TIKVAH-ETHIOPIA
#State_of_Emergency ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ " አማራ ክልል " የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። አመሻሹን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ እንዲሁም የሚወሰዱ እርምጃዎች እና ተከለከሉ ተግባራት ዝርዝር ይፋ ተደርጓል። በዚህም ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬከተር ጄነራል የሚመራ…
#State_of_Emergency

ነገ በአማራ ክልል እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ በሚኒስትሮች ም/ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሕዝብ ተወካዮች በሚሰጡት ድምፅ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል።

ምክር ቤቱ፤ ከቀናት በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ መርምሮ ውሳኔ ለማሳለፍ ለነገ ሰኞ 8 ሰዓት ለምክር ቤት አባላት አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በዚሁ መሰረት አባላት ተሰብስበው ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሕጉ ምን ይላል ?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ ሁለት (ሀ) ይደነግጋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የታወጀ እንደሆነ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበት፣ የምክር ቤቱን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘም ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ ቀጣይ አንቀጽ ይደነግጋል።

6ኛው ዙር ምርጫ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭትና አለመረጋጋት ሳቢያ በተሟላ ሁኔታ ባለመከናወኑ፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ካሉት 547 ወንበሮች መካከል የተወሰኑት የተጓደሉ ናቸው።

በአጠቃላይ አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው ምክር ቤት መቀመጫ የያዙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብዛት 427 መሆኑን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ም/ ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማፅደቅ ይኖርበታል በሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊፀና የሚችለው ከአጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ማለትም በስድስተኛው ዙር ተመርጠው በምክር ቤቱ መቀመጫ ከያዙት 427 ተወካዮች መካከል 285 የሚሆኑት የድጋፍ ድምፅ ከሰጡ ነው።

ከተጠቀሱት 427 ተመራጮች ውስጥ 142 የምክር ቤት አባላት የተቃውሞ ድምፅ ከሰጡ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ ሊሆን ይችላል። 

በም/ቤቱ ወንበር ካገኙ አጠቃላይ 427 አባላት ወስጥ 410 የሚሆኑት በገዢው ፓርቲ ብልፅግና አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 125 ያህሉ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አቅራቢነት የተወዳደሩና የክልሉን ሕዝብ የሚወክሉ ናቸው።

ከብልፅግና ፓርቲ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ አምስት የሕዝብ ተወካዮች ሲኖሩ፣ በኢዜማ አቅራቢነት ተወዳድረው የተመረጡ ሌሎች አራት የሕዝብ ተወካዮች እንደሚገኙም ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ በቀረቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ላይ ለተሰጠው ድምፅ ሥሌት የተደረገው በዕለቱ የነበረውን የምክር ቤቱ ምልዓተ ጉባዔ መሠረት አድርጎ በመሆኑ፣ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምክር ቤት በሚቀርብበት ወቅት የሚኖረው የድምፅ አሰጣጥ ሥሌት በዕለቱ የሚኖረውን ምልዓተ ጉባዔ ታሳቢ የሚያደርግ ይሆናል።

በመሆኑም የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሥሌቱ ከላይ የምክር ቤቱን ጠቅላላ አባላት መሠረት በማድረግ ከተገለጸው ውጤት ያነሰ የድጋፍ እና ተቃውሞ ድምፅ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው።

(የሕግ ጉዳይ ማብራሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ)

@tikvahethiopia