#ትግራይ

የኤርትራ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው የኢሮብ የኢትዮጵያ የትግራይ አከባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ማስጠንቀቅያ ሲሰጥ የሚያሳይ የቪድዮ መረጃ የኢሮብ ብሄረሰብ ተወላጆችን አሰቆጥቷል።

የኤርትራ ሰራዊት ተወካይ የኢሮብ ተወላጆች ስብስቦ ማስጠንቀቅያ ሲሰጥ የሚያሳየው የቪድዮ መረጃ በማህበራዊ የትስስር ገፆች በመሰራጨት ላይ ሲሆን በክልሉ ሚድያዎችም ሽፋን ሰጥተውታል።

የቪድዮው የድምፂ ቅጂ ምን ይላል ?

"... እናንተ ህዝብ ናችሁ። የምትኖሩበት መሬት ደግሞ የኤርትራ ነው። ኤርትራውያን ከሆናችሁ ለዚሁ አከባቢና መሬት ተገዢ እንዲሁም እዚህ ላለው ሰራዊት የማገዝ ግዴታ አለባችሁ።
አገራዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታም አለባችሁ። በትወልዱም በትጠሉም አንድ የኤርትራ ዜጋ የሚያሳልፈውን ህይወት  ልታልፉ ግድ ይላል።

አንድ ሰው ከዚህ አከባቢ ወደ አገራዊ አገልግሎት ከሄደ ለኤርትራ አገሩ ብሎ ነው የሚሄደው። ስለዚህ እያንዳንዳችሁ አገራዊ አገልግሎት እንደሚመለከታችሁ ማወቅ አለባችሁ።  አባቶች የሃይማኖት መሪዎች ስሙ ከመካከላችሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ካለ የኤርትራ መንግስት እዚህ አስገድዶ አያኖረውም። ወደ ኢትዮጵያ የመሄድ መብት አለው። የኤርትራ መሬት ደግሞ ኤርትራውያን ይኖሩበታል።

ወደ አገራዊ አገልግሎት መሄድ ካለብህ ትሄዳለህ፤ ረሃብ ካለ እንደ ሌላው ኤርትራዊ ትራባለህ።  በቃ ተካፍለህ ትኖራለህ። ላንተ ተብሎ የሚደረግ የተለየ ነገር የለም። ልቅ የሆነ አካሄድ ነው የቆየው ይህ ከአሁን በኃላ አይቀጥልም። " ሲል ያስጠንቅቃል የኤርትራ ሰራዊት ተወካዩ።

ቪድዮውን የተመለከቱ የኢሮብ ብሄረሰብ ተወላጆች የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርና የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ከጥፋት እንዲታደግዋቸው ተማፅነዋል።

ብርሃን ወዲ ኢሮብ የተባለው የብሄረሰቡ ተወላጅ በሰጠው አስተያየት " ... አራት ዓመት ሙሉ በሁለት ተከፍለን ኮምፓስዋ እንደጠፋት መርከብ ሆነን ተሰፋችን ጨልሞብናል።  ብሄረሰባችን እየጠፋ አረ የሰሚ ያለህ.." ሲል ምሬቱን ገልጿል።

የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ፦
- የዛላኣንበሳ ከተማ
- በጉሎመኸዳ ወረዳ ማርታ ፣ አዲስ ተስፋ ፣ አዲስ ዓለም ፣ ሸዊት ለምለምና ሰበያ
- በኢሮብ ወረዳ እንዳልጌዳ ፣ ወርዓትለ ዓገረ ሎኽማና ዓሊቴና የተባሉ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በታሕታይ ኣድያቦ የኩናማ ማህበረሰብና ሌሎች የሚኖሩባቸው ገማህሎ ፣ አደመይቲ ፣ የባድመ ከተማና አከባቢው ፣ ዓዲ ፀፀር ፣ ለምለም ሸዊት ፣ ሸምበሊና ፣ መንጠብጠብ ፣ ዓዲ ኣሰር ፣ ሰየምቲ አድያቦ እንደሁ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

መረጃው በመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል የተዘጋጀ ነው።
                                               
@tikvahethiopia