#Ethiopia

ዛሬ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ፤ በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መምከሩን አሳውቋል።

ይህ ተከትሎ ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል።

በዚህ መግለጫ ፦
- ስለ ሀገራዊ ምክክር
- ስለ ሽግግር ፍትሕ
- ከመንግሥት ውጭ ታጥቀው ስለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች
- ስለ ተሃድሶ ኮሚሽን
- ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት
- ስለ ህወሓት ታጣቂዎች
- ስለ ተፈናቃዮች መመለስ

...ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተውበታል።

ምክር ቤቱ፥ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሀገረዊ ምክክር ኮሚሽን በክልል ደረጃ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ ይጀምራል ብሏል።

ሀገራዊው የምክክር ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተስፋ ይደረጋል ሲል ገልጿል።

ም/ቤቱ፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መፅደቁን አስታውሷል።

እንደ አግባብነቱ፦
° የወንጀል ምርመራ እና ክስ
° እውነት ማፈላለግ
° ዕርቅ
° በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምሕረት
° ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያ እንደ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች በሀገራችን ተግባራዊ ይደረጋሉ ብሏል።

" የመንግሥት አንዱ መብት በብቸኝነት ኃይልን መጠቀም " መሆኑን ገልጾ በሀገራችን በተወረሰ የፖለቲካ ስብራት የተነሣ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል ብሏል።

የሀገሪቱን ሰላም የጸና ለማድረግ፣ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው፣ የተሐድሶ ሂደት ውስጥ መቀላቀል አለባቸው ብሏል። " የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ መፍታት ይችላሉ " ሲል ገልጿል።

ለዚህም የተሐድሶ ኮሚሽን ተቋቁሟል። ዓላማውም፦
° መሣሪያ ማስፈታት
° የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ ማድረግና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ነው ብሏል።

መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበር ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጋር የተናበበና የሚመጋገብ እንዲሆን ኃላፊነቱን ይወጣል ብሏል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጦርነትን በፖለቲካዊ መፍትሔ የመቋጨት ባህል አምጥቷል ሲል ገልጿል።

የሰላም ስምምነቱ ለትውልድ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክትን ከቂም ጋር ላለማውረስ የተደረገ ውሳኔ እንደሆነ ገልጿል።

የሰላም ስምምነቱ እስካሁን ብዙ ውጤት እና እፎይታ ቢያስገኝም ቀሪ ሥራዎችም አሉ ብሏል።

በተለይ በስምምነቱ መሠረት " የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው " ሲል ገልጿል።

የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ እልባት ለመስጠት እንዲቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ መደረግ አለበት ብሏል።

" ካለፈ ስሕተተ አለመማር የመጀመሪያውን ስሕተት ከመሥራት የባሰ ነው " ያለው ም/ቤቱ፤ ካለፈው ስሕተታቸው ሳይማሩ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ አሉ ሲል ጠቁሟል።

እነዚህን ሁሉም ተባብሮ አደብ ማስገዛት ይኖርበታል ብሏል።

" ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት ሕግ የማስከበር ሥራ የሚኖረውን አስከፊ ውጤት ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባል" ሲል አሳስቧል።

ም/ቤቱ፤ መንግሥት በትግራይ ክልል ብዙ ርቄት ሄዶ ቁስልን ለመሻር የሚያስችል ሥራ እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።

" ይሄ ግን መንግሥታዊ ኃላፊነት እንጂ ፍርሃት ተደርጎ መወሰድ የለበትም " ብሏል።

" በፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነትና በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንደ ሀገር የሚኖረው አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ክልሎች በክልል ከፖሊስ እና ሚሊሺያ ያለፈ የታጠቀና የተደራጀ ሠራዊት ሊኖራቸው አይችልም፤ አይገባምም " ብሏል።

በዚህ መሠረት ትጥቅ መፍታትና ተያያዥ ሂደቶች በተሐድሶ ኮሚሽኑ ዕቅድ መሠረት በፍጥነት ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ብሏል።

ያንብቡ👇
https://telegra.ph/Tikvah-Ethiopia-04-24

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia