TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ENDF🇪🇹

በሀገር ደረጃ ዛሬ 116ኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተከብሯል።

ለመሆኑ በዓሉ ለምንድነው " ለ116ኛ ጊዜ " እየተባለ የሚከበረው ?

ይህ ቀን / ጥቅምት 15 የተመረጠው ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1900 ዓ/ም ያቋቋሙትን የጦር ሚኒስቴርን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ከዚህ ቀደም የ " መከላከያ ሰራዊት ቀን " ተብሎ ሲከበር የነበረው ኢህአዴግ በ1987 ዓ/ም አዲስ የመከላከያ ሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ አዘጋጅቶ በተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀበት ወቅት ነው።

በዚህ መነሻ የካቲት 7 ቀን በየዓመቱ ሲከበር ነበር።

ኢህአዴግ በውስጡ የነበሩት አመራሮች አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ ካደረጉ በኃላ / በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የሀገር አስተዳደር የቀድሞው ውሳኔው " ከ1987 በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት እና የዘመኑ ትውልድ ተጋድሎን ውድቅ ያደረገና ቆርጦ ያስቀረ ነው " በማለት ቀኑን ወደ ጥቅምት 15 ቀይሮታል።

ቀኑ እንዲቀየር በተደረገው ጥናት ለበዓሉ መከበር መነሻ የሀገር ሰራዊት በቋሚነት ተደራጅቶ እንደ ተቋም የተመሰረተበት ቀን ሊመረጥ ችሏል።

ይህም ቀን ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የአፄ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትር መ/ቤት ያቋቋሙበትና መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ሚኒስትር የሰየሙበት ቀን ነው።

ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፊትአውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ / አባ መላ ነበሩ።

የዘንድሮው የሰራዊት ቀን ለምን በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት ለማክበር ተፈለገ ?

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራት ኃላፊ ሌ/ጄነራል ዓለምእሸት ደግፌ ዛሬ በመስቀል አደባባር በተካሄደው ዝግጅት ላይ ባሰሙት ንግግር " በዓሉ በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት እንዲከበረ የተፈለገው ለእይታ ስለሚማርክ ብቻ ሳይሆን ዋናው እሳቢያችን ዛሬም ነገም ሰላማችንን ለማወክ የሚመኙ ካሉ ሁሌም ዘወትር ዝግጁ መሆናችንን ከወዲሁ ለማሳሰብ ነው " ብለዋል።

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የሰራዊት ቀን በዓል ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጦር ሰራዊት አመራር እና አባላት፣ የክልል ባለስልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ...እና ሌሎችም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው ነበር።

@tikvahethiopia