#Hawassa

" አደጋ ለመከላከል ተብለው የተቀመጡ የፍጥነት መቀነሻዎች ወይም ስፒድ ብሬከሮች ምልክት ስለሌላቸው እራሳቸው የአደጋ መንስኤ እየሆኑ ነው " - ነዋሪዎች

" ችግሩ ጎልቶ የሚታይበትን ዋና መንገድ የሰራዉ የፌደራል መንግስት ነው የፍጥነት መቀነሻዎችን ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክትም ሆነ ከርቀት እንዲታዩ የሚረዳ ቀለም የመቀባት ኃላፊነት አለበት " - የሀዋሳ ከተማ መንገድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት  መምሪያ

በሀዋሳ ከተማ ያሉ የፍጥነት መቀነሻዎች ወይም ስፒድ ብሬከሮች የአደጋ መንስኤዎች ሆነዉብናል ሲሉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸዉን ገለጹ።

በከተማዉ የተለያዩ መንገዶች በተለይም ከተማዉን አልፎ በሚሄደዉ አዉራ ጎዳና ላይ የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት ለመቀነስ በርካታ የፍጥነት መቀነሻዎች እንዳሉ ይታወቃል።

ይሁንና እነዚህ መቀነሻዎች ከፍተኛ መጠን ያላቸዉ ከመሆኑ በተጨማሪ ለአካባቢው አዲስ ለሆኑ አሽከርካሪዎች ምልክት አለመቀመጡንና የተለየ ቀለም አለመቀባታቸዉን ተከትሎ ከፍተኛ አደጋ እየፈጠሩ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ የከተማዉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ የሀዋሳ ከተማ መንገድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት  ምክትል የመምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ አዴላ በበኩላቸዉ ቅሬታዉን ቀድመዉ እንደሚያዉቁት ገልጸዋል።

ችግሩ ጎልቶ የሚታይበትን ዋና መንገድ የሰራዉ የፌደራል መንግስት መሆኑን በመግለጽ ለተሰሩ የፍጥነት መቀነሻዎችም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክትም ሆነ ከርቀት እንዲታዩ የሚረዳ ቀለም የመቀባት ሀላፊነት ያለበት ራሱ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን መሆኑን ያነሳሉ።

አቶ አበራ አክለዉም አሁን ላይ ችግሩን ለመቅረፍ በቅርቡ ከፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ጋር ዉይይት ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዉ ምናልባትም ሀላፊነቱን የከተማዉ መንገድ ትራንስፖርት መቀበል ከቻለ ማስተካከያዎችን በቅርብ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁመዋል።

መረጃ ተዘጋጅቶ የተላከው በሀዋሳ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ነው።

@tikvahethiopia