TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
አንድ ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፣ ህወሓት እና ሀገራት ምን አሉ ?

የኢትዮጵያ መንግሥት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ የፕሪቶሪያው ግጭት የማስቆም ስምምነት ዋና ዉጤት " የጦር መሣሪያ ላንቃ መዘጋቱ " እንደሆነ አሳውቋል።

ሚኒስቴር ከግጭት ማቆሙ ስምምነት በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምትጠቀስበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት የተለየ ሆኗል ብሏል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት መለወጡን የግለፀው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከአየርላንድ እንዲሁም ከአውሮጳ ሕብረት/EU ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲሻሻል ማድረጉን እንደ ማሳያ ገልጿል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ምን አስገኘ ለሚለው ጥያቄም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር " ሰላም አስገኝቷል " ሲሉ ምላሽ ሰጥቷል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ ምንም እንኳን በተደረሰው ስምምነት ግጭት በመቆሙ ሻክረው የነበሩ ግንኙነቶች አሁን መልካቸውን ቢቀይሩም የምልሶ ግንባታ እና የጦርነቱ ሰለባዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ እጥረት መኖሩን አልሸሸገም ሲል ዶቼ ቨለ ዘግቧል።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር

በአሁን ሰዓት ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የስምምነቱ ፈራሚ ህወሓት በየፊናቸው የሰላም ስምምነቱን አንደኛ አመት አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል።

ጊዚያዊው አስተዳደሩ በመግላጫው ላይ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ህዝቡን ለማጥፋት ሲካሄድ የነበረን ዘመቻ እንዲሁም እንደ ብሄር ትግራዋይ እንዲጠፋ የህዝቡ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ከሰዎች ህሊና ሳይቀር እንዲሰረዝ የተጎነጎነ ሴራ እንዲገታ አድርጓል ብሏል።

ስምምነቱ ሁሉም ፍላጎቶች እና ወደ ጦርነት ያስገቡ ጠንቆች በተቻለ መጠን ሰላማዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሊሳካ ይችላል የሚል በር መክፈቱን አመልክቷል።

ስምምነቱ አንድ አመት ቢሞላውም እስከ አሁን ድረስ ነፃ ያልወጣ ህዝብ ነፃ የማውጣት ፣ የተፈናቀለ ወደ ቄየው የመመለስ ፣ ህገ-መንግስታዊና ሉአላዊ የትግራይ ግዛት የማረጋገጥ ጉዳይ ፈፅሞ አልተነካም ፤ አሁንም ህዝቡ መከራ ውስጥ እየኖረ ነው ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመልክቷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያው የሰላም ውል በዓለም ማህበረሰብ ፊት የተፈፀመ ስምምነት እንደመሆኑ መጠን ፣ የዓለም ማህበረሰብ በአፈፃፀሙ ያሉ እንቅፋቶች በማስወገድና የትግራይ ህዝብ ኑሮ ወደ ነበረበት የመመለስ ህጋዊና ሞራላዊ ግዴታውን እንዲፈፅም ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ህወሓት

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ( #ህወሓት ) በፊናው ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ የዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መሰረት መሆኑን ገልጿል።

ለስምምነቱ ተፈፃሚነት አባላቱና ደጋፊዎቹ በማሳተፍ በቁርጠኝነት እየታገለ መቆየቱንና ትግሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

" የስምምነቱ ፈራሚ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በውሉ ላይ የተቀመጡ ወሳኝ መሰረታዊ አበይት ጉዳዮች በአግባቡ አልፈፀመም " ያለው ህወሓት " ይህንንም የዓለም ማህበረሰብ የሚያውቀው ሃቅ ነው " ሲል ገልጿል።

" በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እስከ አሁነ የተገኙት ድሎች በማክበር ፤ የተቀሩት እንዲፈፀሙ የፌደራል መንግስት በውሉ መሰረት ሃላፊነቱ መፈፀም ይገባዋል ፤ ውሉ እንዲፈረም ሚና የነበራቸው ሁሉም አካላት ኢጋድ ፣ የአፍሪካ ህብረት ፣ የአሜሪካ መንግስት ፣ የአውሮፓ ህብረት ፣  ተሰሚነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ተማጓቾችና የሚድያ ተቋማት እንዲሁም የዓለም ማህበረሰብ ሞራላዊና  ፓለቲካዊ ሃላፊነታቸው መወጣት ይገባቸዋል " ሲል ህወሓት በመግለጫው አስገንዝበዋል።

ሀገራት ምን አሉ ?

መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆኑ #የአስር_ሀገራት ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ ለ2 ዓመታት ተካሂዶ በነበረው ግጭት ተሳትፈው የነበሩ ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና አሉ ያሏቸውም ተግዳሮቶች በንግግር መፍትሄ እንዲያገኙ ጥሪ አድርግዋል።
- አውስትራሊያ፣
- ካናዳ፣
- ዴንማርክ፣
- ፊንላንድ፣
- ጃፓን፣
- ኔዘርላንድስ፣
- ኒውዚላንድ፣
- ኖርዌይ፣
- ስውዲን፣
- ዩናይትድ ኪንግደም/ዩኬ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተካሄደ ወዲህ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለማምጣት ያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ስምምነቱ የተፈረመበት #አንደኛ_ዓመት ፣ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች የሚደነቁብት እንዲሁም ደግሞ ተግዳሮቶች እንዳሉ እና የተሟላና አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረቶች በእጥፍ መቀጠል እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚወሠድበት መሆኑን ኤምባሲዎቹ አመልክተዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የጀመረው ደም አፋሳሹ ፣ እጅግ አውዳሚና አስከፊው መነሻውን ትግራይ አድርጎ ወደ አጎራባችን ክልሎች የተዛመተው ጦርነት ከ2 አመት በኃላ ህወሓትና የፌደራል መንግስት በደቡብ አፍሪካዋ የፕሪቶሪያ ከተማ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም በፈረሙት ግጭት ማቆም ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ባካተተ የሰላም ስምምነት ውል ጦርነቱ መቋጫ ማግኘቱ ይታወሳል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።
                  
@tikvahethiopia