TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
" ምዕራባውያን በአንድ በኩል የእህልና የማዳበሪያ አቅርቦታችን እያስተጓጎሉ ነው። በሌላ በኩል በዓለም የምግብ ገበያ ለተፈጠረው ቀውስ ግብዝ ሆነው እኛን ይከሱናል " - ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ኤርትራ እና ሶማሊያን ጨምሮ ለስድስት የአፍሪካ አገሮች ስንዴ በነጻ ለማቅረብ ቃል ገቡ።

ፕሬዝደንቱ ይኸን ቃል የገቡት የአፍሪካ - ሩሲያ ጉባኤ በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ሲጀመር ባሰሙት ንግግር ላይ ነው።

ፑቲን ፤  " በመጪዎቹ ሦስት እና አራት ወራት ከ25,000 እስከ 50,000 ቶን እህል በነጻ ለቡርኪና ፋሶ፣ ዚምባብዌ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ኤርትራ ለማቅረብ ዝግጁ እንሆናለን " ብለዋል።

የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት የዩክሬን የእህል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ይፈቅድ የነበረው ሥምምነት እንዲያበቃ በመወሰኑ አሜሪካን ጨምሮ ከምዕራባውያን ብርቱ ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በቱርክዬ አደራዳሪነት በተፈረመው ሥምምነት መሠረት 32.9 ሚሊዮን ቶን የምግብ እህል ከዩክሬን የእህል ጎተራዎች ለዓለም ገበያ ቀርቧል።

የሩሲያን ውሳኔ ኃላፊነት የጎደለው ሲሉ የሚተቹ የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞች በደሐ አገሮች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለረሐብ ይጋለጣሉ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ግን በሴንት ፒተርስበርግ በመካሔድ ላይ በሚገኘው ስብሰባ በሥምምነቱ ከዓለም ገበያ ከቀረበው እህል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከፍተኛ ገቢ ወይም ከአማካኝ በላይ ገቢ ላላቸው አገራት እንደቀረበ ተናግረዋል። 

" ምዕራባውያን አገሮች በአንድ በኩል የእህል እና የማዳበሪያ አቅርቦታችን እያስተጓጎሉ ነው። በሌላ በኩል አሁን በዓለም የምግብ ገበያ ለተፈጠረው ቀውስ ግብዝ ሆነው እኛን ይከሱናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

በሴንት ፒተርስበርግ እየተካሄደ ባለው የሩስያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምረ የሌሎችም ሀገራት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንት ፑቲን ትላንት ረቡዕ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ከግብጽ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

#ዶቼቨለ

@tikvahethiopia