#Afar

" ከጨው ፓለቲካ ጋር በተያያዘ ከ1,700 በላይ ሰዎች ታስረዋል " - የዶቢ ጨው አምራቾች ማኅበር

" ከጨው ፓለቲካ ጋር በተያያዘ ከ1,700 በላይ ሰዎች ታስረዋል" ሲል በአፋር ክልል የሚገኘው የዶቢ ጨው አምራቾች ኃላ/የተ/የግል/ሕብረት ሽርክና ማኅበር ገለጸ።

ሰዎቹ የታሰሩት የት ማረማያ ቤትና ለምን እንደሆነ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ ማኅበሩ፣ " የታሰሩት በሰመራ ማረሚያ ቤት ነው፣ የታሰሩበት ምክንያት ደግሞ ጨው ለማምረት በመከልከላቸው ቅሬታ ሲያቀርቡ ነው " ብሏል።

ማኅበሩ እንዳስረዳው ፤ 409 አባላቱ ጨው እንዳያመርቱ በመንግሥት መታገዳቸውን፣ የታገዱበት ምክንያትም እንዳልተነገራቸው ነው።

የሚኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሁሴን አሊ የማኅበሩ አባላት በችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በክልሉ ብዙ #ሙስና እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ፤ በጨው ማምረት ሥራ የተሰማሩት በክልሉ የሚገኙ አመራሮች ብቻ ናቸው ብለዋል።

የማኅበሩ አባላት በተናጠልና በጋራ እንደገለጹት ፣ ክልከላው እንዲነሳ  ለሚመለከታቸውን የክልሉ የመንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በማኅበርና በየፊናቸው በሰጡት ገለጻ፣ በዚህ ሳቢያ በአፋር ክልል ግጭት ከመፈጠሩ በፊት የፌደራል መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህም ባሻገር ጨው አምራቾች ምርታቸው የሸጡበት የስድስት ወራት ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ፣ የማኅበሩ አባላት በየፊናቸውና በማኅበር በሰጡት ገለጻ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ፤ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ " ተርበናል " ብለው የሚጠይቁ ሰዎች በፓሊስ እየታሰሩ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ሰዎች በርሃብ እየሞቱ ነው ብለው፣ ለአብነትም በአፍዴራ ሰሞኑን ሁለት ሰዎች ሞተዋል ብለዋል።

ዶቢ የጨው አምራች ማኅበር ኃላ/የተ/የግል/ሕብረት ሽርክና ማኅበር በአፋር ክልል በ1992 ዓ.ም በባህላዊ የምርት አሰራር የተመሰረተና በሂደት ወደ ዘመናዊነት የተሸጋገረ 409 አምራች አባላት ያሉት ማኅበር ነው።

መረጃውን የአዲስ አበባ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ነው ያዘጋጀው።

@tikvahethiopia