#MoE

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚማሩት ትምህርት ውጪ ወደ ተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ሔደው ለሚያደርጓቸው የተግባር ላይ ልምምዶች የሚደረግ ወጪ÷ ከምርቃት በኋላ በሚከፍሉት የወጪ መጋራት ውስጥ እንዲካተት ጥናት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጪ መጋራት (Cost Sharing) መመርያ መሠረት ወደ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎች÷ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ተመርቀው እስኪወጡ ድረስ፣ መንግሥት ለምግብና ለመኝታ ያወጣውን ወጪ በሚገቡት ውል መሠረት ከምርቃት በኋላ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡

ተማሪዎች ወደ ተግባር ልምምድ ሲወጡ ለሚቆዩባቸው ጊዜያት ለሚኖራቸው የተግባር ላይ ትምህርት፣ ከምረቃ በኋላ ከወጪ መጋራት ጋር ተደምሮ እንዲከፍሉ ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር ዕቅድ መያዙንና ጥናት መጀመሩን፣ በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማት ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ተሾመ ዳንኤል ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

ሐሳቡ በጥናት ላይ መሆኑንና ዓላማውም ወደፊት ተማሪዎች የተግባር ላይ ልምምድን ትኩረት ሰጥተው እንዲማሩ ለማድረግ በማሰብ የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለክፍያው የልማት አጋር ድርጅቶች ለትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ትስስር የሚመድቡት ገንዘብ ስለሚኖር፣ ከዚህ ገንዘብ ለወጪ መጋራት ሊከፈል የሚችልበት አሠራርም ሊዘረጋ እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

መረጃው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

@tikvahuniversity