TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ቤቲንግ

የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ሲስተም የሚሰጡ ድርጅቶች ፍቃድ ለሌላቸው የውርርድ ቤቶች ሲስተም እየሰጡ መሆኑን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።

የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፤ የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ሲስተም የሚሰጡ ድርጅቶች ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ህጋዊ ፍቃድ ላላገኙ አካላት የመወራረጃ ሲስተም በመስጠት ህገወጥ ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ፤ ህገወጥ የውርርድ (ቤቲንግ) ቤቶች እየተበራከቱ የመጡት ውርርዱን እንዲሰራ የሚያደርገውን ስርዓት (system) የስፖርት ውርርድ ሲስተም ሰጪ ድርጅቶች ፍቃድ ለሌላቸው የቤቲንግ ቤቶች እየሰጡ በመሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል።

" በዚህ ምክንያት የስፖርት ውርርድ መመሪያው እየተሻሻለ ነው " ያሉ ሲሆን " ሲስተሙን የሚሰጡ ድርጅቶች ለአንድ ሲስተም ለሚፈልግ ግለሰብ ሲስተሙን ከመስጠታቸው በፊት የብሄራዊ ሎተሪ ፈቃድ አለህ ወይ ? ብለው ማረጋገጥ አለባቸው " ብለዋል።

" ፍቃድ የሌላቸው በቀላሉ ሲስተሙን የሚያገኙ ሰዎች ከቅርንጫፍ ስታንዳርድ እና ከኛ ቁጥጥር ውጪ የቤቲንግ ቤቶችን እየከፈቱ ነው " ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ይህ በህግ ስርዓት ላይ እንዲገባ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

" ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሲስተም ፕሮቫይድ የሚያደርጉ ድርጅቶች በስፖርት ውርርድ መመሪያ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የውርርድ ቤቶች ቅርንጫፍ ከመከፈታቸው በፊት በመመሪያው መሰረት ስለመከፈቱ እንዴት ታጣራላችሁ ? የሚል ጥያቄ አንስቷል።

አቶ ቴዎድሮስ ፤ በቁጥጥር ሰራተኞቻቸው በኩል ቅርንጫፍ ከመከፈቱ በፊት መመሪያውን ተከትሎ ስለመከፈቱ ቀድመው ሄደው እንደሚያዩ አስረድተዋል።

ፍቃድ የሌላቸው እና ሲስተሙን በቀላሉ የሚያገኙ ሰዎች በየቦታው ህገወጥ የውርርድ ቤቶችን እየከፈቱ መሆኑን በመጠቆም በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች ይሄ ችግር በስፋት መኖሩን ጠቁመዋል።

በቅርቡ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር መመሪያውን ባልተከተሉና ህገወጥ የውርርድ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ ፤ በክልል ከተሞች የተሰራው የቁጥጥር ስራ አመርቂ ውጤት እንዳልታየበት በመጥቀስ " አዲስ አበባ ላይ እየታየ ያለውን መልካም ውጤት በክልሎች ለመድገም እንሰራለን " ብለዋል።

መረጃው በአ/አ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ተዘጋጅቶ የተላከ ነው።

@tikvahethiopia