#Amhara

" ከአቅማችን በላይ ነው ፤ ከክልሉም አቅም በላይ ነው " - የሰሜን ጎንደር ዞን

የሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ በድርቅ ምክንያት እስካሁን 32 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ከ53 ሺህ በላይ እንስሳትም ሞተዋል።

ድርቅ ከከፋባቸው ወረዳዎችም እና አካባቢዎች ዜጎች ቄያቸውን ለቀው እየተሰደዱ ይገኛሉ።

ዞኑ ያለው ችግር ከዞንም ከክልልም አቅም በላይ እንደሆነ ገልጿል።

የዞን አደጋ መከላከል የምግብ ዋስትና ተጠሪ ፅ/ቤት ለሸገር ሬድዮ ጣቢያ በሰጠው ቃል ፤ ችግሩ በእኛ አቅም የሚፈታ አይደለም ፤ እሱ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃም የሚፈታ አይደለም ብሏል።

ሁሉም ተቀናጅቶ መንግሥት ፣ የሚመለከተው አካል ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊዎች ሌሎችም ተረባርቦ መስራት ካልተቻለ ቀጣይ ነገሮች #እየከበዱ ነው የሚመጡት ሲል ገልጿል። " መንግሥት ችግሩን ብቻውን አይችለውም " ሲልም አክሏል።

በሰሜን ጎንደር ድርቅ በተከሰተባቸው ወረዳዎች በክረምት ወቅት ዝናብ እንዳልተገኘ የታወቀ ሲሆን በዚህ ምክንያት ከ462 ሺህ በላይ ዜጎች አደጋ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 202 ሺህ ሰዎች የረሃብ አደጋ ላይ ናቸው።

ይህ ዞን ቀድሞም በሰሜን ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በአሁን ሰዓት ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሱዳን እና ኤርትራ የተሰደዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተጠልለውበት እንደሚገኙ ሸገር ኤፍ ኤም ዘግቧል።

በሌላ ዘግይቶ ባገኘነው መረጃ በአማራ ክልል 1 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

የክልሉ  አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ይፋ እንደረገው በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ድርቅ ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎችም የዝናብ እጥረት ተከስቷል።

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደር በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የከፋ ችግር እንዳለ በይፋ አሳውቋል።

በማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተተዳደር የዝናብ እጥረት ተከስቷል ብሏል።

ሰሜን ሸዋ ላይም በግሪሳ ወፍ ወረራ ምክንያት ችግር መኖሩን ገልጿል።

በዚህም በክልሉ በድርቁ ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር 1 ሚሊየን እንደሆኑ አሳውቋል።

ዓለም ዓቀፍ ረጂ ድርቶች ድጋፍ ማቆማቸውን የገለፀው ኮሚሽኑ የክልሉ መንግሥት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ነው ብሏል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት ድጋፍ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች አሉ ያለው ኮሚሽኑ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ርብርብ ይደረግ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

@tikvahethiopia