TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#GERD🇪🇹

" በተያዘው በጀት ዓመት ሌሎች ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ ይገባሉ " - ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

ኢትዮጵያ ዛሬ 4ኛውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ (የአባይ ግድብ) የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን በይፋ አብስራለች።

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይኸኛው 4ኛ ዙር ሙሌት የመጨረሻው ስለመሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ሙሌቱ በስኬት በመጠናቀቁ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው ፣ በጉልበታቸው ፣ በፀሎታቸው በስራው ለተሳተፉ ምስጋና አቅርበው " እንኳን ደስ አላችሁ " ብለዋል።

ለኢዜአ ቃላቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዳግሞ ፤ ባለፉት 4 ዓመታት የውሃ ሙሌት ስራውን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የዝናብ መጠን መገኘቱን አስረድተዋል።

የውሃ ሙሌት ስራው በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት በማያደርስ መልኩ መከናወኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በዘንድሮው ክረምት በግብጽ የሚገኘው የአሰዋን ግድብ ከበቂ በላይ ውሃ በመያዙ ምክንያት በግድቡ ማስተንፈሻ አማካኝነት ውሃ የማፋሰስ ስራ ሲያከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስቱ አገራት የትብብር ምንጭ ከመሆን ባሻገር በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚያስከትለው ጉዳት እንደሌለ በተግባር ያመላከተ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ ኃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች በስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሌሎች ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ እንደሚገቡ አሳውቀዋል።

4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በግድቡ ግንባታ ሂደት ሌላኛውን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ የሚኖሩት ስራዎች ከዚህ ቀደም ከተለፈባቸው የተሻሉ እንደሚሆኑ የጠቀሱት ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ ፤ " ይህ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ስኬት ነው " ብለዋል፡፡

@tikvahethiopia