TIKVAH-ETHIOPIA
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ለቀው ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ ፓርላማውም እንዲበተን ጠየቁ። ዶ/ር ደሳለኝ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ መሆኗን እና ለዚህም የዳረጋት " የብልፅግና መራሹ መንግስት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደቀ አመራር " ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሀገሪቱን ከዚህ ችግር ለማውጣት የሀገራዊ ቀውስ መፍትሄ አፈላላጊ ጉባኤ እንዲዘጋጅ…
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ምን አሉ ?

የተ/ም/ቤት አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ፦

" ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ መንበረ ስልጣን ከወጡበት ከመጋቢት 2010 ዓ/ም ጀምሮ እየተወሳሰቡ የሄዱት የሀገራችን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አሁን ላይ ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ መሸጋገራቸውን ማሸፋፈን ወደማይቻልበት ደረጃ ደርሰዋል።

ብልፅግና መራሹ መንግስትዎ ፦
- የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት ፣
- ነጋዴው ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ እና ነግዶ የሚኖርበት
- ገበሬው ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ አግኝቶ አርሶ የሚበላበት እንዲሁም ከተሜውን የሚቀልብበት ሁኔታ መፍጠር አልቻለም።

የኢትዮጵያ ህዝብ በችጋር እየተጠበሰ፣ በረሃብ እየተሰቃየ ነው።

የኑሮ ውድነቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ወገናችንን ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑሮ እንኳን መግፋት ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል።

ኢኮኖሚው ታሟል፣ መካከለኛ ነዋሪ የነበረውም ተመቶ ወደ ድህነት ወለል ወርዷል።

ስራ አጥነት ተስፋፍቷል፣ የሀገራችን የነገ ተስፋ የሆኑ ወጣቶችም ሀገራቸው ውስጥ ተስፋ በማጣታቸው ስደትን ብቸኛ ምርጫ አድርገውታል።

ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ይታገታሉ በሚሊዮን ብር ይጠየቅቸዋል፣ የመንግስት የፀጥታ መዋቅር በተለይም ፖሊስ ደግሞ አማራዎችንን እና የአማራ ልሂቃንን የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን በማንሳታቸውና መንግሥትን በተለያየ ማንገድ በመተቸታቸው ብቻ የፈጠራ ወንጀል እየተሰጣቸው በማንነታቸው በጅምላ ይታሰራሉ ፣ በጅምላ ይከሰሳሉ ፍርድ ቤት ነፃ ሲላቸው ፖሊስ ግለሰቦችን አስሮ ያቆያል።

የኢትዮጵያ መልካፖለቲካ በሙሉ ያዳረሰ በሚባል ደረጃ ሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች የደም ምድር ሆነዋል።

ሙሉ አማራ ክልል አዲስ የጦርነት ቀጠና ተደርጓል፣ ከፊል ኦሮሚያ ክልል የጦርነት ቀጠና ሆኖ ባጅቷል፣ ትግራይ አማራ እና አፋር ፋይዳ ባልነበረው የብልፅግናና የህወሓት የስልጣን ጦርነት ምክንያት ደቋል። ቤኒሻንጉል ፣ጋምቤላ፣ አብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችም ከሌሎች የተለየ አይደለም።

በማህበራዊ ዘርፍም ወንጀል ተበራክቷል፣ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች / ዜጎች በመንግስት ቤታቸው ፈርሶ ጎዳና ላይ ወድቀዋል ፤ እንደ ብልፅግና ሹማምንት አባባል ' ህጋዊ ድሃ ተደርገዋል ' ።

በሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በሰሜኑና በምዕራቡ ሀገራችን ክፍሎች በነበረው ጦርነት እና ማንነት ተኮር ጥቃቶች የውስጥ ተፈናቃይ ሆነው የሰቆቃ ኑሮን ይገፋሉ።

ባለፉት 5 ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን ተነጥቀዋል። ለዚህ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ምስቅልቅል ቀውስ እና ውድመት ወይም ሀገራዊ መክሸፍ ዋነኛው ተጠያቂው የብልፅግና መራሹ መንግስት እና የእርሶ የወደቀ አመራር  / failed leadership ነው።

ገዢው ፓርቲ ብልፅግናን አመጣለሁ እያለ ቢምል ቢገዘትም በተግባር ለኢትዮጵያ ህዝብ ያመጣለት ግን ጉስቅልና ሆኗል።

ብልፅግና ሀገርን ከቀውስ ማውጣት ካልቻለ እና ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የብልፅግና / የአገዛዙ አገልጋይ በመሆናቸው እና የችግሩም አካል በመሆናቸው ከፓርቲዎቹ የሚጠበው መፍትሄ አይኖርም።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለወደቀው የእርሶ እና የብልፅግና ፓርቲዎ አመራር መፍትሄው ምንድነው ? የሀገራዊ ቀውስ መፍትሄ አፈላላጊ ጉባኤ እንዲዘጋጅ አድርገው ስይረፍድ ለሀገራዊ ቀውሱ መላ ቢበጅ አይሻልም ወይ ? እንደእኔ እንደ አንድ የህዝብ ተወካይነቴ ብልፅግና ፓርቲ መራሹም ሆነ ፓርላማው ሀገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት ስለማይችሉ ስልጣኖን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 60 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት በምክር ቤቱ ፍቃድ ምክር ቤቱን እንዲበትኑ እና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ መጠየቅ እፈልጋለሁ።

አመሰግናለሁ ! "

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia