“ ... ለኩራዝ የሚጠቀሙበት ነዳጅ በግልጽ ሁኔታ በችርቻሮ፣ የአረቄ በርሜል በከፍተኛ መጠን የሚሸጥበት ቦታ ነው ” - አቶ ንጋቱ ማሞ

በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አቃቂ ገበያ ማዕከል ትላንት ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ የእሳት አደጋ አጋጥሞ ነበር።

በሰዎች ላይ ጉዳት ያልደረሰ ሲሆን 6 ሙሉ ለሙሉ፣ 10 በከፊል፣ በድምሩ 16 ሱቆች እንደተቃጠሉ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የአደጋው መንስኤ ታውቋል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ፣ “ ፓሊስ ምርመራ እያደረገ ነው። በንብረት ላይ የደረሰን ጉዳትም ባለንብረቶቹን ፓሊስ አጣርቶ ምርመራ እያደረገ ነው ” ብለዋል።

ገበያ ማዕከሉ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብሎ የተለዬ እንደሆነ ፣ ለአደጋ የተጋለጠባቸውን ጉዳዮች ለሚመለከታቸው አካላት ቢያቀርብም የማስተካከያ እንዳልተደረገ ኮሚሽኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ ቲክቫህ ኢትዮጵያም ተሰጥቶ የነበረው ማስጠንቀቂያ ምን እንደነበር ኮሚሽኑን ጠይቋል።

አቶ ንጋቱ በሰጡት ምላሽ፣ “ ለገበያ ማዕከሉ አክሲዮን ማኅበራት አደጋ ውስጥ ናችሁ። ገበያ ማዕከሉ በዘመናዊ መልክ ይገንባ ንብረታችሁ ለአደጋ ሰለባ እንዳይሆን የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበናል። በግልባጭ ደግሞ ለወረዳውም ” ብለዋል።

“ ቤቶቹ በቀላሉ ሊቀጣጠሉ ከሚችሉ ግብዓቶች (ቆርቆሮ በቆርቆሮ) የተገነቡ ናቸው። መፍትሄ ብለን ያቀረብነው ገበያ ማዕከሉ ዘመናዊ ሆኖ እንዲገነባ ነው። ዘመናዊ ስንል እሳትን ሊቋቋም ከሚችል እንደ ድንጋይ ከመሳሰሉ ግብዓቶች እንዲሰራ ነው ” ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ንጋቱ፣ “ ከገጠር የሚመጡ ሰዎች ለኩራዝ የሚጠቀሙበት ነዳጅ በግልጽ በችርቻሮ፣ የአረቄ በርሜል በከፍተኛ መጠን የሚሸጥበት ቦታ ነው” ብለዋል።

“ ንግዱ ዘርፍ፤ ዘርፍ ያስፈልገዋል። በጎን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እየተሸጡ፣ በጎን ደግሞ የካቲካላ ንግድ በፍጹም ምንም አይነት ህብረት የላቸውም ” ነው ያሉት።

የገበያ ማዕከሉ በተደጋጋሚ አደጋ እንደደረሰበት አስታውሰው፣ አደጋ ቢያጋጥም እንኳ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ ለማስገባት ምቹ ባለመሆኑ፣ በውስጡ የሚከናወኑ የንግድ ዘርፎች የተደበላለቁ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት አሁንም ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia