#ALERT🚨

" ሰባ ሰባት እንኳን አንዲህ አልነበረም "

ሰሀላ ሰዬምት ወረዳ በከባድ ድርቅ መመታቱ ተገልጿል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ስር ያለው ሰሀላ ሰዬምት ወረዳ 13 ቀበሌዎች አሉት።

ወረዳው የ2015/2016 የምርት ዘመን #ድርቅ ክፉኛ መትቶታል።

ወረዳው በከፊል አርብቶ አድር የሚታወቅ ሲሆን ከማሳው በሚያገኛት ጥቂት ኩንታል እህል በይበልጥ ለገለባው ዋጋ ሰጥቶ በእንሰሳቱ ኑሮውን የሚገፈ አርሶና አርብቶ አደር አካባቢ ነው።

በወረዳው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብትም ይገኛል።

ጠቅላላ ካለው የእንስሳት ሀብት የዳልጋ ከብት 104,430፣ የጋማ ከብት 22,121 በግ እና ፍየል 465,428 ይገኙበታል።

ከዚህ ውስጥ ለድርቅ የተጋለጡ የዳልጋ ከብት 92,430፣ የጋማ ከብት 16,121፣ በግ እና ፍየል 396,760 ናቸው።

ወደአጎራባች ዞን የተሰደዱ የዳልጋ ከብት 20,328 ፣ በግ እና ፍየል 116,900 ሲሆኑ እስካሁን በድርቅ ምክንያት የሞተ የዳልጋ ከብት 1320 ፣ የጋማ ከብት 71 በግ እና ፍየል 2457 ናቸው።

በወረዳው ከ52 ሺህ በላይ ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን 46ሺ የሚሆነው አፋጣኝ እርዳታ ካለገኘ አደጋ ውስጥ እንደሆነ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ ተናግረዋል።

አቶ ሲሳይ፤ " ምንም እንኳን ድርቅ ቢሆንም ከዚህ በፊት ለእንስሳት የሚሆን ሳር አይጠፋም ነበር። ዛሬ ግን የተቃጠለ መሬት ብቻ ነው የሚታየው፤ ለጥርስ ስጋ ማውጫ የሚሆን የሳር ስንጥር እንኳን አይታይም፤ የወረዳው ነዋሪዎች እንደነገሩን እንደ ወረዳችን እንዲህ አይነት ድርቅ አይተን አናውቅም፤ ሰባሰባት እንኳን አንዲህ አልነበረም " በማለት የድርቁን አስከፊነት ገልጸዋል።

በወረዳው የአርሶ አደሩ ማሳ ርቃኑን ቀርቷል፣ እንስሳት ቆዳቸው ከስጋቸው መጣበቅ ብቻ ሳይሆን ነፍሳቸው በጣዕረሞት ላይ ናት፣  ህጻናት፣ እናቶችና አረጋውያን በርሀብ ተገርፈው ነፍሳቸው ከጉንጫቸው ተጣብቃ ይዛቸው ልትጠፋ አፋፍ ላይ ነች። ተሎ መድረስ ካልተቻለ አሳዛኝ ክስተት በሰሀላ ሰዬምት ወረዳ ሊከሰት ይቻላል።

የአስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ጉዞ አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን የብሄረሰቡ ከፍተኛ አመራሮችና አንዳንድ ግብረሰናይ ድርጅቶች በወረዳው ተገኝተው ቀበሌዎቹን ጎብኝተው ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገው ነበር።

የቀበሌው ማህበረሰብ በውይይቱ ላይ " ከእግዚአብሄር በታች መንግስት ነበር ለሰው ልጅ ዋስትና፣ ዛሬ ግን መንግስትም ፊቱን አዞረብን " ብለዋል።

" በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚበላ ካልቀረበ ልጆቻችን አናገኛቸውም ፤ አሁንም ቢሆን አንዲት እንጀራ ለ10 ሰው ነው የምንሻማው፤ ከዛ ውጭ ግን ጨው በውሀ በጥብጠን ነው የምንጠጣው " ብለዋል።

እስካሁንም በወረዳው በርሀብ ምክኒያት የ2  ሰዎች ሂይወት አልፏል ሲሉ አሳውቀዋል።

እንስሳትን በተመለከተ " በወረዳችን ትንሽ እህል ካገኘን እንሰሳ ስለምናረባ ከብት እና ፍየሎቻችንን ሸጠን እህል ስለምንሸምት ብዙም አያሳስበንም ነበር፤ ዘንድሮ ግን ለከብቶችም ሆነ ለፍየሎችና በጎች የሚሆን የሚጋጥ ሳር ስለሌለ ተስፋ አስቆርጦናል " ብለዋል።

የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ምህረት መላኩ፤ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቃል ከመግባት የዘለለ በመንግስት በኩልም ምንም የቀረበ ነገር የለም።

ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ሪፖርት ከማድረግ ባለፈ የችግሩን አሳሳቢነት ብንገልጽም እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም ብለዋል።

መረጃው ከዋግኽምራ ኮሚኒኬሽን ነው የደረሰን።

@tikvahethiopia