#ጎንደር

° " የሽንኩርት ሽያጭ ዋጋ በኪሎ 60 ብር ነበር አሁን በእጥፍ አድጎ እስከ 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው " - የጎንደር ነዋሪ

° " በሚታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የዕለት ከዕለት ኑሮን መግፋት አስቸጋሪ ሆኖብኛል " - የጎንደር ነዋሪ


በጎንደር ከተማ ተከስቶ የነበረውን ግጭት መነሻ በማድረግ በኢንዱስትሪና በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አስተሪዮ አስማረ በሰጠው አስተያየት ቀደም የሽንኩርት ሽያጭ ዋጋ በኪሎ 60 ብር ነበር አሁን ዋጋው በእጥፍ አድጎ እስከ 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡

የዘይትና የሌሎች የሸቀጥ ምርቶችም ላይም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡

ታዲያ የዋጋ ንረት በመከሰቱ " የዕለት ከዕለት ኑሮዬን ለመምራት ተቸግሪያለሁ " ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሌላው በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጎበዬ መኩሪያው ደግሞ በአካባቢው ተከሰቶ የነበረውን ግጭት ምክኒያት በማድረግ በግብርና ምርቶችና በሸቀጥ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል ይላሉ፡፡

የጤፍ ዋጋ በኪሎ 65 ብር ይሸጥ የነበረው አሁን ወደ 110 ብር አሻቅቧል፡፡

" በእያንዳንዱ የሸቀጥ ምርቶችም ላይም በተመሳሳይ የሽያጭ ዋጋቸው እየጨመረ ነው፡፡ ነጋዴዎች ያላግባብ ምርት ያከማቻሉ፡፡ ያላግባብ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ነዋሪዎች ግጭት ይነሳል በሚል ስጋት እህል እየገዙ ያከማቻሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የዕለት ከዕለት ኑሮን መግፋት አስቸጋሪ ሆኖብኛል " ሲሉ አስተያየት ሰጭው ይናገራሉ፡፡

እየተደረገ ያለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ከሰሞኑን በነበረ አንድ መድረክ ላይ ፤ " በከተማዋ በኢንዱስትሪና በግብርና ምርቶች ላይ ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ይህ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎችና የመንግሰት ሰራተኞችን አስመርሯል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት ይሰራል " ብለዋል፡፡

" የከተማ አስተዳደሩ ለዳሽን የሸማቾች ህብረት ስራ ዩኔን 20 ሚሊየን ብር ያለ ወለድ ብድር ሰጥቶ በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት የግብርና ምርቶችን የማሰራጨት ስራ እየተሰራ ነው " ያሉት ከንቲባው በቀጣይ ለመሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ሰራ ማህበራት የሚደረገው ያለ ወለድ የገንዘብ ብድር ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፤ የማህበራትን አቅም የማሳደግ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ያለ አግባብ ምርት በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይም ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡     

መረጃውን የጎንደር የቲክቫህ-ኢትዮጵያ የቤተሰብ አባል ነው የላከው።

@tikvahethiopia