#መልዕክት

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዜዳንት ቄስ ዶ/ር ዮናስ ይገዙ ፦

" . . . በዓለማችን #የሰላም ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር እግዚአብሔር በራሱና በሰው ልጆች መካከል፤ እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል የነበረውን ጥል አስወግዶ ሰላምን ለማውረድ ያደረገውን ማሰብ ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ምሳሌነት ለመከተል መወሰንን ይጨምራል፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ  በአገራችን የሚታዩት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ተወግደው ሰላም እንዲሰፍንና አገራዊ አንድነት እንዲረጋገጥ መላው የአገራችን ሕዝቦችና ሕዝበ ምዕመኑ እንደወትሮው የእግዚአብሔር አምላካችንን ጣልቃ ገብነት ተግተው መለመንና አቅም የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ለሚነሱ  አዳዲስ ግጭቶችም ሆነ ለሰነበቱት አለመግባባቶች ዋነኛ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው #በሰላማዊ_መንገድ  ተቀራርቦ መመካከርና መነጋገር ብቻ እንደሆነና የትጥቅ ፍልሚያ ሰላም ሊያመጣ እንደማይችል ታምናለች፡፡

የሰው ልጆች አብረው በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ የሰላም ወንጌልን ትሰብካለች፡፡ ከሰላም እጦት የተነሳ የሚፈጠረውን ሞትና እንግልት ትቃወማለች፤ በበኩልዋም ችግሮች ሲፈጠሩ ለእርቅና ለሰላም ጥረቶች የምትጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆንዋንም በየጊዜው ስትገልጽ  ቆይታለች፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱም ራስዋ በየጊዜው በተለያዩ ታጣቂ ኃይላት መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ቀጥታ ተጠቂ የሆነችባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡

ለዚህም በቅርብ ጊዜ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ላይ በነበሩ ንጹሐን ምዕመናኖቻችን ላይ  የደረሰው የጅምላ ግድያ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በጊዜው ድርጊቱን ከመቃወምና ከማውገዝ ባሻገር ሁኔታውን አስመልክቶ ክትትል እንዲደረግና ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ጥሪ ማድረግዋ የሚታወስ ነው፡፡

አያይዛም እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ላንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ የትጥቅ ፊልሚያዎችን አቁሞ ለሰላማዊ ምክክር ዕድል መስጠት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም አስታውሳለች፡፡

አሁንም ይህንኑ ጥሪ ደግማ ደጋግማ ማሰማትዋን ትቀጥላለች፤ ምዕመናንዋንም በዚሁ መስመር በጸሎት በማትጋት ላይ ትገኛለች፡፡ በእግዚአብሔር ተስፋ አይቆረጥም፤ እርሱ የምህረት ፊቱን ይመልስልናል፤ ሰላሙንም በእርግጥ ይሰጠናል፡፡ "

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia