" የትምህርት ሚኒስቴር በዋናነት ለተገኘው ውጤት የኔ ውድቀት ነው ብሎ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል " - ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

የትምህርት ሚኒስቴር ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት መመዝገብ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በጥናት ለይቶ እንዲያቀርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።

በይህ የተጠየቀው በምክር ቤቱ የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ዛሬ ሲገመግም ነው።

በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ " ቀደም ሲል ሲሰጡ የነበሩ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቶች የተማሪዎችን ትክክለኛ ችሎታ ያሳዩ አልነበሩም " ብለዋል።

የፈተና አሰጣጡን በመቀየር የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት በዘርፉ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው እየተካሄዱ ያሉ የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ መርኃ ግብሮችና የመምህራን አቅም ግንባታ ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

በምክር ቤቱ የሰዉ ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ፤ " ሚኒስቴሩ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት መምጣት ሁሉንም ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም " ብለዋል።

በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር የማስተማርና ፈተና የማስፈተን ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተቋም በዋናነት ለተገኘው ውጤት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባዋል ነው ያሉት።

ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ተጠሪ ተቋማትና የትምህርቱ ዘርፍ ተዋንያን ለውጤቱ የነበራቸው ድርሻ ተለይቶ መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ማጣት ምክንያት የሆኑ ሌሎች ችግሮችም በጥናት ተለይተው ሊቀርቡ እንደሚገባም ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል። #ኢዜአ

@tikvahethiopia