" ... ወንዶች በትምህርት ሰአት ሁሉ የቀን ስራ በመስራት ርሀባቸውን ለማስታገስ በጥረት ላይ ሲሆኑ ሴቶችም ላልተገባ ችግር ተጋልጠዉ መማር አልቻሉም " - የደቡብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር አደረኩት ባለው ማጣራት በክልሉ ውስጥ ባሉት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ለመማር የተመደቡ ዕጩ መምህራን ሁሉም በሚባል መልኩ  ትምህርታቸውን በፋይናንስ እጥረት በአግባቡ እየተማሩ አይደለም።

ዕጩ መምህራን በ2015 ዓ/ም ወደ ኮሌጆች ሲገቡ ከመንግስት የሚሰጣቸዉ 450 ብር በቂ እንዳልሆነ እየታወቀ ቢጀመርም እስካሁን ሊስተካከልላቸው አልቻለም።

ይህን ችግር በተመለከተ ኮሌጆቹ በቦርድ ደረጃ ያመኑበት ከመሆኑ ባለፈ ማስተካከያ እንዲደረግ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ይሁንና የክልሉ መንግስት ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ በክልሉ በተለያዬ ደረጃ የመምህራንነት ስልጠና ለመዉሰድ ወደኮሌጆች ገብተዉ በትምህርት ላይ የሚገኙ በርካታ ዕጩ መምህራን በችግር እየተጠበሱና ትምህርታቸዉን ትተዉ ወደመጡበት እየተመለሱ መሆናቸዉን የክልሉ መምህራን ማህበር አውቂያለሁ ብሏል።

የመምህራን ማህበሩ ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል ጳዉሎስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ፤ " ከነዚህ ተማሪዎች መካከል አብዛኛዉ ወንዶች በትምህርት ሰአት ሁሉ የቀን ስራ በመስራት ርሀባቸውን ለማስታገስ በጥረት ላይ ሲሆኑ  ሴቶችም ላልተገባ ችግር ተጋልጠዉ መማር አልቻሉም " ብለዋል።

" በመሆኑም ተማሪዎች በ450 ብር በልተዉና ጠጥተዉ እንዲሁም ሌሎች ወጭዎችን ሸፍነዉ  መማር አይችሉምና የክልሉ መንግስት በተለይም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ባስቸኳይ ችግራቸዉን ይፈታላቸዉ ዘንድ ማህበሩ በደብዳቤ ሁሉ ጠይቋል " ሲሉ ተናግረዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ስለምን ተማሪዎቹ በዚህ ልክ እስኪሰቃዩ ድረስ መፍትሄ አልተፈለገም ? በማለት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

ምላሽ ሲሰጥ ምላሹን የምናካትት ይሆናል።

#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia