TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#TPLF

ህወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ፤ " ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ " ሲል ውድቅ አድርጎታል።

ህወሓት ባወጣው መግለጫ ፥ " የስራ ኃላፊዎቼ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማካሄድ ሕጋዊ ሰውነታችን እንዲመለስ መግባባት ላይ ተደርሷል " ብሏል።

" በአፍሪካ ህብረት ፓናል ውይይትም ይህ ጉዳይ ተነስቶ ህጋዊ ሰውነቱ መመለስ እንዳለበት ስምምነት ተደርሶበታል " ሲል ገልጿል።

ይህን ተከትሎ " ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነታችን ወደነበረበት እንዲመለስልን ብቻ በሀምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጥያቄ አቅርበናል " ብሏል።

ሆኖም " ቦርዱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች፣ ሌሎች ህጎችና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረሱ መግባባቶች ወደጎን በመተው ጥያቄውን ' በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ' መልሷል " ሲል ገልጿል።

ይህን ተከትሎ ህወሓት " ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ ሆኗል " በማለት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ " አልቀበልም " ሲል አሳውቋል።

" በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ የተካተቱት ዝርዝር ይዘቶች አዲስ በወጣው ማሻሻያ ህግ መሰረት የተቀመጡና ካቀረብነው ጥያቄ ጋር የማይገናኙ ናቸው " ሲልም አክሏል።

" የቦርዱ ውሳኔ ህጋዊ ሰውነቴን ወደነበረበት እንዲመለስ የቀረበውን ጥያቄ የማይመልስ ፤ የነበሩ ውይይቶችን የሚቃረኑ ዝርዝር ይዘቶች የሚጭንብን በመሆኑ አልተቀበልኩትም " ያለው ህወሓት " ጥያቄያችን እስኪመለስ ድረስ የፓርቲው ሕገ ደንብ በሚፈቅድልን መልኩ ተያያዥ ስራዎችን እናከናውናለን " ብሏል።

የፌደራል መንግስቱም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመከሩበት ወቅት ፦

- TPLF እና መሰል ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ አዋጅ መሻሻሉ፤
- አቃቤ ህግ ለምርጫ ቦርድ መጻፍ የነበረበትን ማለትም ስራውን ሰርቶ የሚያጣራውን አጣርቶ በሕጋዊ መንገድ እንዲፈቅድላቸው፤
- የአስፈጻሚውን ስራ 100% መሰራቱን፤
- ፓርቲ ለፓርቲ ፤ የመንግሥት ለመንግሥት ውይይቶች ላይ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እንደተሰጠ፤
- TPLF ምርጫ ቦርድ ሄዶ የሚጠበቅበትን ዶክመንት አሟልቶ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት ፤ ይህን ባያደርግ ምርጫ ቦርድም ካልተቀበለው፤ TPLFን ሕጋዊ ፓርቲ ካላለው ፦
በምርጫ ሊሳተፍ እንደማይችል ፤
መንግሥትም ሊሆን እንደማይችል ይህ ደግሞ ተመልሶ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ፤
- ተመልሶ ጦርነት ውስጥ ከመግባት በተበጀው ሕግ ፤ በተደረሰው ስምምነት ህወሓት የቀረውን ጉዳይ አሟልቶ በሕጋዊ መንገድ ጉባኤ አካሂዶ ፓርቲውን መልሶ ወደ ፖለቲካ ስርዓት መመለስ እንዳለበት መግለጻቸው ይታወሳል።

#Ethiopia #TPLF #TikvahEthiopia

@tikvahethiopia