TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.3K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ሰላም

" እርቅ ይውረድ ! የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ ! ሰላም ይታወጅ ! ምድሪቱንም እናሳርፋት ! " - ቅዱስነታቸው

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ አባታዊ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው ካስተለለፉት መልዕክት የተወሰደ ፦

" ከአካላዊ ጦርነት እስከ ቃላት ውርወራ ብዙ ጥላሸት የመቀባባት ሰለባ ሆነው የወደቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆቻችን ትምህርት ሆነውን ልባችን ዘንበል ባለማለቱ ለወደፊት ሊመጣ የሚችለው ሲታሰብ እጅግ ያስፈራልና በዐራቱም ማዕዘን ነፍጥ አንሥታችሁ ያላችሁ በሙሉ ያነገባችሁትን ገዳይ መሣርያ አውርዳችሁ ለሰላምና ለዕርቅ ቅድሚያ በመስጠት ለአንዲት አገራችሁ ሕልውና ተገዢዎች እንድትሆኑ፤ መንግሥትም ልበ ሰፊ ሁኖ ሁሉንም ለውይይት እንዲሰበስብ በጽኑ እንለምናለን።

በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያላችሁ ሽማግሌዎች ሽምግልናችሁ ለዚህ ቀን ካልሆነ ለመቼም አይሆንምና በአገሩም ሽማግሌ የለም ወይ? መባሉ በሰማይ በምድር ያስወቅሳልና ልጆቻችሁን እንድትመክሩና እንድታስታርቁ ከዛሬ ጀምሮም ለሰላም ጠበቆች ሁናችሁ እንድትቆሙ አበክረን እንጠይቃለን።

በውጭ አገር የምትኖሩም #እናንተ_በሰላም_አገር_እየኖራችሁ ዘመዶቻችሁ በእሳት ሲጠበሱ ዝም ብሎ ማየት ስለማይገባ እስከአሁን ስታደርጉት እንደቆያችሁት ሁሉ አሁንም ለሰላሙ ብርቱ ጥረት እንድታደርጉ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረትና እገዛ እንዲያደርጉ፣ ቤተ ክርስቲያንን የምንመራ ውሉደ ክህነትም መፍትሔ መሆን ሲገባን የችግሩ አካል ሆነዋል እየተባልን ነውና ውስጣችንን አጥርተን ለወገኖቻችን በአስታራቂነት ለመድረስ ጊዜው አሁን ስለሆነ ዛሬ እንድንነሣሣ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። "

ቅዱስነታቸው ዛሬ ባወጡት አባታዊ የሰላም ጥሪ ፤ " አሁን ያለው ችግር ወደ ቀጣይ አመት እንዳይሻገር ገትተነው ቀጣዩን አዲስ ዓመት በሰላም ለመቀበል እንችል ዘንድ ከጉልበት ሳይሆን ከልብ ሽብረክ በማለት እርቅ ይውረድ ! የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ ! ሰላም ይታወጅ ! ምድሪቱንም እናሳርፋት ! " በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia