TIKVAH-ETHIOPIA
#ETHIOPIA #Eurobond ኢትዮጵያ የቦንድ ብድር ወለድ በወቅቱ ያልከፈለችው ለምንድነው ? ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ ሰኞ ዕለት መክፈል የነበረባትን ወለድ እስካሁን አልከፈለችም። የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለሽያጭ የቀረበው ከ9 ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም ነበር። ኢትዮጵያ ይህንን ቦንድ ሸጣ ከገዢዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ያገኘች ሲሆን ብድሩ የሚመለሰው…
#Update

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ ወለድን በቀነ ገደቡ መክፈል ባለመቻሏ ዕዳቸውን መክፈል ካልቻሉ አገራት ተርታ እንደተመደበች ሮይተርስ የዜና ወኪል አስነብቧል።

ኢትዮጵያ ትናንት ሰኞ ታኅሳስ 15/ 2016 ዓ.ም. መክፈል የነበረባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር ባለመክፈሏ ዕዳዋን መክፈል ያልቻለች ሶስተኛዋ የአፍሪካ አገር መሆና መመዝገቧ ተገልጿል።

ከ10 ዓመት በፊት በታኅሣሥ 2007 ዓ.ም. የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ሽያጭ አድርጋ ላገኘችው ብድር የወለድ መክፈያ ጊዜያው ከሁለት ሳምንት በፊት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ነበር።

ከመክፈያ ጊዜው ቀነ ገደብ በኋላ የነበረው የ14 ቀናት የእፎይታ ጊዜም እንዲሁ ተጠናቀቋል።

ከዚህ ቀደም መንግስት ወለዱን እንደማይከፍል ማስታወቁ ይታወሳል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የማሻሻያ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሂንዣት ሻሚልም ፤ ክፍያው አለመፈጸሙን እና የሚከፈል አለመሆኑንም ማረጋገጣቸውን ብሉምበርግ ዛሬ ማለዳ ዘግቧል።

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዕዳቸውን መክፈል የማይችሉ (Sovereign default ውስጥ ከገቡት) ሁለት የአፍሪካ አገራት ጎራ ተሰልፋለች። ዕዳቸውን መክፈል የማይችሉ የተባሉት ሁለት የአፍሪካ አገራት #ጋና እና #ዛምቢያ ናቸው።

ገንዘብ ሚኒስቴር ከጥቂት ቀናት በፊት በዚህ ጉዳይ በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ዕዳዋን የማትከፍለው፤ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ እጥረት ሳለልባት ሳይሆን ሁሉንም አበዳሪዎች " በእኩል ለማስተናገድ " በሚል መሆኑን ተናግሯል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋም ከቀናት በፊት ከፋና ቴሌቭዢን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ይህንን የክፍያ ጉዳይ አንስተው ነበር።

ዶ/ር ፍፁም ምን አሉ ?

- ኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ወለድንያልከፈለችው የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ችግር ስላለባት አይደለም።

- በዓመት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ከውጭ ለምናስገባው ዕቃ የምንከፍል ሀገር ነን ስለዚህ 30 ሚሊዮን ዶላር [ገደማ] ገንዘብ ተቸግረን አይደለም ያልከፈልነው ኢትዮጵያ እንዲያውም ብድሯን በጣም በመክፈል የምትታወቅ አገር ናት በችግር ውስጥም ቢሆን።

- ወለዱ ያልተከፈለው ሁሉም አበዳሪ እና ተበዳሪ ተመሳሳይ አይነት አያያዝ ነው ሊያዝ የሚገባው በሚል ምክንያት ነው።

መረጃውን ቢቢሲ አማርኛ አገልግሎት ሮይተርስ እና ብሉምበርግን ዋቢ በማድረግ ነው ያስነበበው።

@tikvahethiopia