" የመኪና ባለንብረቶች መኪና ስታሳጥቡ በተቻለ መጠን ከስፍራው አትራቁ ፤ ወይም ቁልፍ ጥላችሁ ባትሄዱ ይመረጣል " - አዲስ አበባ ፖሊስ

እንዲያጥብ የተሰጠውን ተሽከርካሪ ሰርቆ የተሰወረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ እንዲያጥብ የተሰጠውን ተሽከርካሪ ሰርቆ ከአዲስ አበባ በመውጣት ከተሰወረ በኃላ ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ከነተሽከርካሪው ሊያዝ ችሏል።

የፖሊስ መረጃ ግለሰቡ " ስራ በማጣት ተቸግሬአለሁ " በሚል ምክንያት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አባዶ ገደራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመኪና እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ጠይቆ ስራ እንደጀመረ ያሳያል።

ስራ በጀመረ በሶስተኛው ቀን ግን ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ/ም ከቀኑ 11:30 ሰዓት ገደማ ሲሆን የግል ተበዳይ የሰሌዳ ቁጥር " ኮድ 3-B12112 አ.አ " የሆነች ተሽከርካሪያቸውን እንዲያጥብላቸው ከነቁልፉ በእምነት ቢሰጡትም ተሽከርካሪውን አስነስቶ  ከአዲስ አበባ ውጪ ይዞ መሰወሩን የአባዶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል።

ፖሊስ የግል ተበዳይን አቤቱታ ተቀብሎ ክትትል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ተጠርጣሪው መኪናውን ይዞ ወደ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማ እንደተጓዘ በማረጋገጥ እና ወደ ስፍራው በመሄድ ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል፡፡

ፖሊስ በከተማው ለሚፈፀሙ የተሽከርካሪ ስርቆቶች በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በቂ ጥንቃቄ አለማድረጋቸውና መዘናጋታቸው ነው ያለ ሲሆን በተለይም መኪናቸውን በሚያሳጥቡበት ወቅት በተቻለ መጠን ከስፍራው ባይርቁ አልያም ቁልፍ ጥለው ባይሄዱ  ይመረጣል ብሏል።

#AddisAbabaPolice

@tikvahethiopia