TIKVAH-ETHIOPIA
ፎቶ፦ ዛሬ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በጸሎት ተከፍቷል። " የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ በክልል ትግራይ ባሉ አህጉረ ስብከት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተመድበው የነበሩ አራት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በፈጸሟቸው የቀኖና ቤተክርስቲያን እና የሕግጋተ ቤተክርስቲያን ጥሰቶች ዙሪያ ለመወያየትና ሕግጋተ ቤተክርስቲያንን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ጉባኤውን…
#EOTC

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ፅህፈት ቤት ዛሬ በተረጋገጠው የማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ፤ " ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ/ም በተጠራው አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሊያቀርቡት የነበረው አባታዊ ቃለ በረከት " በሚል 6 ገጾች ያሉት መልዕክት አሰራጭቷል።

በዚህ ቅዱስነታቸው " ሊያቀርቡት ነበር " በተባለው መልዕክት ዙሪያ / ለምን እንዳልቀረበ  ዝርዝር መረጃ ፅ/ቤቱ አልሰጠም።

ከቅዱስነታቸው አባታዊ ቃለበረከት የተወሰደ


" በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት በጦርነቱ ውስጥ ላሉ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም ምእመናን ድምፅ መሆን አልቻልንም።

በትግራይ ክልል ያለው ታሪክና ገዳማት የቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ መነሻ ሆነው ሳለ ከአክሱም ጽዮን ጀምሮ በመላ ትግራይ ስለ ተፈጸመው እልቂት፣ ስለ ገዳማቱ መፍረስ፣ ስለ ቅርሶች መውደም አልተቆጨንም፣ ድምጽም አልሆንም።

አንዳንድ አባቶችም በጊዜያዊ ስሜት ተነሳስተው ለተናገሩት ይቅርታ እንዲጠይቁ ለማድረግ ወይም ንግግራቸው ስህተት ነው ብለን መግለጫ ለመስጠትም አልፈቀድንም።

እኔም የሁሉም አባት እንደመሆኔ መጠን የትግራይ ክልል ሕዝብም ሕዝባችን ስለሆነ እና ቤተ ክርስቲያንም እንዳትወቀስ በማሰብ ከአንድም ሦስት ጊዜ በአጀንዳ ተይዞ እንድንነጋገርበት ለቋሚ ሲኖዶስ ሀሳብ ባቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡

የአባትነት ኃላፊነት ስላለብኝ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተፈጸመ ዝም ማለት የለብኝም ብዬ በሚድያዎች ድምጼን ለማሰማት ብፈልግም ፈቃድ አልተሰጠኝም፡፡

በዚህ መሃል ባገኘኋት አጋጣሚ ' በዓለም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በትግራይ ክልል ግፍ እየተፈጸመ ነው፣ ሕዝቡ እየተጨፈጨፈ ነው፤ ገዳማትና አድባራት እየፈራረሱ ነው፣ ቀሳውስትና መነኮሳት በቤተ መቅደስ ውስጥ ሳይቀር እንደ ዘካርያስ በጭካኔ እየተገደሉ ነው፣ መተኪያ የማይገኝላቸው ቅርሶቻችንም እየወደሙ ነው... ' በማለት የተሰማኝን ኃዘን ገለጽኩ፣ መግለጫዎችንም በተደጋጋሚ ሰጠሁ፡፡

በማግስቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሃገሪቱን ሚድያዎችን በይፋ በመጥራት፡- ' በፓትርያርኩ የተሰጠ መግለጫ የግላቸው እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስን ወይንም ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም ' የሚል መግለጫ ሰጡ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ድርጊቱን በዝምታ ከማለፍ ውጪ ምንም ተግሳጽ ስላላስተላለፈ የትግራይ ክልል ሊቃነ ጳጳሳትና ሕዝቡ ወደ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል። "

(የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ፅ/ቤት ያሰራጨው የቅዱስነታቸው ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia