TIKVAH-ETHIOPIA
1.48M subscribers
56.4K photos
1.4K videos
202 files
3.83K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#እናት #ኢሕአፓ #መኢአድ

እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ ዛሬ በሰጡት የጋራ መግለጫ መንግሥት በአማራ ክልል ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም ጠይቀዋል።

ፓርቲዎቹ ፤ በሕወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል የተከናወነው ከባድ የእርስበርስ ጦርነት አገርንና ህዝብን ከፍተኛ ጉዳት ላይ መጣሉ አስታውሰዋል።

" ጦርነቱ የትግራይ ፣ የአማራ፣ የአፋር ህዝብን የበለጠ  ጎድቶታል " ያሉት ፓርቲዎቹ " ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ወገኖቻችን  የጦርነቱ ሰለባ ሆነዋል፤ በመቶ ሺ የሚቆጠሩት የአካል ጉዳተኛ ተደርገዋል፡፤ ዜጎች በገዛ ሐገራቸው ተፈናቃይና ስደተኛ ሆነዋል፤ የመሠረተ-ልማት አውታሮችና ተቋማት ወድመዋል " ብለዋል።

ህዝቡ ገና ከጦርነቱ ቁስል አላገገመም ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ ጥቃት መክፈቱን የገለፁት ፓርቲዎቹ " ይህ አይነቱ አካሄድ አገር አፍራሽ በመሆኑ ከወዲሁ ጊዜው ሳይሄድ መንግስት እጁን ሊሰበስብ ይገባል " ብለዋል።

አሁን ላይ ነገሮች በተወሳሰቡበት ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በሚያባብስ መልኩ ወደ አማራ ክልል ሠራዊት አዝምቶ ' ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን መቆጣጠርና ትጥቅ ማስፈታት ' በሚል ሽፋን በየቦታው በከባድ መሣሪያ ጭምር በዜጎች ላይ ተኩስ ከፍቷል ሲሉ ሶስቱ ፓርቲዎች በመግለጫቸው ላይ ገልጸዋል።

" የተረጋጋና አስተማማኝ ሁኔታዎች ሳይፈጠሩ፣ ተቻኩሎ፣ በኃይል ትጥቅ ለማስፈታት መሞከር ሌላ ጦርነት ከመቀስቀስ የተለየ ውጤት የለውም " ሲሉ አስገንዝበዋል።

" ሠላም የተነፈጉና እየተሳደዱ ያሉ ዜጎችን፣ በቅድሚያ ትጥቅ ማስወረድ ለምን አስፈለገ ? " ሲሉ የጠየቁት እነዚህ ሶሶት ፓርቲዎች " ኢትዮጵያ ከተዘፈቀችበት #የጎሰኝነት አረንቋ ሳትወጣ፣ በዘውግ በተደራጁ ሃይሎች በሚመራ መንግሥት የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች ወደ ሌላ ችግር የሚያስገቡ ናቸውና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል " ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ፤ " መንግስት በአማራ ክልል ዉስጥ የጀመረውን ህገ-ወጥ ጥቃት በአስቸኳይ አቁሞ ውይይትን መሰረት ባደረጉ አካሄዶች ብቻ ችግሮችን እንዲፈታ አጥብቀን እናሳስባለን " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

(የፓርቲዎቹ ሙሉ መግለጫ ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia