#Tigray

የትግራይ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳይ አቋሙ ምንድነው ?

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር " የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ለማፍረስ ይቋምጣሉ " ያላቸውን በስም ያልጠቀሳቸውን ኃይሎች ዓላማ ለማክሸፍ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ይህንን የገለፀው ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በስም ያልገለፃቸውና በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛሉ ያላቸው ' ፅንፈኛ ' ሲል የጠራቸው ኃይሎችና አጋሮቻቸው " ትግራይ ላይ አሰበዉት የነበረውን የጥፋት አላማ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳከሸፈባቸው በአደባባይ የሚያማረሩበት ፤ ብሎም ከፌዴራል መንግስት ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ሲፈጠረ ፀረ ፕሪቶሪያና ፀረ ትግራይ አቋማቸውን በግልፅ በማራገብ ላይ ይገኛሉ " ብሏል።

" ይህን እንቅስቃሴ እንመራለን የሚሉ አመራሮችም ሆኑ አጋሮቻቸው እንዲሁም ያሰማሯቸው የሚድያ አፈቀላጤዎችና የርእዮተ አለም መሪዎች ፣ መከላከያ ሰራዊቱ በመውሰድ ላይ ያለውን እርምጃ ‘የህወሓት ቀጥተኛ ተሳትፎ አለበት’ በሚል በሬ ወለደ ጩኸት እየደረሰባቸው ላለው ሽንፈት የትግራይን ህዝብ ሰበብ ለማድረግ  ሲዳክሩ ይሰማሉ " ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ " የፌዴራል መንግስት በነዚህ ሀይሎች ላይ እየወሰዳቸው ላሉ እርምጃዎች የትግራይንም ሆነ የሌላውን ወገን የተለየ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለን አናምንም " ያለ ሲሆን " ይሁንና ግን ፀረ ሰላም አቋማቸውን ለማራመድ እስኳሁን ሲረጩት የነበረውን መርዝ  አልበቃ ብሎ የትግራይን ህዝብ በትልቁ በትንሹ ቋሚ ስራ አድርገውት ይገኛሉ " ብሏል።

ይህ ዘመቻ በፍፁም አሸናፊ ሊያደርግ አይችልም ፤ በህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውንም ሰላማዊ ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳ ነው ሲል አሳስቧል።

" አሁንም ቢሆን መላው የትግራይ ህዝብ ሁሉም ችግሮች #በሰላማዊ_መንገድ እንዲፈቱ ያለው ቁርጠኛ አቋም እንደተጠበቀ ነው " ያለው ጊዜያዉ አስተዳደሩ " የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማፍረስ የሚቋምጡ ፅንፈኛ ሀይሎችና የቅርብም የሩቅም አጋሮቻቸው በህዝባችን ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ ለማክሸፍ ከፌዴራል መንግስት እስካሁን ድረስ እያደረግነው የመጣነውን አበረታች ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል " ሲል አቋሙን ገልጿል።

(መግለጫው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia