#አማራ

ዋዜማው እና የአዲስ አመቱ አቀባበል በአማራ ክልል እንዴት ነው ?

በአማራ ክልል በቅርቡ ባጋጠመው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት የዘንድሮው አዲስ ዓመት አቀባበል ቀዝቃዛ እንደሆነ ነዋሪዎች እየገለፁ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት የነበሩ የአዲስ ዓመት አቀባበሎችም ክልሉ ባስተናገደው አስከፊ ጦርነት ምክንያት ዜጎች በተሟላ ሰላም በዓሉን መቀበል እንዳልቻሉ የሚታወቅ ነው።

በዘንድሮው ዓመትም ባጋጠመው ጦርነት ሰላም በመራቁ የአዲስ አመት አቀባበሉ ጥላ ያጠላበት ነው።

የኢተርኔት አገልግሎት በክልሉ እንደተቋረጠ ነው።

ዛሬ ቃላቸውን ለዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች የበዓሉ ድባብ ቀዝቃዛ ነው ብለዋል።

የደብረታቦር ከተማ ነዋሪ ፦

" በዓሉን በተመለከተ የተለየ ነገር በከተማው አይታይም።

የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት በመቋረጡም የመልካም ምኞት መልዕክቶችን መለዋወጥ አልቻልንም። "

የደንበጫ ከተማ ነዋሪ ፦

" አካባቢው እንስሳት የሚደልቡበት አካባቢ ነው። በነበረው አለመረጋጋት እንስሳት መድለብ አልቻሉም። ከሌላ ቦታ ሄዶ የእርድ እንስሳትንም መግዛት አልተቻለም።

አጋጣሚው በአዲሱ ዓመት አቀባበል ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል። "

ሌላ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ፦

" የዓመት በዓሉን መድረስ የሚያመላክቱ ሙዚቃዎች አይሰሙም፣ ለእርድ እንስሳት የተዘጋጄ ሰው አላየሁም። "

የቢቸና ነዋሪ ፦

" ከዚህ ቀደም በነበሩ የበዓል ዝግጅቶች የእርድ እንስሳትን ቀደም ብለው ይገዙ ነበር።

አርሶ አደሩም ሆነ የእንስሳት ነጋዴው የደህንነት ስጋት ስላደረበት እንስሳቱን ወደ ገበያ ማውጣት አልቻለም። "

የደብረ ማርቆስ ነዋሪ ፦

" በጦርነት ቆፈን ሆኖ በዓል ማክበር አይቻልም። "

የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ፦

" ሁሉም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ሥራ ባለመግባታቸው በአዲሱ ዓመት አከባበር ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል። "
ይህች ከተማ በቅርብ ብርቱ ውጊያ ያስተናገደች ናት።

የደሴ ከተማ ነዋሪ ፦

" ወቅታዊ ሁኔታው በበዓሉ ድምቀት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። "

የባህርዳር ነዋሪዎች ፦

" የባሕር ዳር ከተማ የዓመት በዓል ድባቡ ብዙ ባይታይም የእንስሳት አቅርቦት አለ።

ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር የዋጋ መጨመር ይታያል ብለዋል፡፡ "

የእንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ ነዋሪ ፦

" ሰሞኑን በዋለው ገበያ የእንስሳቱም ሆነ ሌሎች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦች ዋጋ እጅግ ጨምሯል።

ምክንያቱም ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች በሙሉ ባለመከፈታቸው ሸቀጦች እንደልብ እየገቡ ባለመሆናቸው ነው፡፡ "

@tikvahethiopia