" 4 አባቶች ተገድለዋል " - ቤተክርስቲያኗ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፤ ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው ጥታዊው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም " እራሱን ' ኦነግ ሸኔ ' ብሎ የሚጠራው ቡድን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ 4 አባቶችን ገድሏል " ሲል አሳወቀ።

ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት ታጣቂዎቹ 3 አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ከወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያርግበት ወቅት የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ አባቶችን በመያዝ ፦
1. የገዳሙ መጋቢ አባተክለማርያም ዐሥራት
2. የገዳሙ ጸሐፊ አባ ኪዳነ ማርያም ጥላሁን
3. የገዳሙ የመጽሐፍ መምህርና ቀዳሽ አባ ገ/ማርያም አበበ
4. በአመክሮ የሚኖሩ መናኝ ኃይለማርያም ወልደሰንበት የተባሉት የገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች እንደተገደሉና አብረው ከነበሩት አንድ አባት ብቻ ማምለጥ መቻላቸውን እንደተረዱ የገዳሙ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የገዳሙ የሥራ ኃላፊዎች ቡድኑ ከዚህ ቀደም ገዳሙን በመዝረፍ ለከፋ ችግር አጋልጦት መቆየቱን አስታውሰው ገዳሙ ጸጥታውን የሚያስከብረበት መሣሪያዎች በቡድኑ በመወረሳቸው ምክንያት ለከፋ የጸጥታ ችግር መጋለጡን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ገዳማውያኑ በስጋት ላይ መሆናቸውንና የመንግሥት የጸጥታ አካላትን እገዛ እንደሚሹ አስታውቀው መረጃውንም በየደረጃው ለሚገኙ የሀገረ ስብከቱና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ መረጃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያና የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት ነው።

@tikvahethiopia