"  ምግብ ካገኘን ሦስት ቀን አልፎናል " - ጎንደር የሚገኙ መምህር

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ለመስጠት አማራ ክልል ወዳሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሄዱ መምህራን በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ወደየመጡበት አካባቢ ለመመለስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

እንጃባራ ዩኒቨርሲቲ ፈታኝ የነበሩ አንድ መምህር ለቪኦኤ በሰጡት ቃል፤ በክልሉ " የሰላም ሁኔታው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ፤ ለመፈተን ሄደን በማናውቀው ሁኔታ ውስጥ ገብተናል " ብለዋል። " መንገዱ ዝግ ነው ነገሩ የደፈረሰ ነው ፤ ያለው ሁኔታ ያስፈራል " ሲሉ ተናግረዋል።

" ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት በመጣልን መልዕክት ' እዛው ባላችሁበት ፔንስዮን ቆዩ፣ አልጋ ይከፈላል ' የሚል ሲሆን እኛ ደግሞ ችግራችን የአልጋ አይደለም ፤ ችግር ውስጥ ነው ያለነው ፤ የየራሳችን ፕሬዜዳንቶችም እየደወሉ አይዟቹ እዛው ሁኑ ነው የሚሉን ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው ኮማንድ ፖስቱ ያለውን ነገር እስኪያሳውቅ ጠብቁ ነው ያሉን ፤ ያለው ሁኔታ ግን ያስፈራል " ሲሉ ገልጸዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ መምህር ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ፤ በከተማው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መሃል ከተማ ከሚገኘው የሆቴል ክፍላቸው ከወጡ ሦስት ቀናት መቆጠራቸውን ገልፀዋል።

" በከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም " ያሉት መምህሩ " የሆቴሉ ሠራተኞችም ወደ ሥራ እየገቡ ስላልሆነ ምግብ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኗል " ብለዋል።

" ምግብ ካገኘን ሦስት ቀን አልፎናል። ባለፈው ሳምንት የገዛነውን ቆሎ ነው እየቆጠብን እየበላን ያለነው። ከሆቴሉ እያገኘን ያለነው ውሃ ብቻ ነው " ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ በደብረ ማርቆስ የሚገኙ መምህር ደግሞ በከተማው ግጭት ባይኖርም የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን ተናግረዋል።

" ከተማው ከሞላ ጎደል ሰላም ነው። የደረሰብን ጉዳት የለም። ዋናው ችግራችን ወደ መጣንበት ለመመለስ አለመቻላችን ነው " ብለዋል።

አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በከተማዋ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሚገልጹት መምህሩ ፤ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከዚህ በላይ ተባብሶ የበለጠ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መልዕክት ያደረሱ የተለያዩ ተቋማት መምህራን ከግጭት ቀጠና የሚወጡበት መንገድ በፍጥነት እንዲመቻችና ወደቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት መንገድ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ያሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ አስገንዝበዋል።

@tikvahethiopia