#Hawassa #ጤና

በሀዋሳ ከተማ በሚገኝ " ፓነሲያ ሆስፒታል " 2,094 የሀሞት ከረጢት ጠጠር በቀዶ ህክምና ከአንዲት 40 ዓመት ሴት በሆስፒታሉ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት በዶ/ር ፀጋዬ ቸቦና በስራ ባልደረቦቻቸው የቀዶ ህክምና ቡድን አማካኝነት ወጥቷል።

ጉዳዩን በተመለከተ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡት ዶ/ር ፀጋዬ ፤ ይህ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ በቁጥር ብዛት የመጀመሪያ የሆነና እስከዛሬ ያልተመዘገበ ከ2,094 በላይ ቁጥር ያለው የሀሞት ከረጢት ጠጠር (Symptomatic Multiple Cholelithiasis) ነው ብለዋል።

ቀዶ ህክምናው 2 ሰዓታት ከ30 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን በተሳካ ሁኔታ ማስወገድ መቻሉን አስረድተዋል።

የሀሞት ከረጢት ጠጠሮቹ በቀዶ ህክምና ቡድን የተቆጠሩ ሲሆን ጠጠሮቹን ለመቁጠር ከ45 ደቂቃ በላይ መፍጀቱን ዶ/ር ፀጋዬ ገልጸዋል።

የ40 ዓመት እድሜ ያላት ታካሚዋ ለ3 ዓመታት የቆየ በአብዘኛው ጊዜ ቅባታማ ምግቦችን ከተመገቡ በሗላ የሚከሰት ለረጅም ሰዓታት የሚቆይ ፦
- የሆድ የላይኛው ቀኝ ክፍል የመውጋትና የማቃጠል ህመም ፣
- ምግብ ያለመፈጨት ችግሮች ፣
- የቀኝ ትከሻ እና የጀርባ ህመም ስለነበራቸው ነው ወደ ሆስፒታሉ ያቀናችው።

አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገላት በኃላ ነው የሀሞት ከረጢት ጠጠር (Symptomatic Cholelithiasis) እንዳለባቸው በመታወቁ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋት የተነገራት።

የቀዶ ህክምናው ውስብስብነት ላይ ውይይት ከተደረገና በቂ መረጃ ከተሰጣቸው በኋላ ተጨማሪ ስምምነት ፈርመው ነው ቀዶ ህክምናውን ለማደረግ የወሰኑት።

የታካሚዋ ቀዶ ህክምና ከባድና ውስብስብ ያደረገው ምንድነው ?

* በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሆስፒታሎች ሶስት ጊዜ (3x) የእንቅርት ዕጢ/ካንሰር ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው መሆኑ
* ከቀዶ ህክምናው በሗላ በታካሚዋ ላይ የነበረባቸው ተጓዳኝ የጉሮሮ ነርቭ  ጉዳት ፤
* የድምፅ ለውጥ/የድምፅ ኃይል መቀነስ እና አልፎ አልፎ የነበረባቸው የአተነፋፈስ ችግሮች የድህረ- ቀዶ ህክምናው ፅኑ እንክብካቤ እና እርዳታ ውስብስብ አድርጎታል።

ምንም እንኳን ቀዶ ህክምናው ታካሚዋ በነበረባቸው  ተጓዳኝ ችግሮች ውስብስብ ቢሆንም በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ቡድን ቅንጅት ቀዶ ህክምናው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።

🔹በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንሳዊ መጽሔቶች እና ምርምር ሪፖርቶች ላይ ከፍተኛ ብዛት ያላቸው የሀሞት ከረጢት ጠጠር በህንድ በሪከርድነት ተይዞ ይገኛል።

🔹በአፍሪካ ጆርናሎችና ሳይንሳዊ ወረቀቶች ወስጥ በዚህ ደረጃ ብዛት ያላቸው የሀሞት ከረጢት ጠጠር ተመዝግቦ አልተገኘም። እስካሁን ባሉ መረጃዎች በኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ጆርናሎች ላይ 146 የሃሞት ጠጠር ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቦ ይገኛል።

በፓነሲያ ሆስፒታል-ሀዋሳ በቀዶ ህክምና የወጣዉ ከ2,094 በላይ ብዛት ያለው የሀሞት ከረጢት ጠጠር በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ በቁጥር ብዛት በሳይንሳዊ መጽሔቶች እና ምርምር ወረቀት ሪፖርቶች ላይ አዲስ ሪከርድ ሆኖ ሊመዘገብ የሚችል መሆኑን ዶ/ር ፀጋዬ ቸቦ ተናግረዋል።

ለጥንቃቄ . . .

በአብዘኛው ጊዜ ቅባታማ ምግቦችን ከተመገቡ በሗላ የምከሰት ለረጅም ሰዓት የሚቆይ የሆድ ህመም ካላ ፦
☑️ በሆድ የላይኛው ቀኝ ክፍል ድንገተኛ የመውጋትና የማቃጠል ህመም ፣
☑️ በቀኝ ትከሻ ላይና በትከሻ መሳቢያዎች መካከል የጀርባ ህመም፣
☑️ የሆድ መነፋት ስሜት እና ምግብ ያለመፈጨት ችግሮች ካሳየና ካለዎት ፤ ይህ የሀሞት ከረጢት ጠጠር ህመም (Symptomatic Cholelithiasis) ምልክት ሊሆን ስለምችል ባፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ማቅናት ያስፈልጋል።

@tikvahethiopia