#ሲዳማ

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ህብረተሰቡ የሚረብሹ አካላትን ሲያስጠነቅቅ ተቃዋሚው የሲዳማ ፊደራሊስት ፓርቲ  በበኩሉ የቢሮው ሰሞነኛ መግለጫ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመሸፋፈን በር የሚከፍት ነዉ ብሎታል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምንድነው ያለው ?

ቢሮው ፤ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ግብረሃይል ወቅታዊ ክልላዊና የሀገራዊ ፀጥታ በተመለከተ ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

ግብረኃይሉ በክልሉ አንዳንድ ግለሰቦች በክልሉ መንግሥትና በሕብረተሰቡ መካከል ጥርጣሬ ለመፈጠር፣ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም፣ ሀሰተኛ መረጃዎች በማሰራጨት ላይ ናቸው ብሏል።

የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ጊዜ እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲመለሱ ቢነገራቸውም መመለስ ባለመቻላቸው የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል በየደረጃው የሚገኙ ፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ህግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስቧል።

መንግሥት ህግን ለማሰከር በሚወስደው እርምጃ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ አካላት ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባቸዋል ብሏል።

ከፀጥታ ቢሮው በተጨማሪ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት አንድነትን በሰበኩ አፋቸው ዛሬ ጎሰኝነት እየሰበኩ በማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ ወሬ እያሰራጩ ህብረተሰቡ ሳይወክላቸው ለግል ጥቅማቸው ከውጭና ከውስጥ ተልዕኮ ተቀብሎ እኩይ ተግባራቸው ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ ያለ ሲሆን እነዚህን አካላት የክልሉ መንግሥት አይታገሳቸውም ብሏል።

የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ፤ የክልሉ ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ ያወጣው መግለጫ ልክ እንዳልሆነና በክልሉ ዉስጥ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመሸፋፈን በር የሚከፍት ነዉ ብሏል።

ለቲኪቫህ ኢትዮጵያ አስተያየታቸዉን የሰጡት የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊዉ አቶ ገነነ ሀሳና ፤ ይህ የክልሉ መንግስት አካሄድ በሶሻል ሚዲያ የሚታገሉትን ወጣቶች ድምጽ በማፈን በመንግስት ስር ሆነዉ የህዝብን ሀብት የሚዘርፉ አካላትን ከለላ የሚሰጥ ነዉ ብለዋል።

አቶ ገነነ አክለዉም ካሁን በፊት በክልሉ የሚከሰቱ በርካታ ችግሮችን አስመልክተን ለሰላም ሚኒስትር ለፌደራል ፖሊስና ለምርጫ ቦርድ የተለያዩ ደብዳቤዎችን ፅፈናል ያሉ ሲሆን አሁንም የክልሉ መንግስት እየሄደበት ያለዉን መንገድ ለማስተካከል እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

ካሁን በፊት ለሚጽፉት የቅሬታ ደብዳቤዎች ፈጣን ምላሽ የሚያገኙት ከምርጫ ቦርድ መሆኑን የሚያነሱት ሀላፊዉ አሁን ላይ ከሌሎችም ሚኒስትር መስሪያቤቶች ጋር በመነጋገር ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

@tikvahethiopia