#Hawassa

በሀዋሳ የውርርድ / ቤቲንግ ቤቶች እየታሸጉ ነው ፤ ለምን ?

በሀዋሳ ከተማ የስፖርት ዉርርድ ወይም ቤቲንግ ቤቶች አየታሸጉ መሆኑ ተሰምቷል።

በከተማዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መበራከታቸዉ የሚነገርላቸዉ የስፖርት ዉርርድ ቤቶች ምንም እንኳን ህጋዊ ግብር ከፋይ ሆነዉ ወደስራ ቢገቡም ከሰሞኑ በሀዋሳ ከተማ የመታሸግ እጣ እንደገጠማቸው አሳውቀዋል።

ይህን ተከትሎ ቤታቸዉ የተዘጋባቸዉን ቅሬታ አቅራቢዎችና የከተማውን የጸጥታ አካላት  የቲክቫህ ኢትዮጵያ ሀዋሳ ቤተሰብ ሪፖርተር አነጋግሯል።

ቤታቸው ተዘግቶ ከስራ ዉጭ መሆናቸዉ አግባብ አለመሆኑንና ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ያለዉን የንግድ ቤት መዝጋት አግባብ አለመሆኑን የገለፁት አስተያየታቸውን የገለጹልን አካላት ቤታቸው ለመዘጋቱ የቀረበላቸው ምክኒያት እርስበርስ እንደሚጋጭ ገልጸዋል።

በመጀመሪያ ቤቱን ሊዘጉ የመጡት አካላት " ስራችሁ ቁማር ነው " እንዳሏቸው የገለጹት አስተያየት ሰጭዎች ቆይቶ ላነሱት ጥያቄ ደግሞ " ጉዳዩ ከግብር ጋር የተያያዘ መሆኑንና የሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከፌዴራል ገቢዎች ጋር እያደረገ ያለዉን ንግግር ሲጨርስ ቤታችሁ ይከፈታል " መባሉን ገልጸዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ በበኩላቸዉ " ጉዳዩ ከግብር ባለፈ የጸጥታ ችግርን ከመቆጣጠር " ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከማህበረሰቡ ጋር በነበራቸዉ የዉይይት መድረክ የስፖርት ውርርድ ማካሄጃ አካባቢዎች የችግሮ ቀጠና እየሆኑ መምጣታቸዉ እንደተገለጸላቸው የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ የሰሞኑ አሰሳም ህጋዊነታቸዉን ከማረጋገጥ በዘለለ የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

የቤቶቹ ህጋዊነትና የግብር ጉዳይ በፌደራልና ሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ በኩል ውይይት ተደርጎበት የታሸጉ ቤቶች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደስራ እንደሚመለሱ የፖሊስ አዛዡ መግለፃቸውን የቲክቫህ ኢትዮጵያ የሀዋሳ ቤተሰብ ዘግቧል።

@tikvahethiopia