#Ethiopia

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እምነት የሚጣልበት ቢሮክራሲና በየጊዜው የማይለወጥ የኢንቨስትመንት ሕግ አተገባበር ተግባራዊ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ተገማች፣ የተረጋጋና ሥልጡን የሰው ኃይል የሚመራውና የውጭ ባለሀብቶች ሊተማመኑበት የሚያስችል ከባቢ እንዲፈጠር ቻይናውያን ባለሀብቶች አሳስበዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ውስጥ በፀጥታ ችግር፣ በቢሮክራሲ፣ በብልሹ አሠራርና በሙስና ምክንያት ሥራ መሥራት አልቻልንም የሚል ቅሬታ በብዛት እየተደመጠ መሆኑን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰናል ያሉት የቻይና ባለሀብቶች ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

ባለው የኢንቨስትመንት ማነቆ ላይ የፖሊሲ ምክክር በማድረግ በመንግሥትና በባለሀብቶቹ መካከል ድልድይ በመሆን ይሠራል የተባለለት " አፍሪካ – ቻይና ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት ፋሲልቴሽን " የተሰኘ አማካሪ ቡድን ይፋ ተደርጓል።

የአማካሪ ቡድኑ መሥራች ቻይናዊው ባለሀብት ጉዋን ሹ ምን አሉ ?

በአገር ውስጥ የተሰማራ አምራች ኩባንያ የሚያመርተው ምርት ብቻ ሳይሆን፣ የሚመረተውን የሚጠቀመው ማኅበረሰብ ለሚቀርብለት ምርት መተማመኛ ይፈልጋል ተብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታና አስቻይ ፖሊሲ ያስፈልጋል።

ግልጽ የሆኑ መመርያዎች፣ ሊተነበዩና ተግባራዊ መደረግ የሚችሉ የኢንቨስትመንት ሕጎች ያስፈልጋሉ። ሕጎቹ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ለአንድና ለሁለት ዓመት ብቻ ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ መተማመን የሚፈጥር መልኩ ዋስትና መስጠት አለባቸው።

የውጭ ኢንቨስተሮች ሀብታቸውን በሚያፈሱባቸው አካባቢዎች ባሉ አስተዳደሮች ለንብረታቸው የጥበቃ ከለላ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለንብረታቸው መተማመኛ ያላገኙና የሕጎች አተገባበር መለዋወጥ ያስቸገራቸው ባለሀብቶች ወደ ጎረቤት ኬንያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ሲሄዱ አይተናል።

በሥራ ላይ ያለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወይም ሕግ ተገማችነቱ በግልጽ መቀመጡ ለኢንቨስተሮች መተማመንን ይፈጥራል። መተማመን ሲፈጠር ባለሀብቶች ባሉበት የመቆየትና ኢንቨስትመንታቸውን የማስፋት አቅማቸው ይጨምራል።

በኢትዮጵያ ያለው የግብር ሥርዓት የኩባንያዎቹን ቁመናና አፈጻጸም ግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም በላይ አሠራሩና አወሳሰኑ ግልጽ አይደለም። በዚህም የተነሳ ኢንቨስተሮች እንዴት እምነት አድሮባቸው ሊሠሩ ይችላሉ ?

መንግሥት በአንድ በኩል የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የኃይል አቅርቦትና መሠረት ልማት ለማሟላት ሀብት፣ እያፈሰሰ በሌላ በኩል የሚወጡ ሕጎች ይዘት ተገማችነትና አተገባበር፣ እንዲሁም አሠራሮች ከዓላማው ጋር በልኩ ካልተጣጣሙ ሒደቱ ወደኋላ ይጎትታል።

የባለሙያዎቹ ቡድን የተቋቋመው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱና ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች፣ በኢንቨስትመንታቸው የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ነው።

አንድ ቻይና ኤምባሲ ዲፕሎማት በኢትዮጵያ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸው የታመነበት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ እየለቀቁ ወደ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ሌሎች አገሮች እየተሰደዱ ናቸው ብለዋል፡፡

ይህ የሆነው ተገማች ያልሆኑ ሕጎችና ብልሹ አሠራሮች ከቢሮክራሲ ማነቆ ጋር በመደራረባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህንን አሳሳቢ ችግር ለማስተካከል  የምሁራን ቡድኑ ትልቅ ሚና ይጠበቅበታል ብለዋል።

በየካቲት 2016 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጀምሮ ባለሀብቶች ወደ ሌላ አገር እየተሻገሩ እንደሆነ መስማታቸውን ጠቅሰው፣ ይህ የምሁራን ስብስብ የቻይና ባለሀብቶችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንም ሊጠቅም ይገባል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት አባልና የአማካሪ ቡድኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዳሌ ኦዳ ምን አሉ ፤ " የተማሰረተው ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ለማስተላለፍ ዕገዛ የሚያደርግ ቡድን ነው " ብለዋል።

" በቀጣይ ኢንቨስተሮች ሊያጋጥማቸው የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማመላከትና የፖሊሲ ማማከር ሥራ በማከናወን ቀጣይነት ያለው የቢዝነስና የንግድ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ላይ ጥረት ይደረጋል " ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ተወካይ ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋይናንስ እጥረትና በጦርነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በፀጥታ ችግር የግብር ሥርዓት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

" አንድ ጊዜ ከገቢዎች ቢሮ ስልክ ከተደወለ ተኝቶ ማደር የለም " ሲሉ ተናግረዋል፡፡

" የገቢዎችና የጉምሩክ ሠራተኞች የሚጠቀሙበት ሲስተም በትክክል ለምን አይሠራም ብዬ ስጠይቃቸው አናውቅም ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ ሠራተኞቹ የተረጋጉ አለመሆናቸው አሳሳቢ ነው " ብለዋል፡፡

" ምንም እንኳ ትርፍ ለማግኘት ኢትዮጵያ ብንመጣም አብረን ማደግ እንችላለን፣ በየተቋማቱ ያሉ አሠራሮች ግን ይስተካከሉ " ብለዋል።

የማይገመት አሠራርና ተለዋዋጭ የሕግ አተገባበር ትልቅ ማነቆ በመሆኑ መንግሥት ማስተካከያ ያድርግ ሲሉም አሳስበዋል፡፡ #ሪፖርተርጋዜጣ

@tikvahethiopia