀረበው ጥያቄ ምንም ተኩስ እንዳልነበር፣ ግማሾቹን መንገድ ላይ በሚጓዙበት፣ ሌሎቹን ደግሞ ከሆቴል አስወጥተው እንደገሏቸው አስረድተዋል።

የመንግስት አካላት ስለሁኔታው እንዲያብራሩልን ብንጠይቅም ፍቃደኛ አልሆኑም።

ከዚህ ባለፈም ፥ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ከደብረ ሲና ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ  " ሾላ  ሜዳ " በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ሰኔ 19 በመንግሥት ኃይሎች ደርሷል በተባለ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን እና 4 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ አማርኛው ዘግቧል።

በጥቃቱት ከአያቶቹ ጋር የሚኖር የ14 ዓመት ታዳጊ መገደሉን ፥ አንድ የአይን እማኝ ደግሞ አንድ ሻይ ቤት 11 ሰዎች መገደላቸውን በ20ዎቹ እድሜ የሚገኝ ወንድማቸው ተገድሎ ሜዳ ላይ እንዳገኙት ተናግረዋል።

ሌላ የአይን እማኝ የ11ዱ ሟቾችን ስም ዝርዝር መሰብሰብ እንደቻሉ ሰኔ 20 ቀን/2016 ዓ/ም 4 ተጨማሪ አስከሬን እንደተገኘ ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሎቹ በአካባቢው ለለቅሶ መጥተዋል የተባሉ 3 የፋኖ ታጣቂዎችን ተከትለው ሳይመጡ እንዳልቀረና ስለ ታጣቂዎቹ መረጃ በመፈለግ ግድያውን እንደተፈጸመ አክለዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ጎጃም ዞን ፤ በይልማና ዴንሳ ወረዳ አዴት ከተማ ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ፥ በእለቱ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች ለሰዓታት የዘለቀ ከባድ ውጊያ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎ ጥቃቱ መፈጸሙን አንድ ሴትና 10 ወንዶች እንደተገደሉ ገልጸዋል።

ግድያው የ ' ፋኖ ታጣቂዎች ' ከተማይቱን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ 02 ቀበሌ እርሻ ሰብል በተባለ ሰፈር መንገድ ላይ እና ቤት ለቤት መፈጸሙን ገልጸዋል።

" ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ " በሚል ግድያው ተፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል።

ፋኖ በከተማው ተቆጣጥሮ ውሎ በወጣበት ሰዓት የመንግስት ጸጥታ ኃይል ተመቶ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተፈጠረው ክስተት ከተማዋ በከባድ ሀዘን ውስጥ መውደቋን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ፤ ያለው ጦርነት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በተለያየ ጊዜ በተለያየ ቦታ እየተፈጠረ ባለው ግጭት የሰዎች ህይወት እየጠፋ ነው።

ከሰሞኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ህዝቡ በሰላም እጦት የከፋ ችግር ላይ ወድቆ እንደሚገኝ ተናግረው ፥ መገዳደሉና ፣ በጠላትነት መፈላለጉ እንዲያበቃ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ አገኘሁ ተሻገር፥ " በቃ! እስኪበቃን ተገዳድለናል ፣ እስኪበቃን ተዋጋን ስለዚህ አሁን ላይ ይብቃን ፣ መፍትሔው ንግግር ነው ፣ መነጋገር ነው ፣ መከባበር ነው " ሲሉ ነበር የተናገሩት።

#Ethiopia
#AmharaRegion

@tikvahethiopia
#Amhara

የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ምን አለ ?

- ይህ የ ' ሰላም ካንውስል ' በአማራ ክልል ውስጥ የተፈጠረውን አለመስማማት እና አለመግባባት ተከትሎ የተከሰተውን የእርስ በእርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት መንግሥትን እና ታጥቀው ጫካ የገቡ የፋኖ አባላትን ለማደራደርና ለማወያየት ይቻል ዘንድ ለመመቻቸት የተሰየመ ነው።

- ድርሻው መንግሥት እና የፋኖ አባላትን ለድርድር፣ ለውይይት እንዲበቁ ማመቻቸት ብቻ ነው።

- ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ደረጃ ፣ በየትኛውም ቦታ ፣ በየትኛውም አደራዳሪ የመንግሥት ኃይሎች እና በጫካ የሚገኙ የፋኖ ወንድሞቻችን ቢያስን ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግር እና ድርድር እንዲያደርጉ ይህ ካውንስል ተሰይሟል።

- በጦርነት እንጨራረሳለን እንጂ አንሸናነፍም።

- የአማራ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ምስቅልቅል ውስጥ ይገኛል።

- ግጭቱ አጠቃላይ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት እና ወደባሰ የድህነት አረንቋ እየከተታት ይገኛል።

- ለዚህ ግጭት መነሻ የአማራ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሰለጠነ ንግግር እና ድርድር አለመፈታታቸው ወይም ደግሞ የሚፈቱበትን ሂደት የሚያመለክት ግልጽ ፍኖተ ካርታ አለመቀመጡ ነው።

የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ተብለው የተለዩት ፦
° የተዛባ ትርክት ማረቅና ማስተካከል
° ህገመንግስት ይሻሻልልን
° የወሰን እና ማንነት ጉዳይ
° ፍትሃዊ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ውክልና ጉዳይ
° በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ህዝብ ጉዳይ
° የአዲስ አበባ የመልካም አስተዳደር እና አድሏዊ አሰራር ችግር አለመቀረፉ
° በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ለሚደርስባቸው ግድያ እና መፈናቀል ተጠያቂነት አለማስፈን ጉዳይ .. የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

- እነዚህ ጥያቄዎች በቅንነት በሀገሪቱ ጥላ ስር በንግግር እና በድርድር ሊፈቱ የሚገባቸው እንጂ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ አልነበሩም።

- የክልሉ መንግሥት በህዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዷል።

- ክልሉም ከችግሩ ሚያወጣው ፣ የተደራጀ የፖለቲካ እሳቤ የሚፈጥርለት ምሁር የመከነ እስከሚስል ደርሷል።

- ላለፉት ዓመታት የኢኮኖሚን ችግር የሚቀርፍ የማሻሻያ ድጋፍ ይደረጋል ሲባል በተለያዩ አጀንዳዎች በመወጠር እና የደህንነት ስጋት ውስጥ እንዲወቅ ሆኖ በከፋ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ውስጥ ይገኛል።

- ከ ' ህወሓት ' ጋር የተደረገው ስምምነት በአግባቡ ሳይተገበርና የአማራ ህዝብ ህልውና ስጋት ዋስትና ሳይበጅለት ቀርቶ ነው የክልሉ የጸጥታ ችግር ተባብሶ ከ2015 ሀምሌ መጨረሻ አንስቶ በነፍጥ የታገዘ ግጭት የጀመረው። በዚህ ምክንያት ለአንድ አመት የሚጠጋ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነበር።

- ለአንድ አመት በተጠጋው ጦርነት የክልሉ ህዝብ መከራ እና ምስቅልቅል ህይወት ውስጥ ይገኛል።

- በአሁን ጊዜ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በመንግስት እና የአማራን ህዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ጫካ ገብተናል ባሉ ' ፋኖዎች ' መካከል በሚካሄድ በትጥቅ የታገዘ ጦርነት ፦
ንጹሃን ተገድለዋል።
ከ12 እስከ 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።
ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ውጭ ሆነዋል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ክፉኛ ተጎድቷል።
የግል እና የመንግስት ተቋማት ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ ባለመቻላቸው አገልግሎት አሰጣት ክፉኛ ተዛብቷል።
ነፍሰጡር እናቶች በአግባቡ የአምቡላንስ አገልግሎት አያገኙም።
እናቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከጦርነት ተሳትፎ ውጭ የሆኑ ዜጎች ለከፋ የስነልቦና ጫና ተዳርገዋል።
እጋታ ተስፋፍቷል።
ዜጎች ያለ ከልካያ በጠራራ ጸሀይ ይዘረፋሉ፤ ይገደላሉ።
ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተስተጓጉለዋል።
ህዝቡ ለሁለት ወገን ግብርና ቀረጥ ይከፍላል።

ይህ ጦርነቱ ካመጣቸው መዘዞች መካከል ነው።

- ችግሩን ለመቅረፍ በአዲስ አበባ እና ከባህር ዳር ከህብረተሰቡ የተውጣጣ ክፍል ውይይት አድርጓል። በውይይቶቹ የሀገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና የሲቪል አመራሮችም ተገኝተው ነበር።

- ጦርነቱ አሸናፊነት የሌለው የእርስ በእርስ ጦርነት ስለሆነ በንግግር በውይይት በድርድር ይፈታ የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

- በክልል ፣ በሀገር ደረጃ በየትኛውም መንገድ ይሁን የአማራን ህዝብ ጥቅም ይዤ ነው የምዋጋው ከሚል ኃይል ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር እንዲደረግ የመፍትሄ ሀሳብ ተቀምጧል።

- መንግሥት አሸናፊ የሌለው ይሄ አውዳሚ ጦርነት በንግግር እና ድርድር ለመፍታት " ፍቃደኛ ነኝ ነገር ግን ፋኖ አደረጃጀቱና መሪው ብዙ ነው ለመደራደር አንድ መሆን አለባቸው " በማለቱ የድርድሩ ደረጃ ጊዜ ፣ ቦታ እና ተደራዳሪዎች ተለይተው ለንግግር እና ድርድር እንዲበቁ ይህ 15 አባላት ያሉት የሰላም ካውንስል ተመርጧል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Amhara

በነገው ዕለት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ይጀመራል።

በአማራ ክልል ውስጥ የተፈታኞች ቁጥር ከታቀደው በግማሽ እንደሚያንስ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዛሬ አስታውቋል።

ቢሮው በዚህ ዓመት ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀመጡ አቅዶ ነበር።

ነገር ግን አሁን ፈተና ላይ ይቀመጣሉ የተባሉት  96 ሺህ 408 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

ቀሪ 106 ሺህ ያክል ተማሪዎች ፈተና አይወስዱም።

አሁን ላይ ፈተናውን የማይወስዱ ተማሪዎች  ተምረው በመስከረም 2017 ዓ/ም በሁለተኛ ዙር ለመፈተን እቅድ እንደተያዘ ተነግሯል።

በነገ ዕለት ፈተና የሚጀምሩት ተማሪዎች ለፈተናው መቀመጥ የሚያስችላቸውን ትምህርት የተከታተሉ እንደሆኑ ቢሮው አሳውቋል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት የሀገሪቱ ከፍተኛው ውጤት የሚመዘገብበት እና እጅግ በጣም ጎበዝ ተማሪዎች የሚገኙበት አማራ ክልል ዘንድሮ የሚጠበቅበትን ያክል ተማሪ ባለማስተማሩ ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች በመጀመሪያ ዙር ፈተና ላይ መቀምጥ አልቻሉም።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ዘንድሮ ትምህርታቸውን መማር ከነበረባቸው 6.2 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል መማር የቻሉት 3.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ናቸው።

ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርት አልተማሩም።

ይኸው እስከ ዛሬ ትምህርት ያልጀመሩ ዞኖች እና ወረዳዎች አሉ።

በቅርቡ ቢሮው ዓመቱን ሙሉ በሙሉ ጭራሽ ምንም ያልተማሩ ተማሪዎች እንዳሉ ገልጾ ነበር።

ተማሪዎች ካልተማሩባቸው መካከል ሰሜን ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ዋነኞቹ ሲሆኑ ምንም አይነት ተማሪ / አንድም እንኳን ተማሪ የ6ኛ ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና እንደማያስፈትኑ መግለጹ ይታወሳል።

#AmharaEducationBureau
#NationalExam
#DeutscheWelle

@tikvahethiopia
#Amhara #Bahirdar

በአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር ክልከላ ተጣለ።

ክልከላው የተጣለው በከተማው የጸጥታ ምክር ቤት ነው።

ከክልከላዎቹ ምንድናቸው ?

-  የቤት መኪና ፣ ታክሲ ፣ የመንግሥት መኪና ፣ ማንኛውም የጭነት መኪና ተሽከርካሪ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኃላ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ተጥሏል። ከተፈቀደው ሰዓት እላፊ ሲያሽከረክሩ መገኘት በሕግ ያስቀጣል።

- ከምሽቱ 3 ሰዓት በኃላ ማንኛውም የሰው እንቅስቃሴ ተከልክሏል።

- ማንኛውም ተሽከርካሪ ታርጋ ሳይኖረው ወይም ሳያስር መንቀሣቀሥ አይችልም።

- ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ውጭ ስቲከር መለጠፍ ተከልክሏል።

-  ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ባጃጅ መጋረጃ እና የግራ ጎን ሸራን ሳያነሱ ማሽከርከር ተከልክሏል።

- የባጃጅ ተሽከርካሪ ማኀበራት ከተሰጣችው የሥምሪት ቦታ ውጭ ማሽከርከር አይችሉም።

- በማኀበራት ተደራጅተው ስምሪት ከተሰጣቸው ባጃጆች ውጭ ማሽከርከር ተከልክሏል።

- የባጃጅ ተሸከርካሪዎች የባሕር ዳር አስተዳደር ትራንስፖርት ጽ/ቤት በአዲስ የሚሰጠውን መለያ ወይም ባር ኮድ ግልጽ እና በሚታይ መንገድ የመለጠፍ ግዴታ አለባችው።

- የባጃጅ ባለ ንብረቶች ለቀን ገቢ ወይም ለተለያዩ የጊዜ ገደብ ለሚያከራዮቸው ግለሰቦች የውል ስምምነት በመያዝ ለፓሊስ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ማሳወቅ አለባቸው።

- ባጃጆች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ማሽከርከር ተከልክሏል።

- ባለ 2 እግር ሞተር ተሽከርካሪ ላልተወሰነ ጊዜ ማሽከርከር ተከልክሏል።

ክልከላው የማይመለከታቸው እነማንን ነው ?

ክልከላ የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች ፦
° በጸጥታ ሥምሪት ላይ የሚገኙ፣
° አንቡላሶች፣
° የእሳት አደጋ መኪናዎች ናቸው። ነገር ግን በማንኛውም ሰዓት በአንቡላንስም ኾነ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።

በሌላ በኩል ፤ ከጸጥታ መዋቅሩ አባላት እና ለጸጥታ ሥራ ተሰማርተው የመንቀሣቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሰዎች ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሣቀሥ ተከልክሏል።

ማንኛውም የጸጥታ አባል ከተሰጠው ስምሪት ውጭ በሚሆንበት ጊዜ ሲቪል ለብሶ የጦር መሣሪያ ይዞ መንሳቀስ እንዳይችል ክልከላ ተጥሏል።

#AmharaRegion

@tikvahethiopia
#Amhara

“ የሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም ”- የደሴ ከተማ አስተዳደር

በአማራ ክልል ፣ በደሴ ከተማ አስተዳደር ፣ በአራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ “ ጀሜ ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር የመሬት መንሸራተት አደጋ መከሰቱን ከተማው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ምን አለ ?

- የመሬት መንሸራተት መጠነኛ የሆነ ጉዳት አድርሷል።

- አደጋው  የተከሰተው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ/ም ሌሊት በዘነበው ዝናብ አማካኝነት ነው።

- በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባይኖርም በመተላለፊያ መንገዶች፣ አስፓልት እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ የመሰንጠቅ አደጋ ደርሷል።

- አንድ መስጂድ ጉዳት ደርሶበታል። የመሰንጠቅ አደጋ፤ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞታል ማለት ነው።

- አስፓልቱ መንገዱ ጉዳት ስለደረሰበት ለጊዜው ለተሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ ተደርጓል።

- አሁን አደጋ በተከሰበት በአካባቢ ላይ ኮሚቴዎች እና የክፍለ ከተማው አመራሮች ስምሪት ተሰጥቷቸው ክትትል እያደረጉ ነው።

- ለአደጋ ተጋላጭ የአካባቢው ማህበረሰቦች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ጊዜያዊ ካምፕ እንዲያርፉ ተደርጓል።

- ችግሩ ከዚህ የበለጠ እንዳይከፋ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የከተማ አስተዳደሩ ሥራ እየሰራ ነው። የአካባቢው ማህበረሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሳተፈ ነው።

- አሁን አደጋው በተከሰተበት ቦታ ላይ ባይሆንም፣ በከተማው አቅራቢያ በሚገኝ ሌላ ቦታ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ ነበር።

ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ በርካቶች መሞታቸው፣ በሌሎች ቦታዎችም በደረሰ ተመሳሳይ ችግር የሰው ህይወት ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
🔈#የህዝብድምጽ

የአማራ ህዝብ አስተማማኝ ሰላምን ካጣ ዓመታት አልፈዋል።

በየጊዜው የሚያገረሸው የተኩስ ልውውጥ የሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል።

በክልሉ ያሉ ሲቪል ሰዎች በሰላም ወጥቶ መግባት ቅንጦት እንደሆነ ይናገራሉ።

የኢኮኖሚውና የሰላም እንቅስቃሴውም ከሌሎች ክልሎች አንጻር እየተዳከመ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም የሀገርና የውጭ ቱሪስት የሚጎርፍባቸው አካባቢዎች ዛሬ ሰው አይታይባቸውም።

በዚህ ስራ የተሰማሩ ዜጎችም ስራ አጠተው ቁጭ ብለዋል።

አስተያየቱን የሰጠን ወጣት አስጎብኚ ፥ " ይኸው ግራ ተጋብተን ቁጭ ብለናል። የሚበላ ማግኘት አልቻልም። ይህ ሁኔታ በዚህ እየቀጠለ ከሄደ ከአሁኑም በላይ ከባድ መዘዝ ይዞ ይመጣል " ሲል ገልጿል።

የሸቀጦች ዋጋም ቀደሞም ተወዷል አሁን ደግሞ ጭራሽ ዶላር ጨምሯል ተብሎ ተሰቅሏል።

ከተኩስ ልውውጥ ባለፈ እገታ ፣ ዘረፋ የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው።

ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች ባለው የፀጥታ ችግር ከክልሉ ውጭ ሃብታቸውን ይዘው እየሄዱ ናቸው።

አንድ ቃላቸውን የሰጡን የንግድ ሰው ፣ ባህር ዳር ላይ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች በሚፈለገው ልክ ስራ መስራት ስላልተቻለ እንዲሁም ጥናት ተደርጎ በሚፈጸመው እገታ ምክንያት የሚወዱትን ከተማ ለቀው አ/አ ለመግባት መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

ከምንም በላይ ግን በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ህዝብ ፣ ህጻናት፣ እናቶች ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ናቸው።

ትራንስፖርት በየጊዜው ስለሚቋረጥ ለህክምናም ይሁን ለሌላ ጉዳይ መንቀሳቀስ አልተቻለም። የአየር ትራንስፖርት ለመጠቀም አቅም የለም።

አንድ ደብረ ማርቆስ ያሉ እናት በሰጡት ቃል " እኔ ልጄን ማሳከም ነበረብኝ አዲስ አበባ ፥ ግን ሰሞኑን የጸጥታ ሁኔታው አስጊ ስለነበር አልተቻለም። ፈጣሪን እየተማጸንኩ ቁጭ ብያለሁ " ብለዋል።

አንድ የባህር ዳር ነዋሪ በበኩላቸው ፥ በየጊዜው የሚያገረሸው ጦርነት ምክንያት ህዝቡ የከፋ ቀውስ ላይ እንደጣለው ይህም ደግሞ አሁን ከአመት እንዳለፈው ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈው በባህር ዳር በየጊዜው የሚጣለው ቦምብ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደደቀነ ምሽት ላይ ለመንቀሳቀስ እንደማይችል ተናግረዋል።

ከባህር ዳር ወደ አ/አ በትራንስፖርት መሄድ አስቸጋሪ እንደሆነ ፣ ያለው የዋጋ ግሽበትም ማህበረሰቡን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግር እየጋለጠ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተለያዩ ቦታዎችም የመድሃኒት አቅርቦት አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

" አሁን አሁን በሰላም ወጥቶ መግባት ቅንጦት " የሚሉት ነዋሪው ፤ የአማራ ጉዳይ ግን ችላ እንደተባለ ተናግረዋል።

ሌላው የተማሪዎች ጉዳይ ሲሆን ዘንድሮ ብዙ ተማሪ ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ አልተቀመጠም። አማራ ክልል ጂኒየስ የሚባሉ ተማሪዎችን በየዓመቱ ያፈራል። በጦርነት ውስጥ እንኳን ሆኖ ከሀገር ከፍተኛውን ውጤት የሚያመጡት የዚሁ ክልል ልጆች ናቸው።

አንድ 12ኛ ክፍል ፈተና መፈተን ያልቻለ የጎጃም አካባቢ ተማሪ ፥ " ቀጣይ እንፈትናለን ይላሉ መቼ እንደሆነ አናውቅም። እኛ አካባቢ ዛሬም ድረስ መረጋጋት የለም። ይኸው እድሜያቻን በከንቱ ማለቁ የማይቀር ይመስላል " ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የአማራ ህዝብ ከዓመታት በፊት የትግራይ ጦርነት ተስፋፍቶ በመጣበት ወቅት ለወራት በከፍተኛ ስቃይ ፣ መከራ እና በደል ውስጥ አልፏል።

ከሲቪሎች ግድያ፣ ጉዳት ባለፈ ለበርካታ ወራት ኢኮኖሚው ቆሞ ነበር። ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከቆመ በኃላ ደግሞ ክልሉ ዛሬም ድረስ በሌላ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ዘላቂ መረጋጋት ታይቶበት አያውቅም። ይህ ሁኔታ በቀጣይ አመታት በሁሉም ዘርድ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው።

#Amhara #Ethiopia

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
TIKVAH-ETHIOPIA
ሬሜዲያል ዘንድሮም ይኖራል። " አምና ሰጥተናል። ዘንድሮ ከዓምናው የቀነሰ ቁጥር እንወስዳለን። የሬሜዲያል ፕሮግራም በሂደት እየቀነሰ ይሄዳል " ሲሉ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ተግረዋል። @tikvahethiopia
#Amhara

የትምህርት ሚኒስቴር ፤ " ዘንድሮ ሁሉም
ክልሎች አምና ካሳለፉት ተማሪ በላይ አሳልፈዋል " ብሏል።

" በፐርሰንቴጅም በአክቹዋል ቁጥርም ካለፈው የተሻለ ነው " ተብሏል።

ከአክቹዋል ቁጥር ያነሰው አንድ ክልል ነው እሱም የአማራ ክልል እንደሆነ ተገልጿል።

ክልሉ ያነሰው ደግሞ የተፈተኑት ተማሪዎች ቁጥር ከግማሽ በታች ስለነበር ነው ተብሏል።

ክልሉ ፈተና ካስፈተናቸው ውስጥ ግን 6.6 በመቶ ተማሪዎች አልፈዋል።

አምና ከተመዘገበው 4.1 በመቶ ዘንድሮ በልጧል።

@tikvahethiopia
#Amhara

" የፋኖ ኃይሎች ወደ ድርድር መግባትን በመርህ ደረጃ ይቀበሉታል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ላይ እምነት የላቸውም " - የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል

በአማራ ክልል በሚፋለሙት የፌዴራል መንግሥት እና የፋኖ ኃይሎች መካከል ያለው ሥር የሰደደ አለመተማመን ሰላም ለማውረድ የሚያደረገው ጥረት ፈተና እንደሆነበት፣ የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አስታውቋል።

የካውንስሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ ምን አሉ ?

(ለሪፖርተር ጋዜጣ)

- የፌዴራል መንግሥት አመራሮችን ለማግኘት ጥረት ተደርጎ ነበር ግን አልተሳካም። እስካሁን ከፌዴራል መንግሥት በኩል ተገናኝቶ መወያየት የተቻለው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ብቻ ነው። የሰላም ሚኒስቴርም ካውንስሉ የሚያቀርበውን ጥሪ እንደሚቀበል አሳውቋል።

- ከተለያዩ የፋኖ ኃይሎች ጋር ንግግር ተደርጓል። ወደ ድርድር መግባትን በመርህ ደረጃ ይቀበሉታል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ላይ እምነት የላቸውም። ' ጊዜ መግዣ ነው ' ብለው ያምናሉ፣ እኛንም የፈተነን ይኸው ያለመተማመን ችግር ነው።

- ከፌዴራል መንግሥት በኩል ካውንስሉ ተጨማሪ ሥራዎች ይጠብቁታል። የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለበት።

- በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እገዛ ለማግኘት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ ከኢጋድና ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮች ጋር በቅርቡ ውይይት ተደርጓል።

- ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር ንግግር ተደርጓል፤ እነሱ ለማገዝም ዝግጁ ናቸው። በካውንስሉ በኩል ደግሞ እየደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር " የአማራ ክልል ሁኔታን ችላ ብላችሁታል " ብለናቸዋል።

- የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ ከስድስት ዲፕሎማቶች ጋር ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም የክልሉን የሰላም ዕጦት ችላ ማለታቸውን ተጠቁሞ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

- ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ካውንስሉ የሚያደርገውን ጥረትም ሆነ ድርድሩ እንዲሳካ ለማገዝ ፈቃደኛ ነው። ነገር ግን በፋኖ አደረጃጀት ላይ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ 

ካውንስሉ አግኝቼ አናገርኳቸው የሚላቸው የፋኖ ኃይሎች እነማን ናቸው ? የትኛውን የአደረጃጀትስ ነው ያናገረው ? ለዚህ ጥያቄ ፦

" ይህንን መናገር አያስፈልግም፣ ምክንያቱም አንዳንዶች ነገሩን ' እገሌ ሊደራደር ነው ' በማለት መበሻሸቂያ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም ከየትኛው የፋኖ አመራር ጋር እንደተወያየን መግለጽ ጠቃሚ አይደለም።

' እገሌ ሊደራደር ነው ' የሚለውን ጉዳይ የፋኖ ኃይሎች እንደ መበሻሸቂያ እየተጠቀሙበት ስለሆነ፣ ካውንስሉ የተደራጀ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በፋኖ በኩል እገሌ እንዲህ ብሏል ከማለት እንቆጠባለን። " ሲሉ መልሰዋል።

የፋኖ ኃይሎች ድርድርን በመርህ ደረጃ እንደሚቀበሉት ነገር ግን " የፌዴራል መንግሥት ድርድሩን እንደ ጊዜ መግዣነት ሊጠቀምበት ነው " የሚል እምነት እንዳላቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ካውንስሉን" ሀቀኛ ድርድር ለማድረግ ሳይሆን ለማምታታት ነው " የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ተጠቁሟል።

ይሁንና አለመተማመኑን ለመቅረፍ የሁሉንም አካላት ቅንነት ካውንስሉ እንደሚፈልግ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጠው ቃል አመላክቷል።

#Amahra #Ethiopia

@tikvahethiopia
#Amhara

" ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ነው እቅድ የተያዘው ከነሐሴ 20/2016 ዓ/ም ጀምሮ የተመዘገቡት ግን 1.7 ሚሊዮን ናቸው - የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በየጊዜው የተኩስ ልውውጥ የሚስተዋልበት አማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዘገብ እንዳቀደ፣ ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ የተመዘገቡት ግን 1.7 ሚሊዮን ተማሪዎች መሆናቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ " ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 292 ሺሕ በላይ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 1.2 ሚሊዮን በላይ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ 180 ሺሕ ተማሪዎች ተመዝግበዋል " ብሏል፡፡

" በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምዝገባው እየተካሄደ ነው፡፡ ትንሽ እሱ ላይ መዘግየት ይታያል፡፡ እስካሁን በጠቅላላ ወደ 1.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ናቸው የተመዘገቡት የእቅዱን ወደ 24 ፐርሰንት አካባቢ " ነው ያለው፡፡

በጸጥታው ችግር ባለፈው ዓመት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡  በ2017 የትምህርት ዘመንስ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች እጣ ፈንታቸው ምንድን ነው ? እውነት ተመዝግበውስ ለመማር አስቻይ ሁኔታ አላቸው ወይ ? ከዚህ አኳያ ቢሮው ምን አቅዷል ? ምንስ እየሰራ ነው? ስንል ቢሮውን ጠይቀናል፡፡

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን " በክልሉ ከ10 ሺሕ 874 በላይ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የእኛ ፍላጎት እነዚህ ሁሉም ትምህርት ቤቶች 7 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲያስተምሩ፣ መማር ማስተማሩ እንዲጀምር/እንዲቀጥል ነው " ብለዋል፡፡

" በተለይ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታ ችግር ስላለ የትምህርት ሥራን ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ሁሉ የምዝገባ ሥራን ለመስራት እንቅፋቶች ቢኖሩም ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ የምዝገባ አፈጸጻሙ በምንጠብቀው ልክ ባይሆንም ምዝገባ እየተካሄደ ነው " ሲሉ አቶ ጌታው ተናግረዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱ እዳይደነቃቀፍ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም ሰው ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ቢሮው አስምሮበታል።

" አንድንድ ቦታ ላይ ትላንት ትምህርት ሲጅሩ ልንማር ይገባል የሚል ሞቶ ሁሉ ይዘው የወጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ ይሄ በጣም ልብ ይብራል ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሁሉ፡፡ ምሁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ በዛኛው ወገን ያሉ ወንድሞቻችንም ጭምር ይህን ተረድተው ትምህርትን ነጻ ሆነን እንድንስራ በጎ ሚናቸውን መጫወት አለባቸው " ሲሉ አስገንዝበዋል።

" በ2016 ዓ/ም በተለያየ ምክንያት ትምህርት ተቋርጦባቸው የቆዩ አካባቢዎች፤ ሳይማሩ የቆዩ ተማሪዎች፤ ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶች አሉ " ሲልም ቢሮው ገልጿል፡፡

ከውድመት ጋር በተያያዘም አቶ ጌታቸው በሰጡት ቃል፣ " በክልሉ ካለው የጸጥታ ችግር ወይም ግጭት ጋር በተያያዘ ከፍተኛም መካከለኛም ጉዳት የደረሰባቸው ወደ 1115 ትምህርት ቤቶች አሉ " ነው ያሉት፡፡

" እነዚህን ትምህርት ቤቶች መልሶ ግብዓታቸውን በማሟላት ረገድ አንደኛ በአካባቢው ማህበረሰብ የሚሸፈን በዚያው ነው የሚሸፈኑት " ብለዋል፡፡

" የእኛን የክልሉን ኢንተርቬንሽን ሚጠይቁት ደግሞ አጋር አካላትን እያሳተፍን እቅድ አቅደን እያነጋገርን ነው፡፡ ከነርሱ ሀብት እያፈላለግን ትምህርት ቤቶች እንደገና ቁስቁሳቸው እንዲሟላ፣ እንዲገነቡ የማድረጉን ሥራ ወደፊት የምንስራ ነው የሚሆነው " ሲሉ አክለዋል፡፡

በክልሉ በ2016 ዓ/ም መመዘገብ ከነበረባቸው 6.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት እንዳልተመዘገቡ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በ2017 ትምህርት ዘመን ደግሞ ቢሮው ለመመዝገብ ካቀደው ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ተመዘገቡ የተባለው 1.7 ተማሪዎች ናቸው፡፡

#TIKvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Amhara " ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ነው እቅድ የተያዘው ከነሐሴ 20/2016 ዓ/ም ጀምሮ የተመዘገቡት ግን 1.7 ሚሊዮን ናቸው - የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በየጊዜው የተኩስ ልውውጥ የሚስተዋልበት አማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዘገብ እንዳቀደ፣ ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ…
#Amhara

“ የእኛ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ 2 ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ደረጃቸው ዝቅተኛ ግን መማር ማስተማሩን ማስኬድ የሚችሉ እንደማለት ነው ” - የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

በአማራ ክልል በተለይ በጸጥታ ችግር ሳቢያ የግብዓት እጥረት ያለባቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉ፣ ይህም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ማነቆ እንደሆነባቸው ወላጆች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገጸዋል፡፡

ለአብነትም እንደ መጽሐፍት፣ ወንበር መሰል ቁሳቁሶች እንደሌሉ፣ የወደሙ ትምህርት ቤቶች አለመጠገን፣ በግጭት የቀጠና ውስጥ የሆኑ አቅመ ደካማ ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው እንኳ የትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዳልቻሉ ነው ያስረዱት፡፡

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጥ የክልሉን ትምህርት ቢሮ ጠይቋል፡፡

ቢሮው ምን ምላሽ ሰጠ ?

“ የግብዓት እጥረት አለብን ያሉ ትምህርት ቤቶች ይኖራሉ፡፡ ትክክል ነው፡፡ የግብዓት እጥረታቸው በሁለት መንገድ ነው የሚፈታው፡፡

አንደኛ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በክልል ደረጃ ደግሞ የሚሟሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍት በክልል ነው የምናሟላው፡፡

ከ14 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት ታትመው ስርጭት ተደርጓል፡፡ አሁንም በቀጣይ የሚሰራጩ አሉ፤ ከ1 ቢሊዮን በላይ በጀት የክልሉ መንግስት መድቦ አሁንም የሚታተሙ መጽፍት አሉ፡፡

እነርሱን አሳትመን እናሰራጫለን፡፡ የመምህራን ቅጥርም እናሟላለን፣ ትክክል ነው፡፡

የእኛ ክልል ትምህርት ቤቶች ሙሉ ግብዓት የተሟላላቸው፣ ስንታንዳርዳቸውን ያሟሉ አይደሉም፡፡

ትምህርት ቤቶች በ4 ደረጃ ይከፈላሉ፡፡ ደረጃ 1፣ 2፣ 3 እና ደረጃ 4 ተብለው፡፡ ደረጃ 4 የሚባል ትምህርት ቤት በክልሉ የለንም፡፡

ደረጃውን ያሟላ በጣም ኢንተርናሽናል እንደማለት ነው፡፡ ደረጃ 3 የሚባለው ደግሞ ለተማሪዎች መማር ማስተማር የተሻለ የሆነ ትምህርት ቤት ማለት ነው፡፡

የእኛ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ 2 ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ደረጃቸው ዝቅተኛ ግን መማር ማስተማሩን ማስኬድ የሚችሉ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ብዙ ግብዓት የሚጎድላቸው ናቸው፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 3ቱም ሳይንስ ቤተ ሙከራ እንዲሟላ፣ ደረጃውን የጠበቀ የኳስ ሜዳ እንዲኖረው፣ አጥር እንዲኖረው፣ ስታንዳርዱን እንዲያሟላ፣ ፋሲሊቲውን በማሟላት ረገድ መስራት የሚጠይቀን ሥራ አለ፡፡

እሱን በእቅድ ለመምራት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ግን ሙሉ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡

የእኛን ትምህርት ቤቶች በስንት ዓመት እንቀይራቸዋለን ደረጃቸውን ለማሻሻል ብለን አንድ በጣም ትልቅ የለውጥ እቅድ አቅደን ወደ ሥራ በገባን ማግስት ነው የጸጥታው ችግር የተፈጠረው፡፡

በዚህ ዓመት ውስጥ ትምህርት ቤቶቹን እንቀይራለን ብለን ነበር ዞሮ ዞሮ ወደ ሥራ መግባት አልተቻለም ”
ብሏል፡፡

የግብዓት እጥረት ላለባቸው ከባለሀብቶችና ባለንብረቶች ድጋፍ የማሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል፡፡

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Amhara “ የእኛ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ 2 ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ደረጃቸው ዝቅተኛ ግን መማር ማስተማሩን ማስኬድ የሚችሉ እንደማለት ነው ” - የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአማራ ክልል በተለይ በጸጥታ ችግር ሳቢያ የግብዓት እጥረት ያለባቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉ፣ ይህም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ማነቆ እንደሆነባቸው ወላጆች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገጸዋል፡፡ ለአብነትም እንደ…
#Amhara #Education

" ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ሁሉም ይተባበር " - የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

ለ2017 ትምህርት ዘመን ምን ያህል ተማሪ ተመዘገበ ?

በአማራ ክልል ፣ ባለፈው ዓመት ት/ቤት መግባት ከነበረባቸው 6 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ግማሽ ያክሉ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት እንዳልተከታተሉ በወቅቱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አመልክቷል።

በተለይም በጎጃም ቀጠና የሚገኙ አብዛኛዎቹ የ6ኛ፣ የ8ኛና የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና መውሰድ አልቻሉም።

እስካሁን በ2017 ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ችግሩ ሳይቃለል በዚህ ዓመት ቢሮው 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ቢያቅድም ከነሐሴ 20/2016 ዓ ም ጀምሮ ባደረገው ምዝገባ ግን እስካሁን የተመዘገቡት 2 ሚሊዮን አይሞሉም።

➡️ እድሜያቸው ከ4 እስከ 6 ዓመት የሆናቸውን 1 ሚሊዮን 760 ህፃናትን ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት 324 ሺህ ያክሉ ናቸው፡፡

➡️ ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል 4 ሚሊዮን 800 ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ቢባልም ባለፉት 20 ቀናት የተመዘገቡት ግን ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ አይበልጡም።

➡️ በሁለተኛ ደረጅ ትምህርት ቤት 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የታቀደ ሲሆን ወደ ትምህርት ቤት የመጡት ግን 300 ሺህ ያክሉ ናቸው።

ተማሪዎች ለምን ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም ?

ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን ፦
- በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፣
- ተማሪዎች ዘግይቶ የመመዝገብ ልማድ፣
- ፖለቲካን ከትምህርት ጋር የማያያዝ ጉዳዮችና ሌሎች ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዶቼ ቨለ ሬድዮ በሰጠው ቃል አመልክቷል።

የክልሉ የትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለሬድዮ ጣቢያው በሰጡት ቃል ፥ " ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ፦
° የሀገር ሽማግሌዎች፣
° የሐይማኖት አባቶች፣
° ተፅዕኖ ፈጣሪዎች
° መንግስትና ኃላፊው
° በጫካ ያሉ ወንድሞች ጭምር ሊተባበሩ ይገባል " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወላጆች በሰጡት ቃል የልጆች ወደ ትምህርት ቤት አለመሄድ እንዳሳሰባቸው እና ጉዳዩ ከባድ እንደሆነ ጠቁመዋል። በአንዳንድ የገጠሩ ክፍል " ትምህርት ቅንጦት እየሆነ ነው " ሲሉም ለሬድዮ ጣቢያው ተናግረዋል።

አማራ ክልል በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈ ያለ ክልል ቢሆንም በተለይ በብሔራዊ ፈተና በየዓመቱ እጅግ ምጡቅ ልጆች የሚወጡበትና ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገብበት ነው። ለአብነት እንኳን ባለፈው ዓመት በብሔራዊ ፈተና ሁለተኛው የሀገሪቱ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በዚሁ ክልል ነው።

#Amhara #Education

@tikvahethiopia