" የ10 በመቶ የተርን ኦቨር ታክስ ተነስቷል "

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ይሰበስብ የነበረውን አሥር በመቶ የተርን ኦቨር ታክስ (ቲኦቲ) ማንሳቱን ሪፖርተር አስነብቧል።

ቢሮው ከገንዘብ ሚኒስቴር አገኘሁት ባለው ማብራሪያ መሠረት፣ በኮድ 03 የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትን ተሽከርካሪዎች ነው የተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ ተግባራዊ እንዳይሆንባቸው የወሰነው፡፡

ተሽከርካሪዎቹ በንግድ ሥራ ፈቃዳቸው ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ቢልም፣ ሊብሬያቸው የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆኑ በመጥቀሱ አሥር በመቶው የአገልግሎት ሰጪዎች ተርን ኦቨር ታክስ ተግባራዊ ይደረግባቸው ነበር፡፡

ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ታዬ ማስረሻ ተፈርሞ ለአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞችና ለአምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተላከው ደብዳቤ፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ የሜትር ታክሲ ተሽከርካሪዎች ከሁለቱ ታክሶች ነፃ እንዲሆኑ አስታውቋል፡፡

ደብዳቤው ላይ " የሚሰጡት አገልግሎት የትራንስፖርት በመሆኑ የንግድ ሥራ ገቢ ግብርን በተመለከተ ግብር ከፋዮች የሚያቀርቡት የሒሳብ መዝገብ፣ የሒሳብ መዝገብ ካልያዙ ደግሞ በመረጃ እንዲስተናገዱ "  ይላል።

በገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኘሁ ካሳዬ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ፥

" የሜትር ታክሲዎች የብቃት ማረጋገጫቸው የመኪና ኪራይ የሚልና ኮድ 3 ሰሌዳ የሚወስዱ ቢሆንም፣ በኮድ 1 ተሽከርካሪዎችም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ይህ ደግሞ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡትን የተለያየ የታክስ አከፋፈል ስለሚተገበርባቸው ቅሬታ ሲያስነሳ ነበር።

የኅብረተሰቡን የትራንስፖርት ጫና በማየትና ተሽከርካሪዎችን እንደ ኮድ 1 በመቁጠር፣ ቢሮው ታክሱን አንስቷል።

በኮድ 3 የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ከታክሱ ነፃ መሆን ዕድል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፣ እነሱን ለመለየት በሲስተሙ ላይ እየሠራ ነው።

የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም መረጃ እየሰበሰብን ነው። "  ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Credit : #ሪፖርተር

@tikvahethiopia