" ከሶማሊያ ጋር የመዋጋት ፣ የመጣላት ፍፁም ፍላጎት የለንም " - ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር #የመዋጋትም ሆነ የመጣላት ፍላጎት እንደሌላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ዶ/ር ዐቢይ ይህን ያሉት ለፓርቲያቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባቀረቡት ገለፃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ " የምንከተለው የዲፕሎማሲ ጉዟችን ክብርንና ጥቅምን ማስከበር ላይ ያተኮረ ነው። " ብለዋል።

" ሶማሊያ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ወንድም ዘመድ ጎረቤት ናት፤ ባለፉት 10 ዓመታት በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሶማሊያ ውስጥ የሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የህይወት ዋጋ ከፍለዋል። " ሲሉ ገልጸዋል።

" ማንም ሀገር በዓለም ላይ ኢትዮጵያ የከፈለችውን ያህል የከፈለ የለም " ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ " አግዛለው ብሎ መፎከርና ሄዶ መሞት ይለያያል " ብለዋል።

" ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ህዝብና መንግስት ጋር ለመጣላት ለመዋጋት ፍጹም ፍላጎት የላትም " ሲሉም ተደምጠዋል።

" አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግስት በሶማሊያ አንድነት የሚታማ መንግስት አይደለም " ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ፤ " ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ሶማሊያዊያን አንድ እንዲሆኑ በንግግር ሳይሆን በተግባር የሰራ መንግስት ነው " ብለዋል።

" ከልባችን አንድ እንዲሆኑ ስለምንፈልግ የቀድሞው ፕሬዜዳንት ፈርማጆ ስልጣን ላይ እያሉ ከሱማሌላንድ ፕሬዜዳንት ቢሂ ጋር ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ ለማገናኘት በተደረገ መኩራ እንዲገናኙ አድርገን ውይይት ተደርጓል ፤ ሶማሊያ እና ኬንያ በድንበር ጉዳይ ሲጣሉ አለም ሲንጫጫ ፕሬዜዳንት ፈርማጆን ኬንያ ወስደን ከወንድማቸው ከፕሬዜዳንት ኡሁሩ ጋር እንዲነጋገሩ ጥረት አድርገናል፤ ለምን ? የነሱ ሰላም የኛ ስለሆነ " ሲሉ አስረድተዋል።

" ሶማሊያ እንደ ግጭት ሰፈር አድርጎ የመጠቀም ፍላጎት ከብዙ ኃይሎች ይነሳል፤ እኛ ለዓለም ህዝብ የቀይ ባሕር 'አክሰስ' ጥያቄያችን ህጋዊ መሆኑን አሳይተናል። ዓለም በሙሉ ይገባቸዋልኮ ግን፣ ግን ነው የሚለው ፤ የኛ ፍላጎት ባሕርን አክሰስ ማድረግ ብቻ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

" ከኢትዮጵያ መውሰድ ሲሆን ችግር የለውም፤ ለኢትዮጵያ መስጠት ነው ነውሩ ፤ ዲፕሎማሲያችን እንደዚያ ነው፤ አሁን መልኩን እየቀየረ ነው " ብለዋል።

" በእኛ እና ሶማሊያ መካከል ችግር ይፈጠራል ብዬ ባላስብም " ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ " በሕዝቦች መካከል ጥላቻ እንዳይፈጠር ቁርሾ እንዳይፈጠር በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ውጫዊ አክተር በሚያሰክን መንገድ መምራት ይጠይቃል " ሲሉ ተናግረዋል። #PP

@tikvahethiopia