#አክሱም

የአክሱም ህዳር ፅዮን በዓልና የቱሪስት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ? 

አክሱም ከተማ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም አመታዊ የህዳር ፅዮን በዓለ ንግስ ታከብራለች።

አክሱምና ዙሪያዋ ለአገር ውስጥና ውጭ  ጎብኚዎች የሚማርኩ በርካታ ቅርሶች የሚገኙባት በኢትዮጵያ ካሉ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዷ ነች።

የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ከአውዳሚው ጦርነት በኃላ የአክሱምና ዙሪያዋ የቱሪስት እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለመታዘብ ቦታው ድረስ ተጉዞ ነበር።

ከቱሪስት እንቅስቃሴ አኳያ የሚመለከታቸው አካላት አነጋግሮ እንዲሁም የህዳር ፅዮን በዓለ ንግስ ቀድመ ዝግጅት ምን እንደሚመስል ተከታትሏል።
 
አቶ ኪዲ ተጠምቀ በአክሱም ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የቱሪስት ማእከል አስተባባሪ ናቸው።

በትግራይ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም ለሶስት አመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መቆሙ ተከትሎ ወደ አክሱም የሚደረገው የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት መጀመሩ መልካም ቢሆንም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የጎብኚዎች ቁጥር  ጋር ሲነፀፀር እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኃላ በአንድ አመት ውስጥ ፦ የፊሊፕንስ  ፣ የቻይና ፣ የኬንያ፣ የጣልያን ፣ የአሜሪካ ፣ የካናዳ ፣ የፈረንሳይ ፣ የዩጋንዳ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የናምቢያ ፣ የአውስትራሊያ ፣የቤሌጅም፣ የሰፔን ፣ የጀርመን ፣ የፓኪስታን ፣ የኮሪያ ፣ የቼክ ሪፐብሊክ ፣ የሃንጋሪ ፣ የደቡብ አፍሪካ ፣ የህንድ ፣ የፓላንድ ፣ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው 200 የውጭ ዜጎች አክሱም ጎብኝተዋል።

ከጦርነቱ በፊት አክሱም የተጠቀሰው ያህል ቁጥር ያለው ቱሪስት በአንድ ቀን ውስጥ ታስተናግድ ነበር ይላሉ አቶ ኪዱ ተጠምቀ።  

በተጨማሪ፦

- በጦርነቱ ምክንያት ውድመትና ዝርፍያ ደርሶባቸው የነበረው ደረጃቸው የጠበቁ ሆቴሎች እድሳት ተደርጎላቸው አገለግሎት እየሰጡ ነው።

- ከአክሱም በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ታሪካዊቷ የዓድዋ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችም አገልግሎት እየሰጡ ነው።

- ለጉብኝት የሚመጡት ቱሪስቶች የማረፍያ እጥረት አይገጥማቸውም።

አቶ ኪዱ ፥ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተከትሎ አንድ አመት የሞላው ተነፃፃሪ ሰላም በክልሉ እንዳለ ፣ የአክሱም አውሮፕላን ማረፍያ አገልግሎት ባይጀምርም የሽረ አውሮፕላን ማረፍያ ከአክሱም በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ መሆኑ ከሽረ ወደ አክሱም በመኪና የሚያጓጓዝ ደረጃው የጠበቀ የአስፋልት መንገድ መኖሩ ፣ በአክሱም ከተማ ለጎብኚዎች የሚያሰጋ የፀጥታ ስጋት እንደሌለ ሚድያዎች እንዲሁም የፌደራል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መ/ቤት በተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች መረጃ በተከታታይ ያለማሰራጨታቸው ለቱሪስቶች ቁጥር ማነስ አስተዋፅኦ አለው ያሉ ሲሆን ይህ እጥረት እንዲታረም አሳስበዋል።

አክሱም የፀጥታ ስጋት የሌለባት ደህንነቷ የተጠበቀና በበቂ ሁኔታ እንግዶችን እያስተናገደችን መሆኗን በማወቅ ቱሪስቶች / ምእመናን ወደ አክሱ። በልበ ሙሉነት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድም በመኪና ካልሆነም ከአዲስ አበባ በአውሮፕላን ወደ ሽረ በመምጣት ከሽረ አውሮፕላን ማረፍያ እስከ አክሱም 60 ኪሎ ሜትር ርቀት በመሆኑ ደረጃውን በጠበቀው የአስፋልት መንገድ በመኪና ተጉዞ አክሱም መግባት ይቻላል።

መረጀው የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ነው።

@tikvahethiopia