TIKVAH-ETHIOPIA
#ትግራይ የኤርትራ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው የኢሮብ የኢትዮጵያ የትግራይ አከባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ማስጠንቀቅያ ሲሰጥ የሚያሳይ የቪድዮ መረጃ የኢሮብ ብሄረሰብ ተወላጆችን አሰቆጥቷል። የኤርትራ ሰራዊት ተወካይ የኢሮብ ተወላጆች ስብስቦ ማስጠንቀቅያ ሲሰጥ የሚያሳየው የቪድዮ መረጃ በማህበራዊ የትስስር ገፆች በመሰራጨት ላይ ሲሆን በክልሉ ሚድያዎችም ሽፋን ሰጥተውታል። የቪድዮው የድምፂ ቅጂ ምን ይላል ?…
#ትግራይ

የኤርትራ ሰራዊት ከሶስት የኢትዮጵያ የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ወረዳዎች ' 93 ወጣቶች ' አግቶ መሰወሩን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ገልጹ።

እገታው የተፈፀመው ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል ከኤርትራ ከምትዋሰንባቸው የዛላንበሳ ከተማ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች ላይ ነው ተብሏል።

ይህን የተገለፀው የከተማ እና የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች ከኤርትራ ድንበር በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው የዓዲግራት ከተማ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች (AU military attaches) ባካሄዱት ውይይት ነው። 

የዛላአንበሳ ከንቲባ መምህር ብርሀነ በርሀና ፣ የጉሎመኻዳ ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቶም ባራኺ በጋራ ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኃላ :- 

በአከባቢያቸው የተለወጠ የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩ ፤

ጦርነቱ ተከትሎ የተፈጠረው ችግር እንዳልተፈታ፤

የኤርትራ ሰራዊት የዛላአንበሳ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ፤

ከዛላኣንበሳ ከተማ መግብያ በቅርብ ርቀት ዝባን ሑፃ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ኬላ አቋቁሞ ፍተሻ እንደሚያካሂድ ፤

የኤርትራ ሰራዊት ከዛላኣንበሳ ከተማ 15 ፣ በቁጥጥሩ ስር ከሚገኙ የጉሎመኻዳና የኢሮብ ወረዳዎች የተለያዩ ቀበሌዎች 78 ባጠቃላይ 93 ወጣቶች አግቶ የወሰዳቸው ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ  አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች 10 ቀበሌዎች የሚኖር ህዝብ እርዳታ ጨምሮ የጤና የትምህርት እንዲሁም ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶች እንደማያገኝ አስተዳዳሪዎቹ ለአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በዝርዝር አስረድተዋል።

በስብሰባው ወቅት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች መሳተፋቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የሀገር መከላከያ ሚንስትሩ ዶክተር አብራሃም በላይ በየካቲት 2016 ዓ.ም የመጨረሻው ሳምንት ላይ በትግርኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ፥ "  የሻብዕያ ሰራዊት " ብለው የገለፁት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መሬት ስለመውጣት ጉዳይ ፤

"  ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በፊት በበርካታ የትግራይ አከባቢዎች የሻዕብያ ሃይል ገብቶ ነበር ፣ ከስምምነቱ በኋላ እንዲወጣ ተደርጓል ፣ አሁንም የተቀሩ ቦታዎች ካሉ ቦታዎቹ እና ቀበሌዎች ከፌደራልና ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ቡድን በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብና መፍትሄ እንዲሰጠው እየሰራን ነው ሁሉም ልክና መስመር ይይዛል " ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

መረጃው በመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው የተዘጋጀው።
                                                
@tikvahethiopia